የሀረማያ ሐይቅ

0
113

የሀረማያ ኃይቅ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሀረማያ ወረዳ ነው የሚገኘው::ርቀቱም ከአዲስ አበባ 505 ኪሎ ሜትር ከሀረር ከተማ ደግሞ በሰሜን ምዕራብ ቀጣና 14 ኪሎ ሜትር ተለክቷል ::

የሀረማያ ኃይቅ ተፋሰስ 50 ኪሎ ሜትር ስፋት ይሸፍናል:: ኃይቁ በውኃ በተሞላበት ዘመን ጥልቀቱ በአማካይ 14 ሜትር ርዝመቱ ደግሞ 7 ኪሎ ሜትር እንደነበረ በ2011 ዓ.ም በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ድረ ገፆች አስፍረዋል::

የሀረማያ ኃይቅ እስከ ደረቀበት 2005 ዓ.ም ድረስ – ለሀረማያ ፣አወዳይ እና ሐረር ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል::ከ2005 ዓ.ም ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች መድረቁን ነው ጥናቶች ያረጋገጡት::

ለሀረማያ ኃይቅ መድረቅ ምክንያት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የኃይቁን ውኃ   በሞተር በተለያዩ አቅጣጫዎች በመሳብ በየዳርቻው ለጫት ልማት መዋሉ ቀዳሚ የኃይቁን ህልውና የፈተነ ሁነት ሆኖ ተቀምጧል:: በሁለተኛነት በኃይቁ ዙሪያ የሚገኙት ኗሪዎች ወደ ኃይቁ (buffer zone) ወይም ክልክል ቀጣና በመጠጋት መሥፈራቸው እና የኃይቁ ዳርቻ በመመንጠሩ አፈሩ ተጠርጎ ወደ ኃይቁ በመግባት በደለል መሙላቱ ለመድረቁ መንስኤ ሆኗል::በሦስተኛነት ለሀረማያ ኃይቅ መድረቅ የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ፣የዝናብ እጥረት እና የሙቀት መጨመር  ለመድረቁ መንስኤ ሆኖ ተቀምጧል::

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኃይቁ ምስራቃዊ ቀጣና ከፍ ያለ (ጋራ ዳሞታ) የተባለ አቀበት ያለበት በመሆኑ በአንፃራዊነት ከሌላው በኃይቁ ዙሪያ ከሚገኘው ቀጣና በላቀ ለአፈር መሸርሸር የተጋለጠ ነው::በዚህም ተጠራርጎ ወደ ኃይቁ መሐል የሚገባው ደለል የኃይቁን መድረቅ ያፋጠነ መንስኤ ሆኗል::

የኃይቁን ትንሳኤ ለማረጋገጥ ከተደረጉ ጥናቶች ማጠቃለያ በኃይቁ ዙሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ማጠናከር ፣በጫት የተያዘውን መሬት አነስተኛ ውኃ በሚፈልግ እንደ ‘ፓም ’ ያለ ተክልን በአካባቢው በማስተዋወቅ መተካት፣ እንዲሁም ወደ ጥብቅ ክልክል ዳርቻው (buffer zone) ሕገ ወጥ ሰፈራ ወይም የኗሪዎችን ጣልቃ ገብነት ማገድ መጠበቂያ ስልት ሆነው ተጠቁመዋል::

ለዘገባችን በመረጃ መንጭነት ሪስረች ጌት ፣ሴማንቲክ ስኮላር እና ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር ድረ ገጾችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here