በዓለማችን 9100 ባለ አራት ጐማ ተሽከርካሪዎችን ጭኖ የማጓጓዝ ዓቅም ያለው መርከብ ቀደም ብሎ 8500 በመጫን አንደኛ የነበረውን በልጦ ቀዳሚ ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል::
በቻይና ጂያንግዙ ከባድ ተሽከርካሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በ2024 እ.አ.አ ነው የተመረተው -የተሽከርካሪ ማጓጓዥ መርከቡ፤ የጐን ስፋቱ 37 ነጥብ 5፣ ርዝመቱ ደግሞ 200 ሜትር ተለክቷል::
የመረከቡ ስሪት ጠንካራ እንዲሆን የተጠበቡበት መሀንዲሶች በ14ቱም ወለሎች ተሽከርካሪዎችን የመሸከም ዓቅም አጐልብተውለታል:: የግዙፉ መርከብ አስደናቂነቱ የጭነት ልኩ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢ ተስማሚ ማለትም ከባቢ ዓየርን የመበከል ደረጃው በእጅጉ ያነሱ መሆኑ በዋናነት ተጠቁሟል:: ለዚህ ደግሞ በመርከቡ የላይኛው ክፍል 1500 ካሬ ሜትር ስፋት ካለው የፀሀይ ሃይል መሰብሰቢያ ንጣፍ የሚገኝ ከብክለት የፀዳ ኃይልን ለመንቀሳቀሻ ማዋሉ በውጤትነት ተጠቅሷል::
ግዙፉ የተሽከርካሪ ማጓጓዣ መርከብ አሁን ላይ ከፀሃይ ብርሃን ከ30 እስከ 35 በመቶ ኃይል በመሰብሰብ ተለምዷዊውን ከብስባሽ የሚገኝ ነዳጅ መተካት ችሏል::
የጭነት ማጓጓዣ መርከቦች ድርጅቱ “ሆግ አውቶ ላይነርስ” የበላይ ኃላፊ ሰብጆርን ዳሀል ድርጅታቸው በቀጣይ መርከቦቹን ሙሉ በሙሉ ከብክለት በፀዳ ኃይል ለማንቀሳቀስ ማቀዱን አስታውቀዋል::
ለዚህም በድረጅታቸው ውስጥ ያሉትን 12 ግዙፍ መርከቦች በ2027 እ.አ.አ የካርበን ልቀታቸውን ዜሮ ለማድረስ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያሰመሩበት::
በባህር ማጓጓዣ ዘርፍ የሚሰሩ በርካታ ግዙፍ ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው በተናጠል ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም በመተባበር እና በመቀናጀት የድርጅቶቹ ማጓጓዣዎች ሙሉ በሙሉ ከበካይ ልቀት ነፃ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ ነው ቃል የገቡት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም