ሚሊዮኖችን የመታደግ ዘመቻ

0
188

ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዳይመለሱ፣ መምህራን የተማረ ዜጋ ለማፍራት የሚያደርጉትን ጥረት ማደናቀፍ ግቡ ምንድን ነው? ይህ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የቀጠለ የአማራ ክልል አንገብጋቢ ችግር ሆኖ አሁን ድረስ የዘለቀ መልስ ያጣ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚበልጡ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው መክረማቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ዓመትም ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አሁንም ትምህርት ቤቶቻቸው፣ አስተማሪዎቻቸው፣ ጓደኞቻቸው… እንደናፈቋቸው የትምህርት ዘመኑ ከተጀመረ  ሰባተኛው ወር ተቆጥሯል፡፡ አሁንም  ግን የትምህርት ቤቶችን መከፈት አጥብቀው ይጠባበቃሉ፡፡ ምክንያቱም ታዳጊዎች ከትምህርት ውጪ በመሆናቸው ብቻ የሚያጋጥማቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፤ በተለይ ለሴቶች ያለ ዕድሜ እና የልጅነት ጋብቻ አሳሳቢ  ሆኗልና፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮም የተለየ የትምህርት ክፍለ ጊዜ (ካላንደር) በማዘጋጀት ቀድመው የተመዘገቡትን ከማስተማር ጎን ለጎን የተማሪ ምዝገባ እያከናወነ ይገኛል፡፡ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ጊዜ ድረስ ተማሪዎችን በዘመቻ የመመለስ እንቅስቃሴም ሲያካሂድ ቆይቷል፤ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶችም የተማሪ ምዝገባ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ኤልያስ ወረዳ ዳግም ትምህርት እንዲጀመር ካደረጉ ወረዳዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ በወረዳው በ32 የመጀመሪያ እና በሦስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 25 ሺህ 821 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር፡፡ ዳግም ትምህርት ሲጀመር በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት የቻሉት አንድ ሺህ 515 ተማሪዎች ብቻ  መሆናቸውን የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌዲዮን አስቻለን ጠቅሶ  የወረዳው መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል፡፡ በቀጣይም የተጀመረው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ትምህርት ያልተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ማድረግ ላይ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ የፀጥታ አካላት፣ ማኅበረሰቡ እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት  ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት  መምሪያም ሁሉም ትምህርት ቤቶች ወደ መደበኛ መማር ማስተማር እንዲገቡ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡  በከተማ አስተዳደሩ 119 የትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፤ 112 ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፤ ሰባቱ አሁንም ከመማር ማስተማር ውጪ መሆናቸውን የትምህርት መምሪያ ኃላፊዋ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ “ትውልድን በትምህርት የመታደግ ልዩ የንቅናቄ ዕቅድ” በሚል መሪ ቃል ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት መቋረጥ ምክንያት ከትምህርት ውጪ የሚሆኑ ተማሪዎች በሂደት የትውልድ ክፍተትን የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም ትምህርት እንዲጀመር፣ የተጀመረውም ሳይቆራረጥ እንዲቀጥል በማድረግ ላይ መረባረብ እንደሚገባ ለተወያዮች አስገንዝበዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞንም ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎችን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ትምህርት መምሪያው “ትምህርት ለትውልድ!” በሚል በተዘጋጀ ንቅናቄ ዋና አስተዳዳሪው አራጌ ይመር የዓለም ሃያልነትም ሆነ አሸናፊነት የሚረጋገጠው በትምህርት በመሆኑ ተማሪዎችን  ወደ ትምህርት ገበታ በመመለስ በኩል አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ እና ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲሰፍን ሁሉም አካል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ዋና አስተዳዳሪው  ጥሪ አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያዎች በበኩላቸው  “ትምህርት ለትውልድ!” የንቅናቄ አፈፃፀም ግምገማ አካሂደዋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በድረ ገጹ እንዳጋራው በትምህርት ዓመቱ በዞኑ 896 ሺህ 165 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዕቅድ ተይዟል፡፡

እስካሁን 247 ሺህ 348 ተማሪዎች መመዝገብ መቻላቸውን ያስታወቁት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ በመማር ላይ ያሉት 184 ሺህ 641 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡

አሁንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ እና ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡ 584 አንደኛ እና 18 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ናቸው፡፡ አሁንም ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ለመመለስ የተማሪ ምዝገባ መቀጠሉን  አስታውቀዋል፡፡

እንደ መምሪያ ኃላፊው ገለጻ ቀድሞ የመማር ማስተማር በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ሀገራዊ እና ክልላዊ ፈተናዎች የሚወስዱ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያልተቆራረጠ  የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ፣ የአዳር ጥናት እንዲሁም የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡

በቀጣይ የትምህርት ተቋማት ያሉበትን ደረጃ ማወቅ፣ ግብዓት ማሟላት፣  የትምህርት ጥራት የሚያጎለብቱ ተግባራትን በውጤታማነት ለመተግበር እንደሚሠራም ገልፀዋል።

በንቅናቄ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ የትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ካሳሁን አዳነ  በበኩላቸው በዚህም ወቅት ክልሉ ከነበረበት የትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት ችግር በተጨማሪ የተፈጠረው ግጭት በብዙ የክልሉ አካባቢዎች የትምህርት ሥራውን እንዳስተጓጎለው አንስተዋል። አሁን ላይ በክልሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ተማሪዎች እና መምህራን ከትምህርት እና ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ “በመሆኑም ትምህርት ከሌለ ዘላለም በድህነት ውስጥ እንደምንኖር ተረድተን የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን በማስከፈትና ተማሪዎች እንዲማሩ በማድረግ እንዲሁም ውጤታማ የሆነ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር እና የትምህርት ቤቶችን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል አልሞ መሥራት ይጠበቅብናል” በማለት  አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት የሚመለሱ ተማሪዎች ክልሉ ባስቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ/ካላንደር/ መሠረት መማር ማስተማራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ይዘቶችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ደግሞ  የማካካሽ ትምህርቶች በዋናነት እንደሚሰጥ የትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

አማካሪው እንዳሉት ቅዳሜ የትምህርት ቀን ሆኖ በበርካታ አካባቢዎች እየዋለ ነው፡፡ ተማሪዎችም ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ ወላጆች እና የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትም የሚጀመረው ትምህርት በዘላቂነት እንዲቀጥል ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመጋቢት 8  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here