የዓለማችን ትንሿ ፓርክ

0
93

በጃፓን ከዋና ከተማዋ ቶኪዮ የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ በኋላ በሚገኘው ናጋዙሚ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አቅራቢያ ከአንድ ካሬ ሜትር ያነሰ የሚሸፍነው መናፈሻ በስፋቱ የዓለማችን ትንሹ የጉብኝት መዳረሻ ሆኖ ክብረ ወሰን መያዙን የዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ድረ ገጹ እንዳስነበበው አበዛኛዎቹ የጉብኝት መዳረሻዎች እጅግ ሰፊ፣ የተለያየ መልካም ድራዊ አቀማመጥ፣ ሰፊ የብዝሃ- ህይወት ሀብትን ያቀፉ ናቸው፡፡ ጐብኚዎችም ያላቸውን ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶች እንደመስፈርት በማነፃፀር ለጉዞ መዳረሻነት እንደሚመርጧቸው ነው የተብራራው፡፡

የጉብኝት መዳረሻዋ ስረ መሰረት በ1988 እ.አ.አ ነው የጀመረው፡፡ በተጠቀሰው ዓመት የናጋዙሚ ከተማ የግንባታ አስተዳደር ሰራተኛ ወደ አሜሪካ ተጉዞ ነበር፡፡ በደረሰበት በኦሪጐን ፓርትላንድ በሦስት ነጥብ አንድ ካሬ ሜትር ክብረወሰን የያዘውን “ሚል ኢንደስፓርክ” ለመመልከት መበቃቱ አገሩ ጃፓን ተመልሶ አዲስ ለመወጠን እርሾ እንደሆነው ነው የተጠቆመው፡፡

የናጋዙሚው ኗሪ አገሩ እንደተመለሰ ጊዜ አላባከነም በቃ በ1988 ትንሿን ፓርክ ገነባ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በይፋ እውቅና ባይሰጠውም የአካባቢው ኗሪዎች  “ከዓለም ትንሿ ፓርክ” የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር፡፡

ትንሿን ፓርክ መገናኛ ብዙሃን ርእሰ ጉዳይ አድርገው በተደጋጋሚ በማንሳታቸውም ከተለያዩ አካባቢ ጐብኚዎች በቦታው በመገኘት ፎቶ ግራፍ ይነሱ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ጐብኚዎቹ ወደየመጡበት ሲመለሱ ያዩትን በማስተዋወቅ የትንሿ ፓርክ ዝና ከቀጣናው አልፎ ከአገር ውጪ መድረስ ችሏል፡፡

የከተማዋ የግንባታ ቡድን ኃላፊ ሹጂ ኮያማ አሜሪካ ደርሰው የተመለሱት መሆናቸውን ልብ ይሏል፤ የትንሿን ፓርክ ልኬታ ለድንቃድንቅ መዝጋቢ ድረጅት ልከው እውነትነቱ ተረጋግጦ የምስክር ወረቀት ወይም እውቅና እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡

በዚሁ መሰረት የድርጅቱ ባለሙያዎች ተፈላጊ መረጃዎችን አሰባስበው እና ልኬታውን አጣርተው በይፋ የዓለማችን ትንሿ ፓርክ ወይም መናፈሻ ስለመሆኗ የክብረ ወሰን ማረጋገጫ መሰጠቱን ነው ድረ ገጹ ማደማደሚያ ያደረገው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here