ታዳጊዎች በታላቁ መድረክ

0
125

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በክለቦች ውድድር ታሪክ ቀዳሚው የተጫዋቾች ህልም ነው፤ ደጋፊዎችም ማየት የሚፈልጉት የፉክክር መድረክ ነው። ውድድሩ ባለተሰጥኦ ታዳጊ ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚያሳዩበት እና አሻራቸውን የሚያስቀምጡበት ነው።

ባለፉት ዓመታት ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የውስጥ ሊግ ውድድሮችን ማሸነፍ ህልማቸው እንደነበር ሲናገሩ ይደመጣሉ። አሁን ግን ይህን ውድድር ማሸነፍ እና በዚህ መድረክ መሰለፍ ህልማቸው ሆኗል። ገና በወጣትነታቸው በዚህ መድረክ ተሰልፈው ግብ ካስቆጠሩ ደግሞ የእግር ኳስ ህይወታቸው ወደ ሌላ ምዕራፍ ይሸጋገራል። መድረኩ እንደመስፈንጠሪያ ያገለግላቸዋልና ነው።

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ከሊዮኔል ሜሲ ምትሀተኛ ብቃት እስከ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግብ አነፍናፊነት በታላቁ መድረክ አንጸባርቀው ዐይተናል። ከ18 ዓመት በታች የሆኑ በርካታ ድንቅ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች ዘንድሮም ማራኪ እንቅስቃሴ በማድረግ ግቦችን እያስቆጠሩ ቡድናቸውን እያገዙ ነው።

ውድድሩ እ.አ.አ 1992 ነው የጀመረው። በዚህ በታላቁ መድረክ ሊዮኔል ሜሲ፣ ማሪዮ ባሎተሊ እና ራውልን የመሳሰሉ ኮከቦች በመድረኩ ታሪክ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆነው ጨርሰዋል። በበርካታ ሻምፒዮንስ ሊግ ምሽቶች ብዙዎች ምትሀታዊ ብቃታቸውን አሳይተዋል፤ የተሳካላቸው ደግሞ ግቦችን በማስቆጠር ይበልጥ የመጪው ዘመናቸውን አሳምረውበታል። የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በአዲስ ቅርጽ እየተከናወነ ይገኛል። ባለትልቁን ጆሮ ዋንጫ ለማንሳት የሚደረገው ትንቅንቅም እጅግ አጓጊ ሆኗል። ታዲያ ልብን በሚያሞቀው እና ትንፋሽን በሚያስውጠው ፉክክር የአርሴናሉ አጥቂ ኤታን ንዋንሪ እና የባርሴሎናው የፊት መስመር ተሰላፊ ላሚን ያማል ዘንድሮ በመድረኩ ክስተት በመሆን ግብ አስቆጥረው የመጪው ዘመን ኮከቦች መሆናቸውን አሳይተዋል። እነዚህ ታዳጊዎች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ግባቸውን ነው ያስቆጠሩት።

የላሜሲያ አካዳሚ ፍሬ የሆነው ባለተሰጥኦው ታዳጊ አሁን ላይ በእርሱ እድሜ ካሉት ቀዳሚ ባለክህሎት ነው። ያማል ኳስ በማቀበል ክህሎቱ፣ የግብ እድሎችን የመፍጠር ብቃቱ እጅን በአፍ ያስጭናል። ተጫዋቹ የካታለኑ ክለብ ወሳኝ ተጫዋች ነው። በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ድንቅ አቋም ማሳየቱም የሚታወስ ነው። ስፔናዊውን የ17 ዓመቱ አጥቂ በርካታ የእግር ኳስ ተንታኞች ከላሜሲያ ፍሬ ከሆነው ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ ጋር ያመሳስሉታል።

ላሚን ያማል ግን በኔይማር ጁኔር  አጨዋወት ተጽእኖ ማደጉን ይናገራል። አሁን ላይ 180 ሚሊዬን ዩሮ የዝውውር ዋጋ እንደሚገመት የሚነገርለት የፊት መስመር ተጫዋቹ በ17 ዓመት ከሁለት ወራት እድሜው በታላቁ መድረክ ግብ ያስቆጠረ ሁለተኛው በእድሜ ትንሽ ተጫዋች ሆኗል። ያማል በመስከረም ወር በሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ጨዋታ ባርሴሎና ከሞናኮ ባደረገው መርሀግብር በመድረኩ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። በወቅቱም 17 ዓመት ከ68 ቀናት እድሜ ላይ እንደነበር መረጃው ያስነብባል። በያዝነው መጋቢት ወር በካምፕኑ ባርሴሎና ቤኔፊካን ሦስት ለአንድ ባሸነፈበት መርሀግብርም ላሚን ያማል ሦስተኛዋን ግብ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ውድድሩ በአዲስ መልኩ ከተጀመረበት 1992/93 እ.አ.አ ጀምሮ ንዋንሪ 14ኛው በመድረኩ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ነው። የአርሴናል አካዳሚ ፍሬ ውጤት የሆነው ንዋንሪ በዚህ ዓመት የመድፈኞች ዋናው ቡድን በጉዳት በታመሰበት ጊዜ ጥሩ ግልጋሎት የሰጠ ተጫዋች ነው። በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑ  አሁን ላይ ለሚኬል አርቴታው ቡድን አስፈላጊ ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል።

ንዋንሪ ለዋናው ቡድን መሰለፍ የጀመረ በ15 ዓመት ከ181 ቀናት እድሜው መሆኑን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ይህም በትንሽ እድሜው በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የተሰለፈ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው። ዘንድሮ ደግሞ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በወርሃ ጥር አርሴናል በኤምሬትስ ስቴዲየም ጂሮናን ባስተናገደበት ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል። ታዲያ እንግሊዛዊው ወጣት በ17 ዓመት ከ314 ቀናት እድሜ በታላቁ መድረክ ግብ ካስቆጠሩ ተጫዋቾች መካከል ስሙን በክብር መዝገብ ማስፈር ችሏል።

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች አንሱ ፋቲ ነው። የ22 ዓመቱ አጥቂ በበርካታ የእግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ ብዙ የተወደሰ ባለተሰጥኦ ነው። በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጊኒ ቢሳው የተወለደው አንሱ ፋቲ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር ሲነጻጸር እንደነበረም አይዘነጋም። ፋቲ በተደጋጋሚ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በባርሴሎና ቤት ቦታውን ማስጠበቅ አልቻለም።

ታዳጊው ባለተሰጥኦ ከ2023 እ.አ.አ ጀምሮ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በብራይተን አልቢዮን ቤት እየተጫወተ ይገኛል። እ.አ.አ በ2019 ፋቲ በካታለኑ ክለብ ቤት የዋናውን ቡድን ሰብሮ በገባ በመጀመሪያው ዓመት በ24 ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል። በዚሁ ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ባርሴሎና ወደ ጣሊያን ተጉዞ በሳንሴሮ ኢንተርሚላንን ሁለት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠራት አንሱ ፋቲ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ወጣቱ አጥቂ በወቅቱ በ17 ዓመቱ ከ40 ቀናት እድሜ ላይ ይገኝ ነበር። ታዲያ ፋቲ በታላቁ መድረክ በትንሽ እድሜው ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን ስሙ በክብረ መዝገብ ሰፍሯል። ፋቲ 18 ዓመት ሳይሞላው በመድረኩ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር መረጃ ያመለክታል። ሌላኛው በሻምፒዮንስ ሊጉ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ላሚን ያማል ነው።

በአውሮፓ ሻምፒዩንስ ሊግ ግብ በማስቆጠር ሦስተኛው በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ጆርጅ ኤሌኒኬና ነው። ናይጀሪያዊው የ18 ዓመቱ አጥቂ ከ2024 እ.አ.አ ጀምሮ በፈረንሳዩ ክለብ ሞናኮ እየተጫወተ ነው። ፈጣን እና ጠንካራ እንደሆነ ብዙዎች የመሰክሩለታል። ተጫዋቹ ወደ ፈረንሳይ ከማቅናቱ በፊት በቤልጂየሙ ክለብ አንተወርፕ በነበረበት ወቅት የመጀመሪያውን የሻምፒዮንስ ሊግ ግቡን ሲያስቆጥር በ17 ዓመት ከሦስት ወር እድሜ ላይ ነበር። በወቅቱ ባለሜዳውን ክለብ አንተወርፕን  አሸነፊ ያደረገች ግብ ኤሌኒኬና ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

ኖርዋዊው የጨዋታ አቀጣጣይ አንቶኒዮ ኑሳ በቡንደስ ሊጋ ከሚጫወቱ ባለክህሎት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። የ19 ዓመቱ ተጫዋች በ2024 ነው ከቤልጂየሙ ክለብ ብሩዥ የቡንደስ ሊጋውን ክለብ አርቢ ላይብዚንግን የተቀላቀለው። እ.አ.አ በ2022 መስከረም ወር የቀድሞ ክለቡ ክለብ ብሩዥ ፖርቶን አራት ለባዶ ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰለፈበት ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል።

ኑሳ ያኔ 17 ዓመት ከ149 ቀናት እድሜ ላይ ነበር። ተስፈኛው አጥቂ በሻምፒዮንስ ሊግ ግብ ያስቆጠረ አራተኛው በእድሜ ትንሽ ተጫዋች ነው። በኖርዌ እግር ኳስ ታሪክ ደግሞ ሁለተኛው በእድሜ ትንሽ ተጫዋች አድርጎታል። ጋናዊው የቀድሞው አጥቂ ፒተር አፎሪ ኳዬ ከ1997 እስከ 2003 እ.አ.አ በግሪኩ ክለብ ኦሎምፒያኮስ ቤት ተጫውቶ አሳልፏል። በክለቡ ውስጥ በቆየባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥም 80 ጨዋታዎችን አከናውኖ 24 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል።

በወርሃ ጥቅምት 1997 እ.አ.አ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ኦሎምፒያኮስ ከሜዳው ውጪ በኖርዌው ክለብ ሮዘንቦርግ አምስት ለአንድ ሲሸነፍ ለግሪኩ ክለብ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ፒተር አፎሪ ኳዬ ነበር። ጋናዊው የቀድሞ ተጫዋች በመድረኩ የመጀመሪያ ግቡን ሲያስቆጥር 17 ዓመት ከ194 ቀናት እድሜ ላይ እንደነበር ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

የሪያል ማድሪዱ አማካይ ጁዲ በሊንግሀም፣ ሁለቱ የባርሴሎና ኮከቦች ማርክ ጉይ እና ፔድሪ፣ የማንቸስተር ሲቲው ተከላካይ ሪኮ ሊዊስ፣ የፓርሴን ዥርመኑ አማካይ ዋረን ዛየር ኤምሪን  የመሳሰሉት ወጣት ኮከቦች 18 ዓመት ሳይሞላቸው በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋች መሆናቸውን የአውሮፓ እግር ኳስ መረጃ ያስነብባል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here