ራሳችንን እንሁን!

0
117

በዓለም ላይ የሰው ልጅ እኩልነት በተግባር የተበሰረበት የአስተሳሰብ ለውጥ እና ሌላ መደብ የተሰጣቸው ጭቁን እና የነጭ ግፍ ሰለባ ሰዎች የነፃነት ተስፋ ችቦ የተለኮሰበት ብሎም የተንቦገቦገበት  የየካቲት ወር በተለይም ለመላው ጥቁር ሁሉ ልዩ ነው። የቀደሙት እናት አባቶቻችን ኢትዮጵያውያን የፈፀሙት ገድል ደግሞ ለዚህ መነሻ ነው።

የጥቁሮች ታሪካዊ ወር የካቲትን ማሰብ ጥቁሮች ለዓለም ያበረከቱትን አስተዋፅኦ፣ የጥቁሮችን የመብት ትግል ምንነት ለሌሎች ለማስተማር  እንደነ እምዬ ምኒልክ ፣ አፄ ሀይለ ስላሴ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ሮዛ ፓርክስ፣ ማልኮም ኤክስ እና ሃርየት ተምብማን እና ሌሎችም በርካታ  የጥቁሮች መብት ተከራካሪዎች ያደረጉትን የነጻነት ትግል ማሰብ እንደሆነ ይታመናል።

በየሀገራቱ ያለውን ሥርዓታዊ ዘረኝነት ጎላ አድርጎ ለማሳየት እና ሁሉም የሰው ዘር ፍትሕን እና እኩልነትን እንዲጎናጸፍ ያስቻለው ወርሀ የካቲት እውነትም ልዩ ነው። በተለይም ለኢትዮጵያውያን ትላንት፣ ነገ እና አሁናዊ ማንነት የተከፈለው ዋጋ ከምንም በላይ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ለየት የሚያደርጋት በታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የዘመን ቀመር እና ሌሎችም የራሷ የሆኑ መገለጫዎች አሏት። ይሄ እንግዲህ 129 ዓመታትን ወደ ኋላ ስንመለስ እና ነጭ የደነገጠበትን፣ ጥቁር አንገቱን ያቀናበትን የዓድዋ ድልን ስናስታውስ መልሱን እናገኛዋለን።

ከዚህ መነሻነት ታዲያ የታሪክ፣ ቋንቋ፣እምነት ባህል እና እሴት መበልፀግ ማደግ እና በዓለም አደባባይ ተፅዕኖ መፍጠር ለአንድ ሀገር የሉዓላዊነት እና ስልጣኔ ግስጋሴ ፅኑ መሰረት እንደሆኑ ይታመናል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ድልና ኩራታችንም ጭምር ነው፡፡ በሌላ አተያይ እነዚህን እና ያልጠቀስናቸውን ሀብቶቻችንን በተለይም በአግባቡ ጠብቀን ስንይዝ እና መጠቀም ሲቻል በረከቱ ብዙ ነው።

ለዚህ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ስራ በቁርጠኝነት መስራት ይበጃል። ካልሆነ በዘመን ሂደት እና ቅብብሎሽ በሚመጣ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለን እንዳልነበረን፣ የሆነው እንዳልሆነው ይሆንና በሌሎች ዓለም ባይተዋር የመሆንን ያህል መዳከር ይመጣል።

ይሄ ማለት በሉላዊነት ዓለም አንድ እየሆነ በመጣበት በዚህ ጊዜ እና በረቀቀ የቴክኖሎጂ መጥለቅለቅ ነገሮች ከቁጥጥራችን ውጪ ይሆኑና በተለይ ታሪክም፣ ባህልም፣ ቋንቋም የሌለን ይመስል እዛ እና እዚህ መርገጥ በስልጣኔ ሰበብ የባዕድ ቋንቋ እና ባህል የበላይነትን የመቀበል ብሎም ራስን የማጣት ፈተናዎች ይጋረጣሉ።

እውነት ለመናገር አሁን ባለንበት ጊዜ ብናምንም ባናምንም እየሆነ ያለው ይሄ ነው። እንደው ለመሆኑ ከዚህ ቀደም ሀይማኖታዊም ይሁን ታሪካዊ፣ ባህላዊም እንበለው… ክዋኔዎቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለምን መልካቸው እየተቀያየረ መጣ? ስለምንስ ቋንቋችን የባዕዳንን ካልቀላቀለ የተወራ አልመስል አለን? እሱ ብቻ አይደለም፤ በዘመን እና ትውልድ ቅብብሎሽ ትላንትን ለዛሬ፣ ዛሬን ለነገ እና ለሚመጣው እኛነታችንን ሳይበረዝ እና ሳይሸረሸር ለማስተላለፍ አሁን በያዝነው የግራ መንገድ ይሳካ ይሆን? በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል እና ስነ ልሳን ተመራማሪው ዶክተር ክበበ ፀሐይ የኛ ሀገር በሌላው ዓለም መነፅር ስትታይ እጅግ ልዩ፣ ውብ እና ቀለመ ብዙ  መልክ ያላት ናት፤ ይሄን በቋንቋው፣ በባህሉ፣በኪነ ሕንፃ አሰራርና ሌሎችም የእኛነታችን መገለጫ የሆኑትን ስንመለከት በሚገባ እንገነዘባለን” ይላሉ። ነገር ግን ይሄ ሁሉ የእኛነት መገለጫ እያለን ስለምን በማይሆነን እና ባልተገባ መንገድ እንደምንዳክር ካስተዋልን የደረስንበት ዘመን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ራሳችን ላይ አለመስራታችን ያመጣዉ ችግር እንደሆነ ያነሳሉ።

በዚህ ረገድ በተለይም ስለቋንቋ እና ባህል ካወራን  የመበረዝ አለፍ ሲልም ደብዛቸው የመጥፋቱ ነገር ሊገጥም ይችላል ብለዋል፤ ዶክተር ክበበ።

ተመራማሪዉ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን ወደራሳችን አናይም እንጂ እዚሁ ሀገር ውስጥ የትም ባህር ማቋረጥ ሳያሻን ልንጎበኘው፣ ልንደመምበት እና ልንደነቅበት የሚያስችል በርካታ መስህብ አለን፡፡ ይሄ በተለይ ቅኝ አለመገዛታችን ያመጣው ፀጋ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ቅኝ ግዛት ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ብሎም ማንነትን በመጭፍለቅ ሁሉንም የሚያሳጣ ነው ይላሉ።

ሌላው ዓለም እኛነታችንን ለማየት ከባህር ማዶ መምጣቱን ማስተዋል በቂ ማስረጃ መሆኑን ያስረዳሉ። ወደ ኋላ መለስ እንበልና በርካቶች ዋጋ የከፈሉለት እና ዛሬ ላይ የጥቁሮች የታሪክ ወር በሚል እስኪታሰብ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሁነት ስናስታውስ እውነት  ዓለም በእኩልነት ያምናል? የጥቁሮችስ ጥያቄ ተመልሶላቸዋል? ተከብረዋልስ ወይ? ስንል አሁንም መሰረታዊ ችግሮች ቁልጭ ብለው ይታያሉ። ለዚህ በአሜሪካ እና በሌሎች የሀገራት ሕገ መንግሥታት እና ሌሎች ሕጎች በሀገራቸው የሚኖሩ ዜጎች እኩልነት የማይካድ መሆኑን በግልጽ ቢያስቀምጡም ሥርዓት ወለድ ጭቆናው ግን አሁንም እንዳልተፈታ  ተናግረዋል።

ለዚህም በአሜሪካ ጥቁሮች እና በሌሎች ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት እንደማሳያ ያቀርባሉ፤ እውነትም አላቸው። እሺ የነሱስ ያኔ  በመኮርኮማቸው ሰበብ የመጣባቸው እዳ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ምስጋና ለታላላቆቻችን ይሁንና ከዚህ ነፃ ነበርን፤ ታዲያ አሁን አሁን በገዛ ፈቃድ እጅን ጠፍሮ የራስ ያልሆነን ማንነት ፍለጋ መኳተኑ አያስተዛዝብ ይሆን? እውነት ለመናገር የሁሉ መሰረት፣መነሻ ምንጭ የሆነው እኛ ርስ በርስ መግባባት እስኪያቅተን ጉራማይሌ መሆናችን ግር ያሰኛል።

ዶክተር ክበበ በተለይ ቋንቋ እና ባህል በተገቢው መጠን በቁርጠኝነት ካልተያዙና እንክብካቤ ከጎደላቸው ውሀ እንዳጣ ተክል መጠውለግ ብሎም መጥፋታቸው የማይቀር መሆኑ መታወቅ አለበት ይላሉ። ዛሬ ኢትዮጵያውያን በርካታ ቋንቋ፣ የራስ ፊደል እና የዘመን መቁጠሪያ፣ አለባበስ ፣አመጋገብ እንዲሁም ልዩ የኑሮ ዘይቤ መላበሳቸውን እንደቀላል ማየታችን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ተጠብቀው ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ውድ መስዋዕትነት የተከፈለበት የታሪክ አደራ አለብንና አሁንም ጊዜ ስላለን በጥንቃቄ ማሰብ እንዳለብንም ነው በአፅንኦት የሚገልፁት።

የነጮች በተለይም ምዕራባውያን በተለያዩ መንገዶች የባህል ወረራ ላይ መሆናቸው በግልፅ ይታያል፡፡ ለዚህም የሙዚቃ እና ፊልም ስራዎቻቸውን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ ዶክተር ክበበ እንደሚሉትም ለምሳሌ አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን አለባበሳችን፣ አነጋገራችን፣ ስሞቻችን እና ሌሎችንም ካየን የኛ ያልሆነ ነገር ይበዛዋል። በተለይ ህፃናት ልጆቻችንን በሚገባ መከታተል እና መቆጣጠር ላይ ካልሰራን ያለጥርጥር የትውልድ ቅብብሎሽ ክፍተት መፈጠሩ እና ማንነታችን መደብዘዙ አይቀሬ ነው።

አሁን ላይ እኮ በሌላው ዓለም ለእንስሳት፣ዛፎች እና ሌሎችም ፍጡራን የሚወጡ ስሞች እኛ ሀገር ለልጆቻችን ስም ሆነዋል፡፡ ይሄ ከየት የመጣ ነው? ካልን ራሳችንን ካለማወቅ ብሎም በጥንቃቄ ካለመስራት እንዲሁም ቅኝ አልተገዛንም በሚል ኩራት ብቻ ለዘመናዊ ባርነት ራሳችንን አሳልፈን በመስጠታችን ነው። በዚህ ረገድ ታዲያ መንግሥት በተለይም የትምህርት ተቋማት ላይ  እኛነታችን ላይ መሠረት ያደረገ ሥራን መሥራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።

(ዮናስ ታደሰ)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here