እንቆቅልሹ የሜሲ ጠባቂ

0
105

እግር ኳስ ተመልካች ከሆኑ ወይም በተለያየ አጋጣሚ ሊዮኔል ሜሲን ከተመለከቱት ከኋላው ወይም ከጎኑ ሰውነቱ ደልደል ያለ፣ ራሰ በራ ኮስታራ ሰው ሲጓዝ ዐይታችሁ ይሆናል። እንደተመለከታችሁትም ይህ ሰው ማነው? የሚል ጥያቄ በአዕምሯችሁ ተመላልሶ ይሆናል። ሰውዬውን እናስተዋውቃችሁ፤ ያሲን ቼኮ ይባላል፤ የአርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ የግል ጠባቂ ነው።

እ.አ.አ ህዳር 22 ቀን 2023 ብራዚል እና አርጀንቲና በማራካና ስቴዲየም ጨዋታቸውን ሲያከናውኑ ለአርጀንቲናዊው ጥበበኛ የብሄራዊ ቡድን አጋሩ ሮድሪጎ ዲፓውል ነበር ጥበቃ ያደረገለት። የአትሌቲኮ ማድሪዱ ተጫዋች በወቅቱ የብራዚል ፖሊስ ለስምንት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ልዩ ጥበቃ ባለማድረጉ ነበር ዲፓውል እንደ ግል ጠባቂ ያገለገለው። በዚሁ ዓመት ሊዮኔል ሜሲ የፈረንሳዩን ሀብታም ክለብ በመልቀቅ ወደ ሜጀር ሊግ ሶከር በማቅናት ኢንተር ማያሚን ከተቀላቀለ በኋላ ለደህንነቱ በመስጋት የግል ጠባቂ ቀጥሯል። ይህ የግል ጠባቂው በክለቡ ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቤካም አማካኝነት የመጣ መሆኑን ሜል ስፖርት አመልክቷል።

ያሲን ቼኮ ሊዮኔል ሜሲን ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ባለው የእለት ከእለት የህይወት እንቅስቃሴው ይጠብቀዋል። በተጨማሪም ለባለቤቱ አንቶኔላ ሩኩዞ እና ለሦስት ልጆችም ጥበቃ ያደርጋል። በጥበቃ ሥራውም በየወሩ 250 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይከፈለዋል። በዓመት ከሦስት ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ ያገኛል። ለመሆኑ ያሲን ቼኮ ማነው? በርካታ የስፖርት መገናኛ አውታሮች ስለ እርሱ ማወቅ ቢፈልጉም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልቻሉም። ስለ እርሱ የሚነበብ  የተጻፈ ታሪክም የለም፤ የቀድሞ ማንነቱን የሚገልጽ አንድም ፎቶ አለመገኘቱም ብዙዎችን አስገርሟል። በማኅበራዊ የትስስር ገጾቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እየሠራ ከሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ውጪ እርሱን የሚገልጹ ሌሎች መረጃዎችን አያጋራም። ህይወቱ ድብቅ ነው፤ ቃለ መጠይቅ እንኳ ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆኑ የአውሮፓ እና የአሜሪካ የስፖርት የመገናኛ አውታሮች እርሱን ለማናገር የሰማይ ያህል ርቋቸዋል። ይሁን እንጂ ዘ አትሌቲክ፣ ሜል ስፖርት፣ ጎል ዶትኮም፣ ዘ ሰንን የመሳሰሉ የእንግሊዝ ታላላቅ ጋዜጦች ስለ ያሲን ቼኮ የተለያዩ መረጃዎች አግኝተናል በማለት ይፋ አድርገዋል፡፡

ያሲን ቼኮ ከሞሮኳዊ አባቱ እና ከፈረንሳያዊቷ እናቱ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት መወለዱን መረጃዎች አመልክተዋል። በእስራኤል እና በሩሲያ የተለያዩ ወታደራዊ ሰልጠናዎችን ወስዷል። ካራቲ፣ ኩንጉፉ፣ ቲኳንዶ፣ ሪሲሊንግ እና ቡጢ ስፖርትን በቻይና፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሰልጥኗል።  አርባ ስምንት የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር ይችላል፤ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ቻይንኛ፣ ጣሊያንኛ እንዲሁም የፖርቹጊዝ እና የአርጀንቲና ቋንቋዎችንም አቀላጥፎ እንደሚናገር መረጃዎች አስነብበዋል። ሲጓዝ ፈጣን ነው፤ ሊዮኔል ሜሲን ለመጠበቅ  360 ዲግሪ በመዞር ከብርሃን የፈጠነ እንቅስቃሴ ያደርጋል።

ሥራውን የሚያከብር፣ ትሁት እና ለሥራው የታመነ ጠንካራ ሰው ነው። ወደ ሜሲ የሚቀርብ የትኛውንም ሰው ካሰበበት ቦታ ሳይደርስ እንደ ማግኔት በሚስበው እጁ  ጎትቶ ከዓላማው ያስናክለዋል። ያሲን  የኢንተር ማያሚ የአክሲዮን ባለድርሻ በሆነው ዴቪድ ቤካም አማካኝነት ከሜሲ ጋር እንደተገናኘ  መረጃዎች አስነብበዋል።  በአውሮፓ ምድር የግል ጠባቂ ያልነበረው ሜሲ በአሜሪካ ለምን ጠባቂ አስፈለገው? የበርካቶች ጥያቄ ነው። በአሜሪካ የደህንነቱ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ  ጥበቃ እንዳስፈለገው መረጃው ያሳያል። እናም የክለቡ ባለቤቶች ምንም ዐይነት ችግር ከመፈጠሩ በፊት  ታላቁ የእግር ኳስ ሰው የግል ጠባቂ እንዲኖረው አድርገዋል።

ያሲን ቼኮ ይህንን ሥራ የሚያከናውነው ብቻውን ሳይሆን በእርሱ ስር ከሚገኙ 50 የሥራ ባልደረብቹ ጋር ነው። ከሜዳው መስመር ላይ በመቆም የሜሲን እያንዳንዷን ሩጫ እና እንቅስቃሴ በንቃት ይከታተላል። የትኛውም ደጋፊ እና ተመልካች ታላቁን እግር ኳስ ተጫዋች እንዳይቀርቡት በፈርጣማ ክንዶቹ ይከላከላል። ብዙዎችም “በጨዋታ ወቅት ሜዳ ውስጥ መግባት ስለማይፈቀድ እንጂ ሜሲ በሮጠበት ሁሉ ተከትሎት ይሮጥ ነበር” በማለት ይቀልዳሉ። የትኛውም ሊዮኔል ሜሲን ማግኘት የሚፈልግ ሰው አስፈላጊው ማጣራት ከተደረገበት በኋላ ነው የሚያገኘው። አሁን ላይ የኢንተር ማያሚ ደጋፊዎች ከሊዮኔል ሜሲ እኩል ያሲን ቼኮን ያውቁታል፤ ሜዳ ውስጥም እርሱን በማሞገስ ይዘምሩለታል።

ቼኮ የአሜሪካ የቀድሞ የባህር ኃይል ሲል  አባል እንደነበር ጎል ዶት ኮም አስነብቧል። እንደ ዘ ሰን መረጃ  ደግሞ በኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነት ወቅት ተሳትፏል። ያሲን ቼኮ ምንም እንኳ የሜሲን ያህል ዝና ባይኖረውም በአሜሪካ ባህር ኃይል ልዩ ኮማንዶ ሆኖ በማገልገል የገዘፈ ስም እንዳለው ሜል ስፖርትም አስነብቧል።

