የዩቱዩብ ‘ኮመንቶች’

0
188

የቴክኖሎጂ ዘመን ብዙዎችን የመረጃ ፍሰቶች ቀይሯቸዋል። ከኢንተርኔት በፊት የነበረው ጊዜ አሁን ሲመለከቱት አልፈውት የሄዱ ጨለማ መንገድን ይመስላል። በወቅቱ የሚጠላ አልነበረም። አሁን የተሻለ ዘመን ሲመጣ የጥንቱን ጠላነው እንጂ።

ኢንተርኔትን ተከትሎ ደግሞ  ዩቱዩብ፣ ፌስቡክ፣ ቲክታክ፣ ኤክስ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕ እና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃ በብዙዎች እጅ እንዲመረት ማድረግ አስችለዋል።

ዛሬ ግለሰቦች ከትላልቅ የሚዲያ ተቋማት በላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜም ከመንግስት በላይ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ያላቸው ተሰሚነት ሲበልጥ እናያለን።

መረጃ የሚታፈንበት፣ በብቸኝነት የሚሰራጭበት፣ ለልዩ ተልዕኮ የሚዘጋጅበት ዘመን ፈተና ውስጥ ገብቷል። የመረጃ ጋጋታ ዘመን ነው። ቆም ብሎ ለመተንተን በሚያስቸግር ፍጥነት እና ብዛት መረጃ ይሰራጫል።

1998 ዓ.ም ትዝ የሚለኝ ነገር አለ። በሰፈራችን ሁለት ቴሌቪዥን ያለባቸው ቤቶች ነበሩ። የኢቲቪ “መቶ ሀያ” ፕሮግራምን ለማየት የምንከፍለውን ዋጋ አሁን ሳስበው በእነዚህ ትንሽ ዓመታት የቴክኖሎጅ ለውጥ ያስደንቀኛል።

ያንን አንድ ለእናቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማየት ሳምንት ሙሉ እሁድን መጠበቅ ነበረብን። በሰው አጥር አይናችንን አጮልቀን፣ እግራችሁን አልታጠባችሁም፣ ወንበር እንዳታቆሽሹ፣ አጥር እንዳትደገፉ እየተባልን  ሁሉንም ማስጠንቀቂያ እና ዛቻ ታግሰን ከማየት ውጪ ምርጫ አልነበረንም።

በጥቂት ዓመታት ልዩነት ውስጥ የአንድ መረጃ አሰራጭ ባለቤትነት ከጠቅላይነት ለብዙኀን ሆኗል። ዛሬ ብዙኀኑ የመረጃ አሰራጭ ሆነዋል። ከአንድ ማዕከል የሚሰራጭ መረጃ አሁን ከብዙ ወገን ሆኗል።

በቀደመው ዘመን ሰዎች በአንድ ዜና ላይ ያላቸውን ስሜት ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይነጋገሩበት ይሆናል። ዘንድሮ ግን በስልካቸው ቀርጸው በፈለጉት ማሕበራዊ ሚዲያ ሐሳባቸውን፣ ስሜት እና ግላዊ ምልከታቸውን ለብዙኀኑ ማጋራት ይችላሉ። ሐሳቡ ካልተዋጠላቸው የመልስ ሐሳብ ይሰጡበታል። ጥሩ ከመሰላቸው አድናቆታቸውን ያንጸባርቁበታል። ዘመኑ የመልስ ምት መስጫ (የሪያክሽን) ነው። ዜና አሰራጩ ሐሳቡን የተለመበት መስመር ብቻ ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በአንዲት ዜና ሕዝብን በአንድ ሐሳብ ላይ አንድ ዓይነት ዕይታ እንዲኖረው ማድረግ ከባድ ሆኗል። አንድን መረጃ ከብዙ ወገን የሚተነትኑ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች፣ ፖለቲከኞች እና  ምሁራን ብዙ ሆነዋል።

