የቅርሶች ጥገና እየተከናወነ መሆኑ ተጠቆመ

0
124

በሰሜን ወሎ ዞን 45 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የቅርሶች የጥገና ሥራ እና ሙዚየም ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት በመደቡት ከ45 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዲሁም በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የአራት ፍልፍልና የአምስት የዋሻ ውስጥ አብያተ ክርስትያናት እንዲሁም የሦስት ሙዚየም ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡

እስካሁንም የሦስት ፍልፍልና የሁለት ዋሻ ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት ጥገና እንዲሁም የመጠለያና የሁለት ሙዚየም ግንባታ ሥራ መጠናቀቁን አቶ ጥላሁን አመልክተዋል።

ቅርሶችን በመጠገን ሂደት የአካባቢው ሕብረተሰብ በጉልበት፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ከ18 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል። ቀሪው የጥገና ሥራ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ እንደሚጠናቀቅም አመላክተዋል።

በጋዞ ወረዳ የዋሻ ሚካኤል አካባቢ ነዋሪ ቄስ አለልኝ አባቡ በሰጡት አስተያየት “ከአያቶቻችን ያገኘናቸውን ቅርሶች ለልጅ ልጆቻችን የማስተላለፍ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው” ብለዋል።

ነዋሪው ዕድሜ ጠገብ የሆነውን የዋሻ ውስጥ ቤተክርስቲያን ለመጠገን የተሰጠው ትኩረት ሕዝቡ መደሰቱን ጠቅሰው “እኛም በጉልበታችንና በገንዘብ የድርሻችንን እየተወጣን ነው” ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ከአራት ሺህ 200 ሜትር በላይ ከፍታ ያለው የአቡነ ዮሴፍ ተራራ እንዲሁም የቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ሌሎች ብርቅየ እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ መሆኑንም ቡድን መሪው አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል።

በኲር የመጋቢት 8  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here