ትኩረት ለኮሪደር ልማት

0
127

ሐገራት ለማህበረሰባቸው ሁለንተናዊ ደህንነት እና ጤናማ ህይወት   በየወቅቱ ልዩ ልዩ ተግባራትን ያከናዉናሉ። ከተግባራቱ መካከልም የኮሪደር ልማት አንዱና ዋነኛው ነው። የኮሪደር ልማት ሥራዎች በተለይም ህዝብ በብዛት በአንድ አካባቢ ሰፍሮ በሚኖርባቸዉ ከተሞች  ዉስጥ ነዋሪዉን ንጹህ አየር ማግኘት   ያስችለዉ ዘንድ አካባቢዉን ጽዱ እንዲሆኑ በማድረግ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አበርክቶው ከፍተኛ እንደሆነ በልማቱ ረጅም ዓመታት የሠሩ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡

ሲንጋፖር በኮሪደር ልማት ሥራዎች ለብዙዎች በተሞክሮነት የምትወሰድ ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቷ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በሕንጻ ዲዛይን እና ደረጃ፣ በጽዱነት እና ውበትን ለገቢ ምንጭነት በመጠቀም ረገድ ለብዙ ሀገራት በተሞክሮነት የምትነሳ ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያም በቅርቡ የኮሪደር ልማትን በተወሰኑ ከተሞች ላይ መተግበር ጀምራለች። ይህ የኮሪደር ልማትም አተገባበሩ ታላሚ ካደረገባቸዉ አላማዎች መካከል  የከተሞች ዕድገትን  ለማቀላጠፍ እና የከተሞችን ውበት ለማስጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ምንጭ  ለማድረግ ፣ ለጎብኝዎች ምቹ እና ማራኪ እይታ እንዲሰጥ ለማድረግ፣የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳለጥ እዲሁም ለበርካታ ዜጎች  የሥራ ዕድል መፍጠሪያ  በማድረግ  እየሠራችበት ትገኛለች።

የኮሪደር ልማት የከተሞችን ደረጃ እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን አቀናጅቶ ለመጠቀም እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ የአረንጓዴ ልማት ሽፋንን ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድልን  ለማስፋት ፣ የሥራ ባህል እና የትብብር መንፈስን ለማዳበር  በእጅጉ እንደሚያግዝ በዘርፉ ካለፉ ሃገራት ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል።

ከሲንጋፖር ልምዱ ተቀምር በአዲስ አበባ ተከናውኖ መልካም ውጤት እየተመዘገበበት ያለው የኮሪደር ልማት ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ክልሎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው፡፡ የአማራ ክልልም የኮሪደር ልማትን በሰባት ከተሞች እያከናወነ ይገኛል፡፡

በክልሉ ሰባት ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ በሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው፡፡ በክልሉ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች በሥራ ፈላጊነት ተመዝግበው እንደሚገኙ የክልሉ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል፡፡ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የኮሪደር ልማትም ለ37 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ተመላክቷል፡፡

የባሕር ዳር ከተማም ለኮሪደር ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥታለች፡፡ በከተማዋ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ሲሆን ይህ ተግባርም ተፈጥሮ ለከተማዋ የሰጠቻትን ውበት ፍንትው አድርጐ ለማውጣት፣ ጽዱ እና ለዜጎቿ የተመቸች፣ ጎብኝዎቿንም በተሟላ መሠረተ ልማት ለመቀበል እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም በእጅጉ ያግዛል።

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ነባር  ሆኑ የአረንጓዴ ልማት ሥፍራዎች  የሕዝብ መዝናኛ አረንጓዴ ቦታዎች በስፋት እየተከናወኑበት ነዉ።

የኮሪደር ልማቱ የተቀናጀ መሠረተ ልማትን አካቶ እየተሠራም ይገኛል፡፡ የመብራት፣ የውኃ እና የቴሌ መስመር ዝርጋታዎች ከመሬት በታች ተቀብረው እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡ ይህም የከተሞችን ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባለፈ በየጊዜው ለተለያየ አላማ ተብሎ በሚከናወን ቁፋሮ የሚቆራረጥን የኀይል አቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ክልሉ ያለውን እምቅ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሐብት ይበልጥ ለጎብኝዎች በሚያስተዋውቅ አግባብ እየሠራ  መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከተሞች በጎብኝዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ እና የረጅም ጊዜ መቆያ ሆነው ገቢያቸውን በእጥፍ እንዲያሳድጉ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ  ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡

በባህርዳር ከተማ እየተሰራ ያለዉ የኮሪደር ስራ ጠቀሜታዉ በርካታ ቢሆንም በተለይ ደግሞ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ መለያ የሆነው የጣና ሃይቅን ፍንትው አድርጎ ከማሳየቱ ባሻገር ውበቱን እዲሁም ከጣና የሚመጣውን ንጹህ እና ነፋሻ አየር ነዋሪዉ እና ጎብኝዉ እንዲያገጘ አስችሎታል።

በባህርዳር በተለይም በጣና ዙሪያ እተከናወነ ያለው የኮሪደር ስራ  ሰው ወደ ጣና ለመሄድ እንዲያስብ ሳይሆን የሃይቁ ውበት እና ገጽታው ሰውን  ስቦ እንዲወስደው ተደርጎ በመሰራት ላይ በመሆኑ የነዋሪውን የጎብኝውን ቀልብ የሳበ ተግባር ሆናል፡፡

በጣና ሃይቅ ዙሪያ የተሰራው ስራም በሁሉም የማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ተዝናኖት የሚያገኝበት የመዝናኛ ስፍራም ሆኖ እየተሠራ በመሆኑ ለነዋሪዎች እፎይታን እና ተስፋን ያሳደረ ተግባር ነው።

በመሆኑም አሁን በኮሪደር ልማቱ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚያስገኙትን በርካታ ጥቅሞች ግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት ልማቱ በታለመለት ደረጃ እንዲፋጠን እና ከተጠናቀቀ በኋላም አገልግሎቱ በተቀመጠለት አግባብ እንዲሆን  መከታተል፣ መቆጣጠር እና ለአላስፈላጊ ተግባራት እንዳይውል በማድረግ የየድርሻችን ተግባር እንወጣ።

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here