ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ ሽርሽር ልንወስዳችሁ ነው:: የአንበሶች ከተማ የሚል ትርጉም አላት፤ ከተማ እና ሀገርነቷን አንድ ላይ ይዛለች፤ ይህ ማለት በእንግሊዝኛው ሲቲ ስቴት ብለው እንደሚጠሩት ከተማም ሀገርም ናት- ሀብታሟ እና የፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ተምሳሌቷ ሲንጋፖር::
እንግሊዞች በራሳቸው አጠራር ሲንጋፖር አሏት፤ በማላይ ሕዝቦች አጠራር ሲናፑራ ነው ተብሎ የሚጠራው፤ ትርጉሙም የአንበሶች ከተማ ተብሎ ይፈታል:: ሲንጋፖር ደሴት ናት፤ በዓለማችን ካሉ በሥራ ከተጨናነቁ ደሴቶች አንዷ ናት:: ሥራ ዋነኛው መግባቢያ ነው::
በሲንጋፖር 74 በመቶ የቻይና፣ 13 በመቶ የማሌይ፣ ዘጠኝ በመቶ የህንድ እና ሦስት በመቶ የሌሎች ዝርያ ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ:: ቡድሂዝም፣ ክርስቲያን፣ ኢስላም፣ ታኢይዝም፣ ሂንዱይዝም እምነት ተከታዮች በስፋት አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች ቁጥራቸው ይልቃል::
ፓርላመንታዊ የመንግሥት ሥርዓት የምትከተለው ሲንጋፖር በአሁኑ ጊዜ ፕሬዝደንቷ ታርማን ሻንሙጋራትናም ሲባሉ ጠቅላይ ሚኒሥትሯ ደግሞ ላውረንስ ዎንግ ይሰኛሉ:: ሀገሪቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበረች:: እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ሰኔ 3 ቀን 1959 ነጻነቷን በማወጅ ራስ ገዝ ሆናለች:: እ.አ.አ በ1963 ሲንጋፖርን ጨምሮ አራት ሀገራትን ለማዋሀድ የማሌዢያ ስምምነት የሚባለውን ፈርማ በማሌዢያ ስር ተካተተች፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከህብረቱ ወጥታ ራሷን የቻለች ሀገር ሆናለች::
ሲንጋፖር 735 ስኩየር ኪሎሜትር አካባቢ ትሸፍናለች፤ በቆዳ ስፋቷም በዓለም 176ኛ ደረጃን ይዛለች:: ሲንጋፖር ከሀገራችን ጋር በቆዳ ስፋቷ ስትነጻጸር 1535 ጊዜ ታንሳለች:: ማይ ላይፍ ኤልስዌር የተሰኘ ድረ ገጽ ሲንጋፖርን በቆዳ ስፈቷ ከባሕር ዳር ከተማ ጋር ያስተካክላታል:: በጎርጎሮሳዊያኑ 2024 በተደረገ ግምት የሕዝብ ብዛቷ ከስድስት ሚሊየን በላይ እንደሚሆን ተቀምጧል:: አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷ ከአምስት መቶ ቢሊየን ዶላር በላይ ሲሆን የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ደግሞ 89 ሺህ 370 ነው፤ በዚህ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ ሕዝቦቻቸው የናጠጠ ኑሮ ከሚኖሩ ሀገራት መካከል ተቀምጣለች:: መገበያያ ገንዘቧ የሲንጋፖር ዶላር ይባላል::
ሲንጋፖር እንደ ከተማ ከመቆርቆሯ በፊት የተለያዩ የባሕር ላይ ሥርዓተ መንግሥታት (ታላሶክራሲ የሚባሉ በባሕር ላይ ዋና መቀመጫቸውን ያደረጉ መንግሥታት ነበሩ) የእቃ ማራገፊያ እና ማጠራቀሚያ ቦታ ነበረች:: እ.አ.አ በ1819 ሳንፎርድ ራፍሌስ የተሰኘ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ባለሥልጣን የእንግሊዝ ወደብ አደረጋት:: በ1867 እ.አ.አ ደግሞ በእንግሊዝ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር ሆነች:: እ.አ.አ በ1942 በጃፓን ቁጥጥር ስር ወድቃ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን መሸነፏን ተከትሎ ወደ እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተመለሰች:: ከላይ እንዳነሳነው በ1959 እ.አ.አ ነጻ ወጥታለች::
