ከመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ለፕላኔታችን ጉልህ የስልጣኔ ምንጭ በሆነው የጢግሪስ እና ኤፍራጠስ ወንዞች መካከል የተመሰረተው ጥንታዊው የሜሶፔታሚያ ስልጣኔ አንዱ ነው። የአሁኑ ዘመን ኢራን እና ቱርክ አብዛኛውን ክልልና በመጠኑም ኢራቅን እና የሶሪያን ያካለለ ሰፊ ግዛት ነበር። በዚህ ስፍራ ተራራማዎቹን አካባቢዎች በቀደምትነት በመስፈር የኩርድ ሕዝብ ተጠቃሽ ናቸው። የኩርድ ሕዝብ ደጋማውን የሜሶፖታሚያ ስፍራ ይዘው መኖር ከጀመሩበት እስከአሁን ድረስ ከ7000 ዓመታት በላይ እንደሚሆናቸው የታሪክ መዛግብት ዋቢ ናቸው።
በታሪክ ውስጥ የማይካድ ሚና የተጫወቱት ኩርዶች እንደ አለመታደል ሆኖ ዛሬ የራሳቸው የሆነ ሉዓላዊ ሀገር የላቸውም። በድንበር በተገናኙት የቱርክ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ኢራን፣ አርመኒያ መጋጠሚያ ውስጥ በሚገኝ ተራራማ ስፍራ በአምስት ሀገራት ተከበው ይኖራሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዳስቀመጠው ኩርዶች በምስራቅ አናቶሊያ የታውሮስ ተራሮች እና በምእራብ ኢራን ውስጥ ባሉት የዛግሮስ ተራሮች መካከል የሚኖሩ የአንድ ዘር እና ቋንቋ ባለቤት የሆኑ ሕዝብ ናቸው። ከዚህም አልፎ በሰሜናዊ ኢራቅ፣ ሶሪያ እና አርመን በሌሎች ኩታ ገጠም አካባቢዎች ይኖራሉ። ኩርዶች በብዛት የሚኖሩት የኢራን ፣ ኢራቅ እና ቱርክ የጋራ አዋሳኝ ድንበሮች መገናኛ አካባቢን አካልለው ነው። ኩርዶቹ በ75ሺ ስኩዌር ማይል መሬት ላይ ሰፍረዋል። በአጠቃላይ ሕዝቡ ከርሰ፣ መሬታቸው ኩርዲስታን እየተባለ ይጠራል። ይህ እንደመጠሪያ ማገልገል የጀመረው ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ አካባቢውን ተቆጣጥረው ያስተዳደሩ የነበሩት ሰልጁክ ቱርኮች የግዛት አካባቢውን ለመለየት የተጠቀሙበት መጠሪያ ሆኖ እስከዛሬ ዘልቋል። በቦታው ኩርዶች ሰፍረውበት ስለነበረም ነው ሰልጁኮች ይህንን ስያሜ የሰጡት። ስለዚህ ኩርድ የሚባል ሀገር በካርታ ውስጥ ይካተት ቢባል በአካባቢው ያሉ ወደ ስድስት ሀገራትን ሊውጥ እንደሚችል ነው የሚነገረው።
ኩርዶች ከምንም በላይ ለቀያቸው ካላቸው ትልቅ ፍቅር የተነሳ ምድራቸውን ለተለያዩ ሀገሮች ተቆራርሶ ቢወሰድም እነርሱ ግን እስከዛሬ ማንነታቸውን እና መሬታቸውን ሳይለቁ እነሆ ይኖራሉ። ኩርዶችን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ባእዳን እጅ ወድቀዋል። አረቦች፣ ሞንጎሎች፣ ሩሲያውያን፣ እንዲሁም በኦቶማን ቱርኮች በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ተገዝተዋል። ነገር ግን ሁልጊዜም ለነፃነታቸው ይታገሉ ነበር።
በኦቶማን ቱርኮች በዓረቡ ዓለም የግዛት አድማሳቸውን ባስፋፉበት ዘመን የኩርዶች እጣ ፋንታም ተመሳሳይ ነበር። ኦቶማን ከቱርኮች ለረጅም ዓመታት እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ቅኝ ገዝተዋቸው ነበር። ይሁን እንጅ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በዓለም ፖለቲካ ላይ የተለየ አሰላለፍ አስከተለ። በኦቶማን ቱርክ በጦርነቱ ተሸናፊ በመሆኗ የእርሷ ግዛቶች በሙሉ ለእንግሊዝ እና ለፈረንሳይ ቡድን በሞግዚትነት እንዲተላለፉ ሲደረግ በመካከለኛው ምስራቅ ክልል የነበረው የኦቶማኖች ተፅእኖ አበቃለት። በዚህም የቀጠናውን ሕዝብ ሕይወት የሚቀይሩ ውሎችን መፈረማቸው አልቀረም።
የሳቨረሱ ውል በ1913 ዓ.ም ላይ በተፈረመበት ወቅት በፊት በኦቶማኖች ያስተዳደሩት የነበረው የኩርዲስታን ሰፊ ግዛት ለኩርዶች ሉዐላዊ ሀገር ሆኖ ይሰጥ የሚል ሀሳብ ተራምዶ ነበር። ይሁን እንጂ በኩርዶቹ አያሌ የደም አፋሳሽ አመፆች ያልተደሰቱት ፈረንሳይ እና እንግሊዝ የኩርዶቹን የነፃ ሀገርነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የኩርዲስታንን ይዞታ ለቱርክ ፣ ኢራቅ እና ኢራን ሸንሽነው ይዞታ አልባ በማድረግ አከፋፈሉት። ከሁለት ዓመታት በኋላ የተደረገው የላውዜን ስምምነት የኩርዲስታኑን ይዞታ ለ3 ጎረቤት ሀገሮች ከፋፍሎ የመስጠቱን ተግባር ሕጋዊ እውቅና በመስጠት አፀናው።
ጥብቅ የድንበሮች ቁጥጥር
ከዚህ ውል ጀምሮ ነው ሀገራቱ የሚዋሰኑባቸውን ድንበሮች አጥብቀው በመጠበቅ ኩርዶቹ አንድነታቸው እንዲዳከም የበታተናቸው ፈታኙ የታሪክ ክስተት የተፈጠረው። ኩርዶቹ ለየሀገራት ተከፋፍለው ተሰጥተው፣ እንዳይገናኙ በድንበር ታጥረው ከቅርብ ርቀት ማዶ ለማዶ እየተያዩ መኖር እንዲሁም በየሀገሩ እየባዘኑ መኖር እጣ ፋንታቸው ሆኖ ክፍለ ዘመናትን ዘለቀ።
ኩርዶቹ ሀገር የመሆን መብት ሆን ተብሎ እንዲነፈጋቸው ያደረጉት ምእራባውያን አንደኛ የኩርዶች አልበገሬነት በቀጠናው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ እንዳሻቸው ለመጠቀም እንቅፋት ሆኖ ስለታያቸው እንደሆነ ይነገራል። ኩርዶቹ በተደጋጋሚ ነፃነታቸውን ከቅኝ ገዥዎች እጅ ለማስመለስ ያደረጉት አያሌ ደም አፋሳሽ ትግሎቻቸው ጌቶቻቸውን በማስኮረፉ፣ እነ ኢራቅ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ሶሪያ ሀገር እንዲሆኑ ሲፈቀድ እነርሱ ግን ሀገር አልባ ተንከራታች ሕዝብ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል።
ኩርዶችን ሀገር አልባ ያደረገውን ውል በመቃወም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን የጀመረው የሀገርነት ጥያቄ ተሰሚነት ሳያገኝ ወደ 21ኛው ክፍለዘመን ተሸጋግሯል። ዛሬ የኢራቅ ኩርዶች፣ የቱርክ ኩርዶች፣ የኢራን ኩርዶች፣ የሶሪያ ኩርዶች፣ የአርመን ኩርዶች፣ የአዘርባጃን ኩርዶች ተብለው፣ ተቆራርጠው በሚኖሩባቸው በርካታ ሀገራት አናሳ ሕዝብ ተደርገው በተዳከመ አንድነት ተበታትነው ይኖራሉ።
አካባቢውን የግዛታቸውን አካል አድርገው ለረጅም ዘመን ያስተዳደሩት ኦቶማን ኢምፓየር ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከገጠመው ሽንፈት በኋላ ሰፊው ግዛቱ ተከፋፍሎ ብዙ አዳዲስ ሀገራት ተፈጥረው የኩርዶች መሬት ለሀገራት ተሸንሽኖ ከተሰጠ ጀምሮ የኩርዶች ስቆቃ በየሀገራቱ አስከፊ መልክ ያዘ። በኩርዶች ላይ ሀጋራቱ አያሌ በደሎችን ፈፅመዋል። ኩርዶች ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆኑ፣ ባህል ቋንቋቸውን እንዳይከተሉ እና ከሌሎች ጋር እንዲቀየጡ ተገድደዋል። ጅምላ ጭፍጨፋም ደርሶባቸዋል።
የኩርዶች በደል
ይቀጥላል….
(መሠት ቸኮል)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም