በእንጨት የተገነባው “ኤልማርኮ” የተሰኘው ስድስት ሜትር የተለካው በዓለማችን ሁለት ሀገራትን የሚያገናኝ አጭሩ ድልድይ መሆኑን ወንደርፉል ኢንጂነሪንግ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::
በእስፔን “ኤልማርኮ” እና ፓርቹጋል “ኦሮንች” መንደሮች መካከል በሚፈሰው አብሪሎንጎ በተሰኘው ወንዝ ላይ ነው ተሰራው 19 ኢንች ወይም 6 ሜትር ብቻ የሚረዝመው አጭሩ ድልድይ:: ድልድዩን በጥቂት ርምጃ ማቋረጥ ከአንዱ ሉዓላዊ ሀገር ወደ ሌላው ማሸጋገሩ ብቻ ሳይሆን አስገራሚው በዚያው ርቀት የሰዓት ጭማሪ አስከትሎ የእጅ ሰዓትን ማስተካከል ግድ ማለቱ ነው::ለዚህ ምክንያቱ ስፔን የመካከለኛው አውሮፓ ሰዓት (uTc 1 ሰዓት) ስትጠቀም ፓርቹጋል ደግሞ በምዕራባዊ አውሮፓ (uTc 0 ሰዓት) መገልገሏ አንድ ሰዓት ማስተካከልን ግድ ማለቱ ነው የተጠቀሰው::
ከ2008 እ.አ.አ አቆጣጠር በፊት መተላለፊያው ሕገ ወጥ /የኮንትሮባንድ/ ንግድ መገናኛ ነበር:: ከተጠቀሰው ዓመት በኋላ ግን በማህበረሰቡ ተሳትፎ በእንጨት መዋቅር ድልድዩ በመሠራቱ ህጋዊ የንግድ ልውውጥ ሰፍኖ የሕገ ወጥ /ኮንትሮባንድ/ የንግድ ቦታነቱ መቅረቱ ነው የተጠቀሰው:: ለዚህም በአውሮፓ ሀገራት መካከል ኗሪዎች ከሀገር ሀገር በነፃ መሸጋገር እንዲችሉ መፍቀዱ ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው::
የ“ኤልማርኮ” አጭሩ ድልድይ ስፋቱ 7 ጫማ ወይም አንድ ሜትር ከአርባ አምስት ሴንቲሜትር ብቻ ነው:: በመሆኑም መተላለፊያ ድልድዩ ከእግረኛ ፡ ብስክሌት እና ሞተር ብስክሌት ሌሎች ተሸከርካሪዎችን ማጓጓዝ አይችልም::
የ“ኤልማርኮ” ድልድይ እ.አ.አ ከመገንባቱ በፊት በነበሩት የቀደሙ ዓመታት የጎረቤታማቾቹ ስፔን እና ፖርቹጋል ኑዋሪዎች ከድንበሩ ወዲያ እና ወዲህ የሚገናኙት በበጋ በተለይም የወንዙ ውኃ በሚቀንስበት ወቅት በመፋሰሻው መካከል የሚገኙ ድንጋዮችን በመርገጥ እየዘለሉ ይተላለፉ እንደነበር ነው የተገለፀው::
በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች ከሀገር ሀገር በነፃ እንዲተላለፉ መፍቀዱ ለ“ኤልማርኮ” ድልድይ መመስረት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩም ነው በድረ ገጹ በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም