ግዙፉ ስቴዲየም መቼ ይከፈታል?

0
108

አንድ ስታዲየም ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የካፍን ዝቅተኛውን መስፈርት ማሟላት ይኖርበታል። ከመስፈርቶች መካከል በምሽት ጨዋታዎችን ማከናወን የሚችል ባውዛ መብራት፣ ደረጃውን የጠበቀ  ሰው ሠራሽ የሳር ንጣፍ ሜዳ፣ የቪ አይ ፒ እና የቪቪ አይ ፒ (የክብር እንግዶች እና የባለስልጣናት) መቀመጫዎች ፣ የተጫዋቾች ፣ የዳኞች እና የታዛቢዎች  የመልበሻ ክፍል እንዲሁም የሚዲያ ክፍል ሊኖረው እንደሚገባ የካፍ ኦላየን መረጃ   ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ አንድም የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ  ብሄራዊ ቡድኖች  ከሀገር ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፤ እያከናወኑም ነው። በተለይ ዋሊያዎቹ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን ለማድረግ ከሀገር ውጪ ተሰደዋል። ይህ ደግሞ በብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም ባለፈ ኢትዮጵያን ለወጪ እየዳረጋት ነው። አሁን ግን ይህን ችግር የሚቀርፍ ዜና የፊታችን ሰኔ ወር መጨረሻ እንደምንሰማ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ሰውነት ከአሚኮ በኵር የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ስታዲየም በ2002 ዓ.ም የመጀመሪያው ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በተጀመረ በአራት ዓመታት ውስጥ  የመላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎችን አስተናግዷል። ከ2015 ጀምሮ ግን የካፍን መስፍርት ለማሟላት እና ለአገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ለመገንባት እየተከናወኑ ናቸው።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየም 52 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። የመቀመጫ ወንበሮች እየተገጠሙ ሲሆን 47 ሺህ አምስት መቶ ወንበሮችም እስካሁን ተገጥመዋል ። በቅርቡም ቀሪዎቹ አራት ሺህ አምስት መቶ ወንበሮች የሚገጠሙ ይሆናል። ጣሪያ ሳይለብስ ለምን ወንበሮች ተገጠሙ? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምስክር ሰውነት የተገጠሙት እነዚህ ወንበሮች ሙቀት እና ቅዝቃዜን መቋቋም የሚችሉ በመሆናቸው ቶሎ እንደማይበላሹ ተናግረዋል። እሳት እንኳ ቢነሳ ቶሎ መቀጣጠል በማይችል ቁሶች መሠራታቸውንም ነግረውናል። ለፕሬዝዴንሺያል( ቪቪ አይፒ) ክፍሎች በአጠቃላይ 30 ወንበሮች በቅርቡ ይገጠማሉ። ጥይት የማይበሳው መስታወትም የሚገጠምለት ሲሆን የራሱ ካፍቴሪያ እና ሪስቶራንትም  ይኖረዋል ተብሏል። የቪ አይ ፒ ቦታው ደግሞ መቶ ሰዎች መያዝ ይችላል ነው የተባለው።

ዋናው ስቴዲየም በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የእግር ኳስ ሜዳ ሳር ለብሷል፤ የማስተካከል ሥራውም እየተከናወነ እንደሆነ ተገልጿል። ሜዳውን ሳር የማልበስ ሥራ የካፍ እና የፊፋ ፈቃድ ባለው የፈረንሳዩ ግሪጎሪ ድርጅት እየተከናወነ ነው። ከዚህ በፊት ዝናብ ሲዘንብ ሜዳው ላይ የሚጠራቀመው ውሃ ወደ ውስጥ ይሰርግ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ወደ ውጪ እንዲፈስ ተደርጎ ተሰርቷል፡፡ በዝናብ ምክንያት ሜዳ ውስጥ የሚያርፈው ውሃ በአስር ሰከንድ ውስጥ ወደ ውጪ ይፈሳል ተብሏል። ይህም በዝናብ ምክንያትም ጨዋታዎች እንደማይቆራረጡ ነው የተነገረው።

ሁለቱም የመለማመጃ ሜዳዎች የጥራት ደረጃቸው ከዋናው ሜዳ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን አቶ ምስክር ያስረዳሉ። አንደኛው የመለማመጃ ሜዳ ተመሳሳይ ሳር የለበሰ ሲሆን ሁለተኛው የመለማመጃ ሜዳም በቅርቡ ሳር ይለብሳል። እነዚህ ሜዳዎች መለማመጃ ብቻ ሳይሆኑ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዲችሉ ተደርገው ነው እየተዘጋጁ ያሉት። እያንዳንዳቸው ሦስት ሺህ 500 ወንበሮች አሏቸው፤ መልበሻ ክፍል እና መታጠቢያ ክፍልም ተዘጋጅቶላቸዋል። ዋናው መጫዎቻ ሜዳ በሳምንት አራት ቀን ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን በቀሪ ቀናት ጨዋታዎች በመለማመጃ ሜዳዎች የሚደረጉ ይሆናል። የካፍ ገምጋሚ ቡድን እነዚህን መለማመጃ ሜዳዎችን ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሜዳ አድርጋችሁ አስመዝግቡ ብሎ በሰጠው አስተያየትም በካፍ የሚመዘግቡ ይሆናል ብለዋል- አቶ ምስክር።

በግራ እና በቀኝ ሁለት ግዙፍ ስክሪኖች የሚገጠሙ ሲሆን የእያንዳንዳቸው ስፋት መቶ ካሬ ሜትር ይጠጋል። እነዚህ ስክሪኖች ከቻይና ተገዝተው ሀገር ውስጥ ገብተዋል፤ ስክሪኖችን ለመገጣጠም የሚያስችሉ ሥራዎችም ተጀምረዋል- እንደ አቶ ምስክር ገለፃ። በምሽት ጨዋታዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ 20 ባውዛ መብራቶች የሚተከሉ ይሆናል። በካፍ መስፈርት  መሰረት ባውዛ መብራቱ የሚረጨው የብርሃን መጠን  (Lux)  ከአንድ ሺህ 200 እስከ አንድ ሺህ 600 መሆን ይኖርበታል። በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ግን የሚተከለው የባውዛ መብራት አንድ ሺህ 600 ላክስ (Lux) እንደሆነ ነው የስቴዲየሙ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሚያስረዱት። ይህም በዓለም ላይ ያሉት ታላላቅ ስቴዲየሞች የሚጠቀሙበት ደረጃውን የጠበቀ ባውዛ ነው። ከዋናው ሜዳ በተጨማሪ ለሁለቱ መለማመጃ ሜዳዎችም ተመሳሳይ ስምንት ባውዛ መብራቶች የሚገጠሙላቸው ሲሆን ሥራውም በቅርብ ቀናት ውስጥ  ይጠናቀቃል።

በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየም አራት የመልበሻ ክፍሎች ያሉ ሲሆን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የማጠናቀቅ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የቀድሞው የካፍ ስቴዲየሞች ገምጋሚ አህመድ ሳዳት በቅርቡ ስቴዲየሙን በጎበኙበት ወቅት እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች መደሰታቸውን አቶ ምስክር ያስታውሳሉ። ታዲያ የቪ አይፒ እና ቪቪ አይፒ ክፍሎች መውጫ እና መግቢያ ራሳቸውን ችሎ እንዲዘጋጅላቸው አስተያየት ሰጥተው ሄደዋል፤ በአስተያየቱ መሰረትም ሥራዎች ተከናውነዋል። በጨዋታ ወቅት ተጋጣሚ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ እና ሲወጡ መገናኘት ስለሌለባቸው የተለያየ መግቢያ እና መውጫም ተዘጋጅቶላቸዋል።

ከየትኛውም የዓለም ማዕዘን ጨዋታዎችን በቀጥታ ማስተላለፍ ለሚፈልጉ የሚዲያ ባለሙያዎች በአጠቃላይ 120 የሚዲያ ክፍሎች ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ለአራት የተለያዩ ቋንቋዎች በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ የሚያስችል ክፍሎች እንዳሉት አቶ ምስክር ተናግረዋል። ለቪ አይፒ፣ ለቪቪ አይፒ ፣ለሚዲያ ባለሙያዎች እና ለመሳሰሉት መኪና ማቆሚያ  ደረጃውን በጠበቀ አስፋልት ተሰርቶ ተጠናቋል።

የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ሁለገብ ስቴዲየም ከእግር ኳስ በተጨማሪ 21 ስፖርቶችንም ማስተናገድ ይችላል። ከቤት ውጪ ስፖርቶች ለአብነት ውኃ ዋና፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊ ቦል እና እጅ ኳስን የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህን  ሜዳዎች የማጽዳት ሥራም እየተሠራ ሲሆን ለውኃ ዋና ውድድር የሚያገለግለው የመዋኛ ገንዳ እንደገና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል። ለቤት ውስጥ ስፖርቶች የሚውሉ ማዘወተሪያ ስፍራዎችም ተዘጋጅተዋል፤ የሚቀሩ ሥራዎችም በቅርቡ የሚጠናቀቁ ይሆናል- እንደ ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ።

ዓለም አቀፍ ስቴዲየሙ ግቢ ውስጥ 16 ሔክታር የሚሆን የአረንጓዴ ቦታ አለው። ይህ ዓለም አቀፍ ሁለገብ ስቴዲየም ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ሁለት ዓይነት አገልግሎት ይኖረዋል። የመጀመሪያው የስፖርት ማዘወተሪያ አገልግሎት ሲሆን ሌላው የመዝናኛ አገልግሎት ነው። የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራው የካፍ መመዘኛን ለማሟላት ሥራው በጥድፊያ እየተከናወነ ይገኛል። ሥራውም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የደረሰ ሲሆን አሁን ላይ የማጠናቀቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን  እኔም በቦታው ተገኝቼ ታዝቤያለሁ።

ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስቴዲየምን የሚያስተዳድር ማዕከል ተቋቁሟል። ተጠሪነቱም ለአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ነው። ዓለም አቀፍ ሁለገብ ስቴዲየሙ ገቢ እያመነጨ ሕዝብ ሊጠቀምባቸው የሚችሉባቸው ዕድሎችን ያመቻቻል። ግቢው ውስጥ ካፍቴሪያዎች፣ ሱቆች እና ለቲያትር፣ ለኮንሰርት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ቦታም ተዘጋጅቷል። ሕዝብ ከሚጠቀምባቸው እና ገቢ ከሚያመነጩ ማዕከሎች መካከል አንዱ ጅምናዚየም ነው።

ጅምናዚየሙ በከፊል ቁሶች የተሟሉለት ሲሆን አሁን ላይም በጨረታ ተከራይቷል። በቅርቡ ለማህበረሰቡ እና ስፖርተኞች አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ቀሪ ቁሶች ይሟሉለታል ነው የተባለው። ለአምስት ካፌ እና ሬስቶራንቶችንም ሥራ ለማስጀመር ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ይገኛል። ለስፖርት ትጥቅ ሱቆች፣ ለውበት መጠበቂያ ሳሎኖች፣ ለቢሮዎች እና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ 80 ሱቆች ይኖሩታል። በዚህ ዓመት ግን  24 ሱቆች ብቻ ተዘጋጅተው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።

በዚህ ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ሁሉም ሥራ ተጠናቆ ስቴዲየሙ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተብሏል። ከዚያ በኋላ የሚቀር ሥራ ጣሪያ የማልበስ ሥራ ሲሆን ጣሪያውን ለማልበስም አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ባለሙያዎች መናገራቸውን የስቴዲየሙ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ ነግረውናል። ጣሪያው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ይህን ሥራ ለማከናወን ከወዲሁ ለመንግስት እና ሌሎች የእርዳት ድርጅቶች ጥያቄ ቀርቧል። ገንዘቡ ከተገኘ ሥራው በአንድ ዓመት ተከናውኖ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ባለሙያዎች መግለጻቸውን አቶ ምስክር ተናግረዋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here