የግጭት እና የጦርነት መዘዝ

0
230

በጦርነት ወይም በግጭት ቀጣና የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጦርነቱ ተሳታፊ ባይሆኑ እንኳ የዳፋው ቀማሾች ናቸው፡፡ በተለይም ጦርነት በሴቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡  ምክንያቱ ደግሞ   በግጭት እና በጦርነት ጊዜ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፣ ከሚኖሩበት ቀዬ ይፈናቀላሉ፣ የጤና አጠባበቅ እና የኑሮ አለመደላደል  ያስከትልባቸዋል በማለት ዩናይትድ ኔሽን ፖፑሌሽን ፈንድ በድረ ገጹ ያትታል፡፡

ለአብነትም በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የበለጠ ተጎጂ እየሆኑ ካሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች እና ሕጻናት በግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህንንም በየጊዜው ከሚወጡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርቶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ብዙውን ጊዜ የጦር ወንጀሎች የሚፈጸምባቸው ሕጻናት እና አዋቂ ሴቶች  በግጭት ወቅት ለአስገድዶ መደፈር፣ ለወሲብ ባርነት እና  ለሴተኛ አዳሪነት ይጋለጣሉ፡፡ ከነዚህ ጥቃቶች  ባለፈ ሴቶች ለግድያ፣ በጾታዊ ጥቃቱ ምክንያት ላልተፈለገ እርግዝና  እና ለሕገ – ወጥ ውርጃ ይዳረጋሉ፡፡

መረጃው እንደሚያመላክተው ግጭቶች ብዙውን ጊዜ ወደ መፈናቀል ያመራሉ፡፡ ሴቶች  በሚሰደዱበት   ወቅትም ለጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ። በተለይም በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ሲሰፍሩ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለጾታዊ ትንኮሳ በጣም ተጋላጪ ናቸው። መሰረታዊ የምግብ፣ የመጠለያ እና የመጓጓዣ  ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ሲሉም ወሲብ ሊፈጽሙ ይችላሉ። በዚህም ለአባላዘር በሺታዎች ይዳረጋሉ፡፡

ሌላው ግጭቶች እና ጦርነቶች  የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶችን በእጅጉ ይጎዳሉ፡፡ በተለይም በጦርነት ጊዜ ሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የእናቶች ክብካቤ እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡ በመሆኑም በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሺታዎች እንዲሞቱ እና ዘላቂ የጤና ዕክል እንዲያጋጥማቸው ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም ጦርነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን  ስለሚያደናቅፍ ሴቶች ገቢ ለማግኘት ይቸገራሉ፤ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርም ከባድ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል፡፡

ግጭቶች በተከሰቱበት አካባበቢ የተረጋጋ ሰላም ስለማይኖር  ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፡፡ ይህም ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡ ሴቶች በጦርነት ጊዜ በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት ለከፋ የአዕምሮ ጤና መታወክ ይዳረጋሉ፡፡

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ከጦርነት በኋላ ሴቶች በተለይም እናቶች ብዙውን ጊዜ በጦርነቱ  የተጎዱትን ወይም አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ልጆቻቸውን፣ የትዳር አጋሮቻቸውን ፣ ዘመዶቻቸውን  ወይም የቤተሰብ አባላትን እንዲንከባከቡ ይደረጋል።  ይህም  ኑሯቸው  ላይ ጫና ስለሚፈጥርባቸው ሕይወታቸውን በፈለጉት  መንገድ እንዲመሩና ከፈለጉት የስኬት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ  አያስችላቸውም፡፡

ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ጦርነት እና ግጭት በሕጻናት እና አዋቂ ሴቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ ነው።  እ.አ.አ በ2023 በትጥቅ ግጭቶች የተገደሉት ሴቶች ቁጥር ከ2022 ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል። በ2023 በግጭት ምክንያት ከሞቱት ዐሥር ሰዎች አራቱ ሴቶች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አረጋገጥኩት ብሎ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ከግጭት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ቁጥር ደግሞ  50 በመቶ ጨምሯል።

በተጨማሪም በጦርነት ቀጣና ውስጥ ያሉ ሴቶች በተገደበ የጤና አገልግሎት እየተሰቃዩ ነው። በየዕለቱ 500 ሴቶች በግጭት በተጠቁ ሀገራት ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይሞታሉ። እ.አ.አ በ2023 መገባደጃ ላይ በጦርነት በምትታመሰው ጋዛ ውስጥ 180 ሴቶች  በየቀኑ  ያልተሟላ የሕክምና አገልግሎት  ሳያገኙ ይወልዱ ነበር፡፡

ለብዙ ዓመታት በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክሮች ቢደረጉም ፣የሴቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማረጋገጥ ቢሞከርም የውሳኔ አሰጣጡ በወንዶች ቁጥጥር ስር (አብዛኛዎቹ መሪዎች አምባገነነ በመሆናቸው) በመዋሉ ችግሩ ሊፈታ አልቻለም።

ምንም እንኳን ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴቶች በሚሳተፉበት የሰላም ስምምነት ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ እና በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ቢሆኑም በ2023 በሰላም ሂደት ውስጥ ሴቶችን ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶውን ብቻ ተደራዳሪ ያደረጉ ነበሩ።

በተመሳሳይ በሱዳን በሴቶች የሚመሩ 49 ድርጅቶች   የሰላም ሂደት እንዲፈጠር ግፊት እያደረጉ ነው። ቢሆንም ግን እነዚህ ጥረቶች በአብዛኛው ያልተደገፉ ወይም በመደበኛ የሰላም ድርድር ውስጥ ዕውቅና የሌላቸው ናቸው፡፡

በሪፖርቱ ከተለዩት የሴቶች የሰላም እና የጸጥታ ቁርጠኝነት ቁልፍ ተግዳሮቶች አንዱ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ነው። ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሴቶችን መብት የሚደግፉ ድርጅቶች እና ንቅናቄዎች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው አስፈላጊውን  እርዳታ በወቅቱ እንዳይደርሳቸው እንቅፋት ሲሆንባቸው ይስተዋላል።

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እ.አ.አ በ2023 የዓለም ወታደራዊ ወጪ ሁለት ነጥብ 44 ትሪሊዮን ዶላር (ለዘርፉ እስካሁን ወጪ ከሚደረገው ክብረ ወሰን የሆነ) ደርሷል። በአንፃሩ የሴቶችን መብት ለሚደግፉ ድርጅቶች እና እንቅስቃሴዎች የሚሰጠው የገንዘብ መጠን እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ይህም በዓመት ከጠቅላላ እርዳታ ውስጥ ዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶው ብቻ ነው፡፡

በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሥርዓተ ፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ድጋፎች ከሁሉም ሰብአዊ ወጪዎች ውስጥ ከአንድ በመቶ በታች ናቸው።

እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተከሰቱ ያሉት በጦርነት ጊዜ ሴቶችን እና ሕጻናትን ለመጠበቅ የተነደፈው ዓለም አቀፍ ሕግ ባለመተግበሩ እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል፡፡

በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የፀደቀው ሕግ ግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት የሴቶችን ደኅንነት ማረጋገጥ  እና ሴቶች በሰላም ሂደቶች ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነበር፡፡

እ.አ.አ በ2025 ዓለም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን እና ለሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብቶችን ለማበረታታት የታቀዱ ተከታታይ ጉልህ ዓለም አቀፍ ተግባራትን ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም  በጦርነት ጊዜ በሴቶች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም በጦርነት እና በግጭት ምክንያት   በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመቀነስ  የሚፈጠሩ ግጭቶችን በድርድር መፍታት መለመድ እንዳለበት መረጃው አመላክቷል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here