ይህ ዘመን ሐሳቦች በነጻነት ይንሸራሸሩ ዘንድ በቴክኖሎጂ የፈቀደ ነው። ቀድሞ ሰው በሰማው ዘፈን፣ በተመለከተው ዜና፣ ባነበበው ጋዜጣ ወይም መጽሔት ላይ ሐሳብ መስጠት ቢፈልግ የጋዜጣውን፣ መጽሔቱን ወይም ቴሌቪዥን ጣቢያውን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ማክበር ይጠበቅበታል። ካልሆነ ሐሳቡ ታፍኖ ይቀርበታል። የላከው ሐሳብም ላይተላለፍለት ይችላል። ሲናገርም ከብዙ አቅጣጫ ለትርጉም ተጋላጭነትን በማሰብ እና ሊያመጣበት የሚችለውን ውጤት እያሰበ ነው።

አሁን ያ ታሪክ በብዙ ተቀይሯል። እንዲያውም ኢንተርኔት እና ስልክ ያለው ሁሉ የፈለገውን ሐሳብ መናገር የሚችልበት ዘመን ነው።

ከብዙ የማህበራዊ ሚዲያ አንዱን መርጠን የሐሳብ ነጻነት እና ቅብብሎሽን እንመለከታለን። ዩቱዩብ ማህበራዊ ሚዲያ ዛሬ የ20 ዓመት እድሜ ያለው ግዙፍ የመረጃ ማሰራጫ እና ገንዘብ ማግኛ ድርጅት ነው። በየካቲት ወር እ.አ.አ በ2005 ነበር አሜሪካ ውስጥ የተመሰረተው።

ዩቱዩብ የሐሳብ መድረክ ነው። 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ቪዲዮዎች በየቀኑ ይጫኑበታል። 122 ሚሊዮን ሰዎች በቀን ይጠቀሙበታል። አንድ ቢሊዮን ሰዓት በቀን ይታያል። በቀን አምስት መቶ ሺህ የዩቱዩብ ቻናሎች ይከፈታሉ።

ሕንድ 476 ሚሊዮን የዩቱዩብ ተጠቃሚዎችን በመያዝ በዓለም ቀዳሚ ናት። ከጎግል ቀጥሎ በሰርች ኢንጅን ማሽን ኢንተርኔት ላይ ሰው ከሚጠቀምባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ ይጠቀሳል። ከዓለም ህዝብ 2 ነጥብ አራት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል። በ2024 እ.አ.አ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የድርጅቱ የማስታወቂያ ገቢ 8 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ነበር።

በተወዳጅነት ከፌስቡክ ቀጥሎ ይቀመጣል። 63 በመቶ የሚሆኑት የዩቱዩብ ተመልካቾች በስልካቸው የሚጠቀሙ ናቸው ሲል ግሎባል ሚዲያ ኢንሳይት ድረ ገጽ አስፍሯል። በአማካይ ሲታይም  እያንዳንዱ የዩቱዩብ ተመልካች በቀን በአማካይ 19 ደቂቃዎችን በመመልከት ያሳልፋል።

113 ሚሊዮን  በስራ ላይ ያሉ የዩቱዩብ ገጾች አሉት። በቀን 5 ቢሊዮን የቪዲዮ ዕይታዎች አሉ። እነዚህ መረጃዎች ወደ ሀገራችን የዩቱዩብ ተጠቃሚዎች ይወስዱናል። በሀገራችን ዩቱዩብ በማደግ ላይ ካሉ እና ብዙ ለውጥ እያመጡ ካሉ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መካከል አንዱ ነው። ብዙዎች ሚሊዬነር እየሆኑበት ነው። ብዙዎች እንጀራቸው አድርገውታል፤

ብዙዎች ትምህርት ቤታቸው አድርገውታል፤ ብዙዎች ስራቸው እና የስልጠና እና አመለካከት ለውጥ ማግኛ መድረክ አድርገውታል፤ የሃይማኖትም ቦታ ጭምር ሆኗል። በአጠቃላይ መዝናናት፣ መማር፣ ማወቅ የሚሉ የሚዲያ አንኳር ጥቅሞች ዩቱዩብ ውስጥ አሉ።

ከምንም በላይ ዩቱዩብ የሐሳብ ነጻነትን ፈቅዶ እንመለከታለን። ሰዎች ሐሳብ፣ ስሜት፣ ትዝታ፣ ትዝብት፣ አድናቆት፣ ወቀሳ፣ እውቀት እና የሕይወት መረዳታቸውን በነጻነት የሚያሰፍሩበት ሚዲያ ነው።

የዩቱዩብ “ኮመንቶች”

በዩቱዩብ ሐሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ የተለያዩ ሐሳቦች ይሰነዘራሉ። በዩቱዩብ ሙዚቃዎች ላይ የተሰጡ ጥቂት ሐሳቦችን እንመልከታቸው እስኪ።

የቴዎድሮስ ታደሰ እና አሰፉ ደባልቄ “አትባቢ ስለይሽ” የሚለው ዘፈን  ከ 12 ዓመታት በፊት  ዩቱዩብ ላይ ተጭኗል። 2 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል። 492 ሐሳቦች ተጽፈውበታል። ብዙ ሐሳቦች አድናቆት፣ ሙገሳ እና ለሁለቱ ዘፋኞች የተሰጡ ፍቅሮች ናቸው።

እንዲሁም የድሮ ዘመን ሙዚቃዎች እንዴት ምርጦች እንደነበሩ የዛሬዎቹ ደግሞ ጥራዝ ነጠቅ ናቸው በሚል ሐሳቦች ተነስተዋል። የቀደሙትን ማወደስ የአሁኖቹን ደግሞ የማሳነስ ሐሳቦች ተነስተዋል። ዘፈን ድሮ ቀረ የሚሉ ሐሳቦች ናቸው።

“እውነት በእናንተ ጊዜ ተፈጥሬ  ብሞት በጣም ነበር ደስ የሚለኝ ይህን ክፉ ዘመን ከማየት…!”  የሚል ያንን ዘመን የሚናፍቅ ሐሳብ ሰፍሯል። ቀጥሎም  በአዲስ አበባ መድኅኔዓለም ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት የገጠመውን ሁኔታ “እኔ የማስታውሰው ደጃች ውቤ ሰፈር  በዚህ ዘፈን ስንጨፍር እና ስንጠጣ አድረን በነጋታው ወደ ትምህርት ቤት ሂድ ተብዬ አልሄድም ብዬ ስገረፍና አባቴ ወስዶ ትምህርት ቤት ካደረሰኝ በኋላ ተመልሼ ወጥቼ ተባርሬያለሁ። ይህንን ስሰማ በጣም ወደ ኋላ እያስታወስኩ እንባዬ ይመጣል” ብሏል።

“ይህንን ሙዚቃ አራተኛ ሜካናይዝድ ቢኤም ምድብተኛ  ውጊያ እያለሁ ትዝታ አለብኝ” ሲልም ሌላ ሰው ሐሳብ አስፍሯል። ሌላም ሰው እንዲሁ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ትምህርት ቤት እንማር ነበር። በጣም ልጆች ነበርን። የቀድሞ ወታደሮች በጣም ይወዱት ነበር የሚል ሐሳቡን የሐሳብ ሳጥኑ ውስጥ አስፍሯል። “በዚያ ዘመን መወለድ መታደል ነው። አሁን የምንኖረው አርቴፊሻል ኑሮ ነው፤ እባካችሁ መልሱን ናፍቆናል” ሲል  በትናንትናው ናፍቆት ውስጥ ሆኖ ጽፏል።

ሙዚቃ ትዝታ ነው። ሙዚቃው በወጣበት  ዘመን ሰዎች ከነበራቸው አኗኗር፣ ገጠመኝ፣ ሕይወት፣ እና ትዝታ ጋር በማያያዝ ያደምጡታል። ትርጉም ይሰጡታል። ይህ ሙዚቃ 1982 ዓ.ም ነበር የወጣው። ዛሬ ላይ የዚያ ዘመን ልጆች ጎልማሳዎች ሆነዋል። ሙዚቃውን ያደመጡበትን ዘመን ትዝታ በማንሳት በዚያ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ በዚያ ጊዜ እንዲህ ነበርሁ የሚሉ ሐሳቦችንም የሚሰጡት ከሙዚቃ የትዝታነት ባህሪ አንጻር ነው።

“ብታምኑም ባታምኑም ይሄንን ሙዚቃ እየሰማሁ ሰክሬ ውጪ አድሬያለሁ። ቤት ስገባ የተመታሁት አይረሳኝም። መቼም አይ ጊዜ፤ ፍቅር ነበረን፤ ሰላም ነበረን” ብሎ አንድ ሰው ሐሳቡን አስፍሮ አስነብቦናል። ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ ላይ ምላሽ ሰጥተውበታል። ሐሳቡን መጋራታቸውን እንመለከትበታለን።

በዩቱዩብ ሙዚቃዎች ስር በርካታ ውይይቶች፣ የሐሳብ ምልልሶች እና አስተያየቶች ይጻፋሉ። ከዘጠኝ  ዓመታት በፊት በግል የዩቱዩብ ገጿ የጫነችው የአቢ ላቀው የኔ ሐበሻ ሙዚቃ 89 ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል። 31 ሺህ ሐሳቦች ተጽፈውበታል። የመልካም ምኞት፣ አድናቆት፣ ፍቅር ሐሳቦችም ቀርበዋል።

ከሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ፣ ከሕንድ፣ ዩጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስፔን፣ ግብጽ፣ ሴራሊዮን፣ አንግሊዝ፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች ሀገራት ሰዎች የኢትዮጵያን ሙዚቃ እንሰማለን የሚሉ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወዳጆች በተደጋጋሚ ሐሳብ ጽፈዋል። አድናቆታቸውንም አስፍረዋል።  ሙዚቃው በአማርኛ ቋንቋ ቢቀርብም እንኳን “ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው” በሚለው ባህሪው ድንበር እና ዘርን ይሻገራል። “እኔ ሶማሊ ነኝ የኢትዮጵያን ሙዚቃ እወዳለሁ። እርስ በርስ መጠላላታችንን እናቁም። እንደ እፍሪካዊ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንቁም” ሲል ጽፏል።

ሐይማኖታዊ መልእክቶች፤ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞቶች፣ ስብከቶች፣ እና ሌሎች መልካም ይዘት ያላቸው ሐሳቦች ቀርበዋል።

የሚጻፉ ሐሳቦች አንዳንድ ጊዜ ከሙዚቃው ዋና ሐሳብ ጋር ተያያዥ ሆነው ይነሳሉ። ሙዚቃው ጠንከር ሲል ጠንከር ያሉ ሐሳቦች ይቀርባሉ። በአንጻሩ ዘፈኖቹ ፓለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ  የሚሰነዘሩትም ሐሳቦች ፖለቲካዊ ቅርጽ ይይዛሉ።

ሐሳብ እንደሚሰጠው ሰው ሁኔታ እና ስሜት ልዩነት ሐሳቦችም ልዩነት ይፈጥራሉ። አንዳንድ ጊዜ የፍቅር ሙዚቃ ላይ ስድብ ወይም የፖለቲካ ሐሳቦችን የሚጽፉም አሉ። ወይም ደግሞ መድረኩ ከተገኘ አይቀር ብለው ሐይማኖታዊ መልእክቶችን የሚያሰፍሩ አሉ።

በብዛት ስለሀገር  በተዜሙ ሙዚቃዎች ውስጥ መብሰልሰል እና ናፍቆት፣ ጸጸት እና ብቸኝነትን እናስተውላለን። ሐሳብ ሰጪዎች ስልካቸውን ሙዚቃ ከማድመጥ ባለፈ የሚፈጠርባቸውን ስሜት ለመግለጽም ሐሳብ ይጽፋሉ።

የማስተዋል እያዩ “መጥቼ ነበር” ዘፈን በኤላ ሪከርድስ ዩቱዩብ ቻናል ላይ ከዓመት በፊት ተጭኗል። ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል። ዘጠኝ መቶ ሰዎች ሐሳብ ሰጥተውበታል። የሙዚቃው መልእክትም በሞት መለያየትን ነው የሚያሳየው። ሰው እኖራለሁ በሚል ምኞት ድንገት ጤዛ ሲሆን በዘፈኑ ውስጥ እንመለከታለን።

የሙዚቃውን፣ የዘፋኙን፣ የዜማ እና ግጥም ደራሲዎች አቅም የሚያወድሱ በርከት ያሉ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። ለዚህ ይመስላል “የዚህ ሙዚቃ ትልቁ ችግሩ ማለቁ ብቻ ነው” የሚል ሐሳብ የተሰጠው። ከሦስት መቶ በላይ ሰዎችም ይህን ሐሳብ መውደዳቸውን ገልጸዋል።

“ይሄን ዘፈን የምሰማው በለቅሶ ነው። መና ለቀረው ልጅነቴ፤ ከ16 ዓመቴ ጀምሬ አረብ ቤት የተቀቀልኩ ለውጥ ለሌለው ሕይወት። 16 ዓመት አረብ ቤት ድካም ብቻ” የሚል ሐሳብ በዚህ ሙዚቃ ስር ተጽፏል። ሙዚቃው ከባድ የኀዘን ስሜት የመፍጠር አቅም አለው። ይህን ሐሳብ ያቀረበው ሰው በብሶት ውስጥ የሚኖር፤ የሕይወት ተስፋ ያጣ ነው። አጋጣሚው ሲገኝ ስሜቱን በመተንፈሱ ጊዜያዊ ረፍት ያገኝ ይሆናል። ሌሎች ሐሳቡን የሚጋሩትም ሰዎች አጽናኝ ሐሳብ ሰጥተዋል።

“አላህ ይቅር ይበለኝ፤ ይሄው ገና ዛሬ ሰማሁት ይሄን ሙዚቃ። በረመዷን እያዳመጥሁት ነው። ልቤን ጎትቶ ሊያወጣው ነው። ገራሚ ሙዚቃ ነው” የሚል ሐሳብ የሙዚቃውን ጉልበት ያሳያል። የሐሳብ ሰጪውንም ሁኔታ፣ስሜት እና ጊዜ በሚገባ ተንጸባርቆ እናያለን። ርግጥ ደግሞ የሐሰት እና ጥላቻ ሐሳቦች እንደሚሰነዘሩም መረሳት የለበትም።

በርካታ ሙዚቃዎችን ስንመለከት ሕዝባችን ምን እና  እንዴት ያስባል የሚለውን ፍንጭ እናገኛለን። ምንም እንኳን ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም በአንጻራዊነት የዩቱዩብ ሐሳቦች ማንነትን ሳይገልጹ የሚጻፉ በመሆናቸው ግልጽ እና ነጻ የመሆን ዕድል አላቸው።

ብዙዎች ትካዜ እና ለቅሶ ውስጥ ሆነው ሙዚቃውን ማድመጣቸውን ጽፈዋል።

“ይሄን  መልእክት  የምታነቡ ሁሉ ፈጣሪ ያልታሰበ በረከት በሕይወታችሁ ይፈጽምላችሁ” የሚል ሐሳብ በዚህ ዘፈን ስር ተጽፏል። በብዙ ቪዲዮዎች ስር የሚደጋገም ሐሳብ ነው።

ዩቱዩብ የሐሳብ ሜዳ እና የሙግት ሸንጎ ሆኗል። ብዙዎች እርስ በርስ ሐሳብ በመመላለስ ይከራከሩበታል፤ ይመካከሩበታል፤ አጀንዳ ይይዙበታል። ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ፍቅር ግለሳባዊ ጉዳዮች፣ ኢኮኖሚ፣ ስራ፣ ደስታ እና ኀዘን በአጠቃላይ የሰው ልጆች የሚሰማቸውን ሐሳብ ለመግለጽ ይጠቀሙበታል።

አንዳንድ ጊዜ ከቪዲዮው ይልቅ በስሩ የሚንሸራሸሩ ሐሳቦች ክብደት ኖሯቸው እንመለከታለን። ሰዎች ያለ ገደብ ሐሳብ የሚሰጡበት በመሆኑ የነጻነት ሜዳነቱ ከዚህ የሚነሳ ነው። መዝናናት፣ መማማር እና ማሳወቅ የሚሉ የሚዲያ ቁልፍ ዓላማዎች በየዘርፉ ይስተናገዱበታል።

የዩቱዩብ ሐሳቦችን አንስተን አንዘልቃቸውም፤ እየተዝናናችሁ እንድታነቡ በመጋበዝ እሰናበታለሁ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here