ሲንጋፖር በትምህርት፣ ጤና፣ የተሻለ አኗኗር (quality of life)፣ ደህንነት፣ መሠረተ ልማት፣ የቤት አገልግሎት ምርጥ ከሚባሉት ሀገራት ትመደባለች፤ ያም ሆኖ ግን ከሌላ ሀገር ለመጡ ሠራተኞች ውድ የምትባል መሆኗን ብሪታኒካ ይጠቁማል:: ሲንጋፖር እና ዙሪክ፣ ጀኔቫን፣ ኒውዮርክን እና ሆንግ ኮንግን በማስከተል የዓለም ውድ ከተሞች መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሲንጋፖራዊያን ረጅም ዓመታት ከሚኖሩ ሕዝቦች ይመደባሉ:: 88 በመቶ የሚሆኑት የራሳቸው ቤት አላቸው፤ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘርግቶላቸዋል፤ የሙስና መጠኑ ዝቅተኛ ነው፣ የሕጻናት እና የእናቶች ሞት እጅግ አነስተኛ ነው፤ ይህ ሆኖ እያለ ሀገሪቷ ካላት አነስተኛ የቆዳ ስፋት አንጻር እጅግ የተፋፈገ የሕዝብ አኗኗር አላት:: ከዓለም ሕዝብ በጣም ተጠጋግቶ የሚኖርባት በመሆን ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች:: ይህም ቢሆን ግን ዘመናዊ የከተማ እቅድ በመተግበሯ አያሌ አረንጓዴ ቦታዎች እና የሕዝብ መዝናኛዎች አሏት::
የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ሲንጋፖር አራት ብሔራዊ ቋንቋዎች አሏት:: እነሱም እንግሊዝኛ፣ ማላይ፣ ማንዳሪን እና ታሚል ናቸው:: በሚገርም ሁኔታ እንግሊዝኛ በስፋት የሚነገር ቋንቋ ነው::
ሲንጋፖር ውብ የሆኑ 63 ደሴቶች በውስጧ አሉዋት:: ሀገሪቷ የመሬት ጥበት ችግሯን ለመፍታት ውሃማ ቦታዎችን ለማድረቅ ተገዳለች፤ በዚህም 580 ስኩየር ኪሎሜትር የሚሆን ቦታ ማግኘት ችላለች:: እኛስ ኢትዮጵያዊያን ምናችን ይሆን የጠበበው?
ሲንጋፖር ከ1967 እ.አ.አ በፊት 95 በመቶ የሚሆነውን የጫካ ሀብቷን በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ አጥታ ነበር:: ከ1967 ዓ.ም በኋላ የሀገሪቱ መንግሥት የጫካ ከተማ የማድረግ እቅድ ይዞ በመምጣት ተግባራዊ አደረገው:: በዚህም መሠረት የሀገሪቱ 10 በመቶ የሚሆነው መሬት ለፓርኮች እና ለአካባቢ ጥበቃ እንዲውል ተደርጓል:: ይህን በመሥራትም ማራኪ፣ ምቹ እና ለጤና ተስማሚ ከተማ መፍጠር ችለዋል::
የትሮፒካል ዝናባማ የአየር ጸባይ ያላት ሲንጋፖር ሞቃታማ ናት:: የሙቀት መጠኗም ከ23 እስከ 32 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል:: ከፍተኛ የዝናብ መጠንም የምታገኝ ሲሆን እንደ ሀገራችን አብዛኛው አካባቢዎች ሁሉ በረዷማ የአየር ጸባይ የላትም::
ቱሪዝም ለሲንጋፖር የጀርባ አጥንቷ ነው:: እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2023 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ሲንጋፖርን ጎብኝቷል፤ ይህም ማለት ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ሁለት እጥፍ ነው:: ከዚህ በመነሳት ሀገሪቱ ምን ያክል ውብ እና ሳቢ መሆኗን ልብ ይሏል:: በ2015 እ.አ.አ ሎንሊ ፕላኔት እና ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ምርጥ የጎብኝዎች መዳረሻ ካሏቸው ሀገራት ውስጥ ስድስተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠዋታል::
የጎብኝዎችን ቀልብ ከሚስቡ መስህቦች መካከል ሜርላየን የተሰኘው የአንበሳ ቅርጽ የሚመስል ሀሳባዊ ግዙፍ ቅርጽ፣ ኢስፓላንዴ የተሰኘው መሀል ከተማ የሚገኝ ባሕላዊ ትይንቶች እና ኪነ ተውኔቶች የሚቀርቡበት ማዕከል፣ ማሪና ቤይ ሳንድስ የተሰኘው ማራኪ ሪዞርት እንዲሁም እንጦጦ ፓርክ ላይ የተገነባውን መሳይ የከተማ ጫካ ተጠቃሽ ናቸው::
ሲንጋፖር በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የጎብኝ መዳረሻዎቿ የተጥለቀለቀች ናት:: ወንዞች፣ ኮረብታማ ቦታዎች፣ ጫካዎች፣ ፓርኮች፣ መካነ አራዊቶች፣ የባሕር ዳርቻዎች እና ሌሎች በጎብኝዎች ተመራጭ ቦታዎች አሏት:: የጠንካራ የሥራ ባሕል ባለቤት፣ ሀብታም፣ ለኑሮ ምቹ እና በጎብኝዎች ተመራጭ የሆነችውን ሲንጋፖር እንዲህ አስቃኘናችሁ፤ ሰላም!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም