ሱዳን እንዴት ሰነበተች?

0
176

በሱዳን  ያለው ሁኔታ  በጣም  አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሁለት ዓመታት ሊቆጠሩ  ጥቂት ሳምንታት የቀሩት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከዐሥር ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል:: በሁለቱ ዋና ተቀናቃኝ የሱዳን ወታደራዊ አዛዦች መካከል በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ሚያዚያ 15 ቀን 2023 የተጀመረው ጦርነት እየተባባሰ ቀጥሏል::

ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ማለትም በሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ በአብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ መሪ በጀኔራል ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) መካከል  እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሀገሪቱን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ነው:: ግጭቱ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ኢትዮጵን ጨምሮ ወደ ጐረቤት ሀገራት  በመሰደድ የመከራ ኑሮን እየገፉ ነው፡፡ በሀገሪቱ የምግብ፣ የውኃ፣ የመድኃኒት እና የሌሎች መሠረታዊ አስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት አጋጥሟል፡፡ ሀገሪቱ የዓለማችንን ትልቁን የውስጥ መፈናቀል እያስተናገደች ነው:: ይህ ጦርነት እንዲቆም በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም ሊሳኩ አልቻሉም፡፡ ከክልላዊ ድርጅቶች እስከ ዓለም አቀፍ አደራዳሪ ተቋማት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁንና ሙከራቸው መና ቀርቷል::

ጦርነቱ ዓለም አቀፉን የጦርነት ሕግ በመጣስ በተደጋጋሚ ንፁሃንን ዒላማ በማድረግ እና በሰብዓዊ (በረዴት) ሠራተኞች ላይ ጥቃት እያደረሰ ቀጥሏል፡፡ የመብት ረገጣ ሪፖርቶችም በየጊዜው እየወጡበት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል::

ጦርነቱ በሱዳን የነበረውን የፖለቲካ ክፍተት በማባባስ ወደ ሲቪል አገዛዝ የሚደረገውን ሽግግር አደናቅፏል፡፡ እ.አ.አ በ2019 የረዥም ጊዜ አምባገነን መሪ የነበሩት ኦማር ሃሰን አል በሽር ከሥልጣን ሲወገዱ ሱዳን ወደ ሲቪል አገዛዝ ልትመለስ ነው በሚል ትልቅ ተስፋ ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን የሱዳናዊያን ተስፋ ሁለት ዓመታትን መሻገር አልቻለም፤ ከሁለት ዓመት  በኋላ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተስፋ የተጣለበትን የሽግግር ሲቪል መንግሥት አፈረሰው፡፡ ቀጥሎም አሁን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት አገርሽቶ ሀገሪቱ መታመሷን፣ ሱዳናዊያንም የመከራ ኑሮን እንዲገፉ በማድረግ ቀጥሏል።

ጦርነቱ  መሰረተ  ልማቶችን በማፈራረሱ  እና በንፁህ መጠጥ ውኃ  እጥረት  ምከንያት  እንደ  ኮሌራ  እና ኩፍኝ ያሉ ወረርሺኞች እንዲያገረሹ አድርጓል::

ጦርነቱ  የሱዳንን  ምጣኔ  ሀብት ክፉኛ ጐድቷል፡፡ ንግድ፣ ግብርና እና ሌሎች ቁልፍ ሴክተሮችን ባዶ አስቀርቷል፡፡ እንዲሁም የግብርና ምርትን እና የአቅርቦት ሰንሰለትን  በማስተጓጐሉ ሀገሪቱ ሰፊ የምግብ ዋሳትና እጦት እና የረሃብ አደጋን እንድትጋፈጥ አድርጓታል:: ከአሁኑ ጦርነት በፊት ሱዳን እ.አ.አ በ2003 የዳርፉር ቀውስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁከት እና መፈናቀል ስትታመስ ቆይታለች፡፡ በሌላ በኩል የዛሬን አያደርገውና ሱዳን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ነበረች፡፡ በዚህም በአፍካሪ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ስደተኛ ሕዝብ የምታስናግድ ሀገር ሆና ነበር፡፡

የምትቀበላቸው ስደተኞችም አብዛኛዎቹ ከደቡብ ሱዳን እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከኢትዮጵያ (በዋናነት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት) የተሰደዱ ነበሩ:: አሁን ግን እንኳን ስደተኛ ልታስተናግድ ዜጐቿ ርስ በርስ ጦርነቱ ምክንያት የሚገቡበት አጥተው ተጨንቀው ይገኛሉ፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነው (ሱዳን ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ልብ ይሏል) የሱዳን ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል:: ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት ከተጋለጡት 25 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሱዳናዊያን መካከል ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮኖች በድንገተኛ (የከፋ) ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው::

የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ከሰሞኑ እንዳስጠነቀቁት ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች (አብዛኛዎቹ ህፃናት) በጅምላ ጭካኔ ውስጥ፣ በረሃብ እና በገዳይ በሽታዎች መካከል ለመኖር ይገደዳሉ:: ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ተገድለዋል፡፡ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

ሦስት ነጥብ አምስቱ ሚሊዮኑ ደግሞ በጐረቤት ሀገራት ተጠልለዋል:: የሱዳን ለም የእርሻ  መሬቶች  በባሩድ  ንዳድ  አመድ ሆነዋል፡፡ የተረፉትም ባለው የጦርነት ሁኔታ ሊታረሱ አልቻሉም:: ዩኒሴፍ ህጻናት ላይ ግድያ እና ጾታዊ ጥቃት ከመድረሱ በተጨማሪ የታጠቁ ቡድኖች ውስጥ በግዳጅ ለውጊያ እየተመለመሉ መሆኑን አስታውቋል:: በህፃናቱ ዙሪያ ከባድ እና አስደንጋጭ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡

እ.አ.አ ከሰኔ እስከ ታኅሳስ 2024 ብቻ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ከባድ የህፃናት መብት ጥሰቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ግድያ ወይም አካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን የዩኒሴፍ ሪፖርት ያመላክታል:: አስፀያፊ የአስገድዶ መድፈር ምስክርነቶች ለዩኒሴፍ እየደረሱት መሆኑን ነው ካትሪን ረስል የሚናገሩት፡፡ በግምትም 12 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ሴቶች እና ወንዶች በአሁኑ ጊዜ ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ ሆነዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 80 በመቶ ጨምሯል:: በተያያዘም የሰብዓዊ ድርጅቶች እርዳታን ለማድረስ ከባድ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የተነናገሩት፡፡ የረዴት ሰራተኞች የመጠቃት እና የመገደል ዕድላቸውም እየጨመረ ነው:: እንዲሁም በተያዘው የአውሮፓዊያን 2025 ዘመን ከ770 ሺህ በላይ ህፃናት ለከፋ የምግብ  አጥረት  ይጋለጣሉ  ተብሎ  ይጠበቃል፡፡

አፋጣኝ የነፍስ አድን ሥራ ካልተሠራ ከእነዚህ ልጆች መካከል ብዙዎቹ ሊሞቱ ይችላሉ ሲሉ ራስል አበክረው አስጠንቅቀዋል:: ራስል የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያልተቋረጠ የሰብዓዊ አገልግሎት በተለይም ቁልፍ በሆኑ የድንበር ማቋረጫዎች እንዲደርስ ጫና እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ ለተፋላሚ ወገኖችም የሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል:: ለስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ተጋላጭ ለሆኑ ህፃናት የሕይወት አድን እርዳታ ለመስጠት ዩኒሴፍ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ነው የጠቆሙት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቀውሱ ከሱዳን ባለፈ ቀጣናውን እንደሚያውክ ነው ያሳሰቡት:: ሱዳን ለአየር ንብረት ለውጥ  አደጋዎች ተጋላጭ መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ ሱዳን እንኳንም ዘንቦብሽ ሆነና ጦርነቱ ሲጨመር በሕዝቦቿ የሚደርሰውን ጉዳት በእጅጉ እያባባሰው ነው::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መሪ ሃምዳን ዳጋሎ ኬንያን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ከኬንያ  የሚገቡ ምርቶችን ከልክላለች። የሱዳን መንግሥት በናይሮቢ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎችን (RSF) ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ካስተናገዱ በኋላ ከኬንያ የሚገቡ ምርቶችን በሙሉ  ማገዷን ነው ያስታወቀችው::

በሌላ በኩል በሱዳን የሰብዓዊ ቀውስ  ላይ የሚያተኩር  ከፍተኛ ደረጃ ያለው ኮንፈረንስ እ.አ.አ ሚያዚያ 15 ቀን 2025 በእንግሊዝ፣ በአውሮፓ ኅብረት፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ የአውሮፓ ኅብረት  ማስታወቁን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here