ማዜ ብሔራዊ ፓርክ

0
100

ከአዲስ አበባ 460 ኪሎ ሜትር ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ዋና ከተማ ከአዋሳ ደግሞ 235 ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል- ማዜ ብሔራዊ ፓርክ፡፡

በ2005 ዓ.ም የተመሰረተው ፓርኩ ስፋቱ 202 ካሬ ኪሎ ሜትር  ተለክቷል፡፡

በፓርኩ ቀጣና በርካታ ወንዞች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ማዜ ወንዝ በመጠን ትልቁ ነው፡፡ የፓርኩ መጠሪያም ይህንኑ ወንዝ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው በድረ ገፆች የሰፈረው፡፡

የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ እሴታቸው ከፍ ያለ መስህቦችን አቅፎ ይዟል፡፡ በፓርኩ ክልል የሚገኙት የጋሞ፣ ቆቻ፣ ጐፋና ኦሞቲክ ጐሳዎች የቀጣናው ጌጦች ናቸው፡፡ ጐሳዎቹ እርስ በርስ ተቻችለው እና ተከባብረው ነው የሚኖሩት፡፡ በዚህም የየራሳቸውን አኗኗር፣ ባህል እና ልምድ ጠብቀው በእጅ የሚሰሩ መገልገያ እና የእደ ጥበብ ውጤቶቻቸውን፣ የማንነታቸውን መገለጫ አድርገው  ለትውልድ በማስተላለፍ ዛሬ ላይ ማድረስ ችለዋል፡፡

ጐብኚዎች በየጐሳዎቹ መኖሪያ ቀጣና ተዘዋውረው ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ውበትን ለመቃኘት በቅድሚያ ከጐሳው መሪ ወይም አገር ሽማግሌ ፈቃድ ማግኘት ግድ ይላቸዋል፡፡

በብሔራዊ ፓርኩ ከሚገኙ፡-

ከዱር እንስሳት – የዱር አሳማ፣ ጐሽ፣ ዝንጀሮ፣ ነብር፣ ከርከሮ እና ጦጣ ይጠቀሳሉ፡፡ የዱር እንስሳቱን ለመመልከትም በወንዝ ዳር ውኃ ለመጠጣት የሚሰባሰቡበት ሰዓት በእጅጉ ተመራጭ እና አመቺ ነው፡፡

ከዓእዋፍ- ከ196 የሚበልጡ ዝርያዎች በቀጣናው ይገኛሉ፡፡ ፓርኩ ከአንዱ ቀጣና ወደ ሌላው የሚፈልሱ ዝርያዎችን ለመመልከትም ያስችላል፡፡

ለዚህም በፓርኩ ክልል በእግር ተዘዋውሮ ለመመልከት አስጐብኚ መያዝ ግድ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከነባር ጐሳዎች ጋር በቋንቋ ለመግባባት አስፈላጊ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በፓርኩ የሚገኙ የእፅዋት ዝርያዎች እንደየ መልከአምድራዊ አቀማመጡ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከፍታ ባላቸው ቦታዎች ደን፣ ዝቅ ባለው ቁጥቋጦ ከዚያ ያነሰው በግጦሽ ሳር የተሸፈነ ነው፡፡

ለጐብኚዎች ከጥር እስከ ግንቦት ያሉት ወራት ይመከራሉ- ዝናብ የማይበዛባቸው በመሆኑ፡፡ ወደ ፓርክ ለማምራት ደግሞ በጂንካ ወይም በሶዶ በኩል በተሽከርካሪ መጓዝ ይመረጣል፡፡

በመረጃ ምንጭነት ዊኪፒዲያ፣ አፍሪካን ቱር ኦኘሬተርን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here