ከውትድርናው ዓለም ከተገለለ በኋላ ፊቱን ወደ ድብልቅ ማርሻል አርት ስፖርት በማዞር 12 ውድድሮችን አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥ በስምንቱ ያሽነፈው በዝረራ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.አ.አ በ2021 በጉዳት እና በግል ምክንያት ከስፖርቱ ተገልሏል። ከዚህ በኋላ ነበር ያሲን ወደ ሆሊውድ መንደር በመዝለቅ የዝነኛ ከያኒያን የግል ጠባቂ ሆኖ ሥራውን የጀመረው። የሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ፣ የስሌና ጎሜዝ እና የኦውን ዊልሰን የግል ጠባቂ ሆኖ መሥራቱን የሜል ስፖርት መረጃ ያሳያል። እንዲሁም ፕሪንስ ሀሪ እና ሜጋን ማርክል በአንድ ወቅት በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ በተገኙበት ወቅት ጥበቃ ካደረጉላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ያሲን ቼኮ ነበር።

ታዋቂው የእንግሊዙ ጋዜጣ ዘ አትሌቲክ ግን ታይላንድ ውስጥ የሚገኘውን ጓደኛውን ሊዊስ አጉኤር ኤሊያስን በማነጋገር ያሲን የአሜሪካ ባህር ኃይል አባል እንዳልነበረ አስነብቧል፡፡ ስሙ በየትኛውም የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የመረጃ ቋት ውስጥ የለም። ስለቼኮ ግለ ታሪክ አውቃለሁ የሚል ሰው አለመገኝቱንም መረጃው ይገልጻል፡፡  የአሜሪካ ባህር ኃይል ልዩ ኮማንዶ ሲል (በባሕር፣ በአየር እና በየብስ) ልዩ ተልዕኮ የሚፈጽሙ ወታደሮች  ናቸው፡፡ በምድራችን ጠንካራ የሚባሉ ሰዎች ሲሆኑ ያሰቡትን ለመከወን ምንም የሚሳናቸው ነገር የለም። የትኛውም የአየር ፀባይ እና መልካም ምድራዊ አቀማመጥ አይበግራቸውም። በቁጥርም ሁለት ሺህ 500 እንደሆኑ መረጃው ያሳያል።

ከአሜሪካ ባሕር ኃይል ከመቶው አንዱ ሲል ነው። ታዲያ ዘ አትሌቲክ ከአሜሪካ ባሕር ኃይል ተቋም እና የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ ናቸው ከተባሉት አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ያሲን ቼኮ የዚህ ግዙፍ ተቋም አባል እንዳልነበረ ያስረዳል። እንዲሁም በፈረንሳይ  በቆየባቸው አምስት ዓመታት የፈረንሳይ ልዩ ኮማንዶ እንደነበረ የሚወራውም ሀሰት ነው በማለት ያረጋግጣል። ያም ሆነ ይህ ግን ሜሲ በአስተማማኝ እጅ ነው ያለው። በያሲን መጠበቁ ሙሉ ትኩረቱን ጨዋታ ላይ በማድረግ ኢንተር ማያሚን በታሰበው ልክ ወደ ሌላ ምዕራፍ ለማሸጋገር አስችሎታል። የሜጀር ሊግ ሶከር ውድድር እንዲነቃቃም አድርጓል። ክለቡ ኢንተር ማያሚ ደግሞ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ እንዲያነሳ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ዝነኞች፣ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች የግል ጠባቂ እንዳላቸው ይታወቃል። ታዲያ ጥቂት የማይባሉ የግል ጠባቂዎች የሚጠብቋቸውን ሰዎች ገመና በማጋለጥ እና ትንኮሳ በመፈጸም ራሳቸው የደህንነት ስጋት ሲሆኑ መመልከት እንግዳ አይደለም። አለፍ ሲልም በግል ጠባቂዎቻቸው እጅ ሲገደሉ ማየት የተለመደ ነው። ታዲያ የግል ጠባቂዎች የግል ስብዕና በዝነኞች ወይም በሚጠብቋቸው ሰዎች ህይወት ላይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሊዮኔል ሜሲ የግል ጠባቂ ያሲን ቼኮ  ልምድ ብዙ ያስተምራል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here