ሃሳብን ወደ ሀብት

0
145

“በአማራ  ክልል   ሰሜን  ጎጃም ዞን  መርዓዊ ከተማ  በሚገኝ  የጤና ተቋም   በአጋጣሚ በተገኘንበት    ወቅት  ረጅም  ሰልፍ   ተመለከትን፡፡

ሰልፉ ምንድን ነው? በማለት ስንጠይቅ የአልትራሳውንድ ሕክምና ለማግኘት የመጡ ታካሚዎች እንደሆኑ ተነገረን፡፡ የታካሚዎች መብዛት ደግሞ ለአልትራሳውንድ  ምርመራ የሚያገለግለው ቅባት /ጄል/   ስለሌለ እና ከቅርብ አካባቢ እስኪመጣ እየጠበቁ መሆኑ  ተነገረን፡፡

ወዲያውኑ ችግሩ እንዴት ይፈታ ይሆን? የሚል  ጉጉት በእኔ እና በጓደኞቼ አደረብን” በማለት ያጫወተን  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት የኢንቫይሮመንታል ሳይንስ ተማሪው ናሁ አስተርዐየ ነው:: የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ የሆኑት ታሪኩ ሻረው እና ተመቸው ደሴ ችግሩን ከናሁ ጋር ከተመለከቱ  በኋላ በአልትራሳውንድ ምርመራ ወቅት ገላ ላይ የሚቀባው ጄል ከምን ይሠራል? በሀገር ውስጥ ስለማይመረት ከየት ይመጣል?…. ለሚሉት ጥያቄዎቻቸው  ዝርዝር መረጃዎችን ራዲዮሎጂ (የጤና ባለሙያ) በማናገር እና የተለያዩ ጥናቶችን በመመልከት ለማዘጋጀት ወሰኑ፡፡

ወጣቶቹ ሃሳባቸውንም ወደ ዩኒቨርሲቲው የሃሳብ ማበልፀጊያ ተቋም በማቅረብ ተቀባይነት አገኙ፡፡ ሥራቸውንም ከዘርፉ አማካሪ ጋር የካቲት ወር 2016 ዓ.ም ጀመሩ:: “ችግር ብልሀትን ይወልዳል” እንደሚባለው ወጣቶቹ በመርዓዊ የጤና ተቋም የተመለከቱትን እና የሰሙትን መነሻ በማድረግ  በዩኒቨርሲቲ በቀሰሙት ዕውቀት በመታገዝ እና ባለሙያ በማማከር ለአልትራሳውንድ ምርመራ የሚያስፈልገውን ቅባት /ጄል/ ማዘጋጀት እንደቻሉ ተናግረዋል::

ናሁ እና ጓደኞቹን  ያገኘናቸው የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መጋቢት 7ቀን 2017 ዓ.ም  በተዘጋጀ የቴክኖሎጂ  /ስታርት አፕ / ውድድር ላይ ነው፡፡ በዕለቱም ወጣቶቹ በጤና ተቋማት ያዩትን የረጅም ሰልፍ ምክንያት ጠይቀው ላገኙት  ምላሽ የጄል እጥረት ወዲያውኑ መፍትሔ ለመስጠት ያዘጋጁትን የአልትራሳውንድ መመርመሪያ ቅባት ለውድድር አቅርበው ነበር፡፡

በውጤቱም  ማሸነፍ ከቻሉት ተወዳዳሪ ወጣቶች መካከል አንደኛ ለመሆን  በቁ:: ናሁ እና ጓደኞቹ እንደነገሩን በወቅቱ ለውድድር የቀረቡት 192 ሃሳቦች ነበሩ፤ ከነዛ ውስጥ  30 የሚሆኑት ሥራቸውን ሠርተው ለመጨረሻው የፍፃሜ  ማጣሪያ ውድድር መቅረብ ከቻሉት መካከል የነ ናሁ አንዱ ነበር፡፡ በውድድሩ ሥራቸው  የተለያዩ ምርመራዎችን አልፎ በክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ይሁንታን በማግኘቱም በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ  እና በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታሎች ጥራቱ በሙከራ የተረጋገጠ ሥራ ይዘው መቅረባቸው  ለአሸናፊነት  አብቅቷቸዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ ሥራቸው በኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይሁንታን ካገኘ ወደ ምርት ገብቶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ምርት መሆን እንደሚችል በዕለቱ ተጠቁሟል::

ናሁ በዕውቀት የሚያበቁ የሥልጠና ማዕከላት እና  ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ  ውድድሮች ካሉ ወጣቶች ተወዳድረው ለለውጥ እንዲተጉ ተነሳሽነትን ስለሚፈጥሩ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጠይቋል::

በባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ የሆኑት እና በፈጠራ ውድድሩ  የሕትመት ቀለም /ፕሪንት ባይንደር ፕሮዳክሽን/  የሠሩት የሦስተኛ ደረጃ አሸናፊዎች ከሆኑት አንዷ ዕጹብድንቅ ቦሩ በኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት  ክፍል  የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ወጣቷ እንደነገረችን  በቀለም ፋብሪካዎች ግብዓት በመሥራት ነው ማሸነፍ የቻሉት፡፡

ለፈጠራው መነሻ ሃሳብ የሆናቸው አራተኛ ዓመት እያሉ ለተግባር ልምምድ የተመደቡበት የቀለም ፋብሪካ  ቀለም ለማምረት የሚጠቀምበት ግብዓት ከውጭ ብቻ የሚመጣ በመሆኑ የሚጠይቀው   የውጭ ምንዛሬ እና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የሚያልፈው   የተንዛዛ  ሂደት  ምርት ሲቋረጥ መመልከታቸው ነው፡፡

ዕጹብድንቅ እንደምትለው በፋብሪካው ቀለም በፍጥነት እና በብዛት እንዳይመረት  የተመለከቱት የግብዓት እጥረት  ወደ ምርምሩ እና ፈጠራው እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

በቀጣይም በርካታ ሙከራዎችን አጠናቀው ለምርት ዝግጁ በማድረጋቸው ችግሩ  እንደሚፈታ አረጋግጣለች፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንኪዩቤሽንና ስታርት አፕ ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ ካሳ የዩኒቨርሲቲው ዋና ዓላማ ከክልሉ እና ከሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ ካገኘ ሃሳባቸውን  ማሳደግ እና ወደ ሃብት መቀየር ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሀሳብ ባለቤቶችንም  ሃብት ካላቸው ጋር በማስተሳሰር የገቢ ምንጭ  እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል::በውድድሩ ከዩኒቨርሲቲው ወጣቶች በተጨማሪ አንድ የ11ኛ ክፍል ተማሪ መካተቱን ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ የፈጠራ ሥራን ከባሕር ዳር ውጭ በዘጌ፣ ዳንግላ፣ ባሕር ዳር ዙሪያ… ለመጀመርና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ባሉበት ስቲም ሴንተር ለመክፈት መታሰቡን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ለሙከራ በስድስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ሥልጠና መሰጠቱን አንስተዋል:: በሽልማቱ ስነ ስርዓት የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ  ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ሥራ መከናወኑን አድንቀዋል፡፡ “እንደ ሀገር ብዙ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ የምናደርገው ቁስን  ብቻ ነው፤  የወጣቶችን ሃሳብ ፋይናንስ የሚያደርግ ሥርዓት አልነበረም፡፡  በዚህም ወጣቶች በዐይን የሚታይ እና በሰነድ የሚረጋገጥ  አዳዲስ ሃሳቦቻቸው ወደ ተግባር ገብተው የሀገርን ዕድገት በማፋጠን በኩል ያላቸው አስተዋጽኦ እና ድርሻ አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን ላይ ወደ ቴክኖሎጂ መግባት አስገዳጅ  ነው፤ ወደ ቴክኖሎጂ መግባት ካልተቻለ ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት አይቻልም፤ ግብርናም ያለ ፈጠራ፣ ያለ ዲጅታላይዜሽን ሊቀጥል አይችልም፡፡ የትምህርት እና የጤና ተቋማትም በቴክኖሎጂ መደገፍ አለባቸው” በማለት  የወጣቶችን የፈጠራ ሥራ አበረታተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወጣቶችን በማሠልጠን ላደረገው አስተዋጽኦም  ርእሰ መስተዳድሩ ምሥጋና አቅርበዋል። ዘርፉን በቋሚነት ለመምራትም የክልሉ መንግሥት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እንዲደራጅ ማድረጉን አንስተዋል።

የዕውቀት ተቋማት፣ መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ተጣምረው የሚሠሩበትን አሠራር መዘርጋት እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እንደ ክልል ሞዴል  ማዕከል መገንባት እንደሚገባ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስገንዝበዋል፤ ለእነዚህ ተግባራትም  የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል:: የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒሥትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ቴክኖሎጂን ለማልማት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ ኑሮን ለማሻሻል፣ በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ውድድሩ ከክልሎች እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሠራ  ለወጣቶቹ የመማሪያ ተሞክሮ፣ የፈጠራ ባሕል ማሳደጊያ፣ ሃሳባቸውን ወደ አዋጭ ንግዶች ለመቀየር የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ማስገኘትን ዓላማ ያዳረገ ስለመሆኑም ተጠቁሟል:: ወጣቶች ተሰጥዖቸውን እንዲያዳብሩ፣ ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ የስታርት አፕ ሥነ ምሕዳር ለመፍጠር የተጀመሩት ውድድሮች እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል::

በውድድሩ  ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለያዙ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡  አሸናፊዎቹም በቀጣይ ወደ ሥራ ለመግባት መነሻ ካፒታል ሊሆናቸው እና የሥራ ተነሳሽነት ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ነው በማደማደሚያነት የተገለፀው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here