የሕጻናት እንጥል ማስቆረጥ እና ጉዳቱ

0
502

እንጥል ማስቆረጥ ሀገራችን ውስጥ ከሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው:: ድርጊቱ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከተፈረጀ ዘመናት ቢያስቆጥርም አሁንም በከተማም ሆነ በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍሎች እየተፈጸመ ይገኛል:: እኛም በጤና አምዳችን እንጥል ማስቆረጥ  የሚያስከትለውን የጤና ጉዳትና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከዘርፉ የጤና ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል::

ባለሙያዉ ዶክተር ሞላልኝ ይስማው ይባላሉ፤ በጥበበ ግዮን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ  ሆስፒታል ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው:: ባለሙያዉ እንዳብራሩት እንጥል ከአፋችን ጣሪያ  በተለምዶ ላንቃ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ  በአፍ እና በጉሮሮ መካከል ተንጠልጥሎ ይገኛል::

በምራቅ እጢዎች የሚሸፈነው እንጥል እንደ አብዛኛው የአፋችን ግድግዳ ሁሉ ምራቅ ያመነጫል:: የሚመነጨው ምራቅ በንግግር ወቅት የአፍ መድረቅ እንዳይኖር፣  በንግግር ጊዜ ድምጽ ከፍ ብሎ እንዲሰማ እና የተለያየ ድምጸት እንዲኖር ያደርጋል::

እንደ ዶክተር ሞላልኝ ይስማው ገለጻ እንጥል በአመጋገብ (በምንመገብበት) ጊዜ ከአፍ ጀርባ ባለው የጉሮሮ ክፍል እና በአፍ መካከል እንደ መዝጊያ በር ሆኖም ያገለግላል:: ይህ የላመ እና የጣመ ምግብ ወደ ጉሮሯችን በሚገባበት ጊዜ ደግሞ እንጥል ከላይ የተጠቀሱትን  ተግባራት ትቶ በአፋችን እና በአፍንጫችን ጀርባ ባለው ጉሮሮ  መካከል እንደ መጋረጃ ሁኖ ምግቡ ወደ አፍንጫ እንዳይመለስ ያደርጋል::

እንጥል ይወርዳል ወይ? ስንልም ላነሳንላቸው ጥያቄ ዶክተር ሞላልኝ የሚከተለውን ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ ከጉሮሮ ክፍል ጋር ተያይዞ ላንቃ አለ:: የጉሮሯችን  ግድግዳ በጎን እና በጎን አለ:: በእነዚህ ውስጥ ቶንሲሎች አሉ:: መቆጣት ወይም ኢንፌክሽን ሲኖር እነዚህ የአፍ ክፍሎች ሊታመሙ ይችላሉ:: በዚህም እንጥል አብሮ ሊታመም ይችላል:: ለእንጥል መቆጣትም ዋነኛው መንስኤ ኢንፌክሽን ነው::

ቫይረሱ ወይም ባክቴሪያው እንጥልን ብቻ ለይቶ አያጠቃም:: በተለይ ሕጻናት ላይ በጉንፋን እና በሌሎች ቫይረሶች ምክንያት በሚከሰቱ በሽታዎች ከጉሮሮ ጀርባ ያለው ክፍል ሲታመም ከእንጥል  ጋር አፈጣጠራቸው የተያያዘ በመሆኑ አብሮ በቫይረሱ የመጠቃት አጋጣሚ አለ:: ከጉሮሮ እና ከቶንሲል መቆጣት ጋር ተያይዞ እንጥልም አብሮ ይቆጣል::  በዚህ ጊዜ እንጥል ይቀላል፤ ይወፍራል:: ወደ ታችም ሊረዝም ይችላል:: የቁመቱ መርዘምም ወረደ ሊያስብለው ይችላል እንጂ እንጥል በራሱ አይወርድም::

እንጥል ሲረዝም ወይም በኢንፌክሽን ሲጠቃ ታዲያ የሕመም ስሜት ሊሰማ ይችላል፤ የጉሮሮ ሕመም፣ የጉሮሮ መከርከር፣ ምግብ ለመብላት እና  ለመዋጥ መቸገር፣ አንገት አካባቢ ያሉ የንፊፊቶች( ፍርንትት) እብጠት እንጥል በኢንፌክሽን ሲጠቃ ሊከሰቱ የሚችሉ የሕመም ስሜቶች ናቸው:: እነዚህ ምልክቶች በእንጥል መቆጣት ብቻ የሚታዩ ምልክቶች ናቸው:: ከዚህ ባለፈ እንጥል ሲረዝም የምላስን  መሠረት ስለሚነካው ምቾት አይሰጥም:: ወደ ታች በደንብ ከረዘመ ደግሞ ሳል ማሳል ይጀምራል፤ ከፍተኛ ትኩሳትም ይከሰታል::

እንደ ዶክተር ሞላልኝ ማብራሪያ የእንጥል መታመምን የሚለየው ሐኪም ነው:: በሙያው የተመረቀ ከአንገት በላይ ሐኪም ቢያየው ደግሞ በጣም የተሻለ ነው:: ምክንያቱም ለችግሩ ቀረቤታ ስላለው:: የሕመሙን ምልዕክቶች በመለየት ተገቢውን ሕክምና ህጻናት ያገኛሉ::

በማኅበረሰቡ ውስጥ እንጥል ይወርዳል፤ ከወረደ ደግሞ መታፈን ስለሚኖር ሞት ያስከትላል የሚል ግንዛቤ  አለ::  ይህን በተመለከተም ለዶክተር ሞላልኝ ሐሳብ እንዲሰጡን ጠይቀናቸውል፤ ሐሳቡ የተሳሳተ እና ሳይንስም የማይደግፈው እንደሆነ ያብራሩት ባለሙያው እብጠት ወይም ኢንፌክሽን ሲከሰት ደግሞ (ከላይ የተሰጠውን ማብራሪያ መሠረት በማድረግ) ከተገኘ ከአንገት በላይ ስፔሻሊስት ሐኪም ካልሆነ ደግሞ ማንኛውንም የጤና ባለሙያ ማማከር ተገቢ ነው ብለዋል::

ኢንፌክሽን እንዳለ ከተረጋገጠ ታዲያ ቤት ውስጥ ሕጻናት በቂ ፈሳሽ እንዲወስዱ፣ ያበጠውን ስለሚቀንስ ለብ ያለ ውኃ እንዲጠጡ  እና ሕመም ሲኖር ማስታገሻ መድኃኒት እንዲወስዱ ማድረግ ይመከራል:: በሀኪም የታዘዘ የሕመም ማስታገሻ ለውጥ ከሌለው ደግሞ ለሐኪም ማሳየት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል::

እንጥል ማስቆረጥ አሁንም ድረስ የሚስተዋል ተግባር ነው፤ ይህ ተግባር ግን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተብሎ የተፈረጀ መሆኑን ነው ባለሙያው ያነሱት:: ከበርካታ ዓመታት በፊት የኅብረተሰብ የጤና ችግር ተብሎ ስለመሰየሙም ነው በአስረጂነት ያቀረቡት::

ድርጊቱን ለማስቆም ታዲያ ሙከራዎች ቢደረጉም ማስቆም አልተቻለም:: ድርጊቱ ግን ወዲያው የሚከሰትና ዘላቂ ጉዳትን ያስከትላል:: ከዚህ አለፍ ሲልም ሕይወትን ሊነጥቅ ይችላል:: እንጥል ወዲያው እንደተቆረጠ በደም መፍሰስ ምክንያት ሕጻናትን ለህልፈት ይዳርጋል::

ባለሙያው እንዳስገነዘቡት እንጥል በባሕላዊ መንገድ ሲቆረጥ አብረው የደም ስሮች ስለሚቆረጡ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ይኖራል:: ባሕላዊ ሐኪሞች ደሙን ለማስቆም የሚያስችል መድኃኒት ስለማይኖራቸው ህጻናት የከፋ ችግር ይገጥማቸዋል::

በባሕላዊ የሕክምና ቦታዎች እንደምንታዘበው ባሕላዊ ሐኪሞች ወረፋ አስይዘው የበርካታ ህጸናትን እንጥል ይቆርጣሉ:: ብዙዎችም ደም ይፈሳቸዋል፤ ደም መፍሰሱ ካልቆመ ደግሞ ወደ ሐኪም ቤት ሳይደርሱ ሊሞቱ ይችላሉ::  እንጥሉ ሲቆረጥ ሙሉ በሙሉ ከስር ጀምሮ ሊቆረጥ ይችላል:: ይህ ደግሞ ሌላው ለተራዘመ ጊዜ የሚከሰተው የጤና ጉዳት እንደሆነ ነው ዶክተር ሞላልኝ ያነሱት:: በዚህ ጊዜ የላንቃ መከፈት ይፈጠራል:: ላንቃ ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ ድምፅ ላይ ጉዳት ይደርሳል:: የድምጽ ጥራት ችግር ያጋጥማል:: ምግብ ወደ አፍንጫ ሊመለስ ይችላል::

ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ ታዲያ እንጥል ማስቆረጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች በመዘንጋት ይባስ ብሎም ስለ አስፈላጊነቱ የሚከራከሩ በርካቶች እንደሆኑ ነው የተናሩት፤ “በጣም የሚያሳዝነው ተምረዋል የሚባሉት ድርጊቱን ሲደግፉ ይስተዋላል:: እኔ በልጅነቴ እንጥሌን ተቆርጫለሁ፤ ግን ምንም አልሆንኩም የሚሉ አሉ:: መታወቅ ያለበት እነሱ ላይ ችግር አልደረሰም ማለት ሌሎች ላይም አይደርስም ማለት አይደለም” ሲሉ ነው ያብራሩት::

ይህንን ሐሳብም በሥራ የገጠማቸውን አሳዛኝ ክስተት ዋቢ በማድረግ ነው የገለጹት፤ “አንድ ጊዜ አንዲት ጨቅላ ሕጻን የመተንፈሻ ክፍል ላይ ችግር ተፈጥሮባት ወደ እኛ አምጥተዋት ነበር:: ባደረግንላት ምርመራ የሕጻኗ እንጥል በሚቆረጥበት ጊዜ የተቆረጠችው የእንጥሏ ጫፍ ከቆራጩ ዕጅ አምልጣ ወደ ጉሮሮዋ ገብታ ነበር:: ለማውጣት ሞከርን፤ ሙከራችን ግን አልተሳካም:: ሕጻኗም ሕይወቷ አለፈ! ይህ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው!”

ዶክተር ሞላልኝ  በመጨረሻም የሚከተለው መልዕክት “ይድረስልኝ!” ብለዋል፤ “ሕብረተሰቡ መገንዘብ ያለበት እንጥልን ማስቆረጥ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን ነው:: እንጥል አይወርድም፤ በኢንፌክሽን የሚያብጥ ወይም የሚወርድ ከሆነም በማስቆረጥ ሳይሆን በመድኃኒት ይድናል:: እንጥል ላይ ችግር ከተፈጠረ ወዲያው   በሕክምና   ባለሙያ መታየት ይገባል::

“እንጥል ማስቆረጥ ሕይዎትን የሚያሳጣ ተግባር ነው:: እንጥል ለሕክምና ባለሙያ እንኳ በጣም አስቸጋሪ ቦታ ላይ ነው ያለው:: ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል:: እንጥላቸውን ያስቆረጡ ሰዎች ‘እኔ ምንም አልሆንኩም’ በሚል በድርጊቱ ተሳታፊ መሆን የለባቸውም:: እነሱ ላይ ባይደርስ ሌሎች ላይ የመድረሱ አጋጣሚ ሰፊ ነው:: ስለዚህ ይህን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ከመፈጸም እና ከማስፈጸም መቆጠብ ይገባል!” ።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here