የፍትሕ ቢሮ በፍታብሔር አስተዳደር ተግባር

0
167

በኵር ጋዜጣ በመጋቢት 8/2017 ዕትም በፍትሕ እና መልካም አስተዳደር አምዷ በፌዴራል ደረጃ የፍትሕ ተቋማት ተግባር እና ሚናን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀፅ ስድስት ንኡስ አንቀፅ ሁለትን መሰረት አድርጎ ፍትሕ ሚኒሥቴር በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት ዋና አማካሪ እና ተወካይ ሆኖ የመሥራት ሥልጣን እንዳለው ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

ሚኒሥቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ በወንጀል ፣ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ፣ በሰብአዊ መብት ፣ በሕግ ማርቀቅ እና ማስረፅ እንዲሁም በተለያዩ ሕግ ነክ ጉዳዮች ዝርዝር የማየት ሥልጣንና ተግባራት እንደተሰጡት በዘገባችን በዝርዝር አሳውቀን  ነበር::

እኛም በዚህ ዕትም ደግሞ የፍትሕ ተቋማት  በፍትሃብሔር ጉዳዮች  ዙሪያ  ያለው ኃላፊነት እና ተግባር ምን እንደሆነ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሃብሔር ጉዳዮች  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ መንበሩ ማናዬን ጠይቀን እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በርካታ ተግባር እና ኃላፊነት  አለበት፤ ከዚህ አንፃር በወንጀል እና ፍትሕ አስተዳደር ላይ መንግሥትን በመወከል መከራከር፣  በፍትሃብሔር  ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ መወከል፣ ሕግ ማርቀቅ ፣ የሰብዓዊ መብት አስተዳደር ዘርፍ ሰነዶችን ማረጋገጥ፣ መመርመር እንዲሁም ውክልና የመስጠት ሰፊ ሥልጣን እና ተግባር አለው፡፡

ፍትሕ ቢሮ ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች አንዱ በሆነው በፍትሃብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ አካል የሆነው አቃቢ ሕግ ሁለት ነገሮችን ያከናውናል፡፡  ይህም ማለት በቅድመ መከላከል  ረገድ የአገልግሎት ሕጎች በአግባቡ መፈጸማቸውን ክትትል ያደርጋል፡፡ በዚህም የመንግሥት አሠራሮች ግልፅ  እና ተጠያቂነት ያለባቸው እንዲሆኑ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12 በተደነገገው መሰረት በሕግ መመራት ያለባቸው ሥራዎች በሕግ አግባብ እንዲሠሩ በዋናነት ያማክራል፡፡ የመሬት ፣ የገንዘብ ፣ የከተማ ሊዝ… በአጠቃላይ በሕጉ አግባብ እንዲሠሩ ከሕግ አውጭው፣ ተርጓሚው  እና ፈፃሚው አካል ጋር በጋራ አብሮ ይሠራል፡፡

እንደ አቶ መንበሩ ገለፃ ሌላው የቅድመ መከላከል ሥራ የሕግ  ድጋፍ አገልግሎት መሥጠት ነው፡፡ የእያንዳንዱን ተቋማት አሠራራቸውን የሕግ ድጋፍ እና ቁጥጥር  ሥራ ይሠራል፡፡ ለአብነት አንድን  የግንባታ ሥራ  ከጨረታው ጀምሮ  እስከ ግንባታው አፈጻጸሙን በሕግ አግባብ መከናወኑን ምልከታ በማድረግ ለየተቋማቱ ሪፓርት ያደርጋል፡፡

ሌላው ቅድመ መከላከል ሥራ ደግሞ የውሎችን ረቂቅ የመመርመር ሥራ ነው፡፡ በፍትሃብሔር ሕግ 1678 በተቀመጠው መሠረት በትክክል መዋዋል የሚችሉ ሰዎች (ለመዋዋል ችሎታ ያላቸው ሰዎች) ናቸው ወይ ውሉን የሚመዋዋሉት?  ተዋዋይ ወገኖች ግልጽ የሆነ ሃሳብ ሰጥተው ነው ወይ ? ( ውሉን አውቀውት) ነው ወይ የሚገቡት? ብሎ ምልከታ ያደርጋል፡፡ የተዋዋሉበት ጉዳይ በሕግ ያልተገደበ ነው ወይ? (ለሞራል ወይም ለግዴታ ) በማለት ተቃራኒ አለመሆኑን ይመረምራል፤ ከዚህ ባለፈ ውሉ በጽሁፍ መሆኑን እና ሥልጣን ባለው አካል የሚደረግ መሆን እንዳለበት ሁሉ ይመረመራል፡፡

እንደ አቶ መንበሩ ገለፃ የቢሮው ሌላው  ተግባር ደግሞ በድሕረ መከላከል ረገድ ያለበት ሚና ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ አስፈጻሚ አካላትን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 280/2014 አንቀፅ 28 ንኡስ አንቀፅ 9 መሰረት አቃቢ ሕግ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚከሰሱበትም ሆነ በሚከሱበት ወቅት እነሱን ወክሎ ክርክር ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ በዓመት በአማካይ እስከ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በገንዘብ የሚገመቱ ክርክሮችን አድርጎ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረት ያድናል፡፡

በፍትሃብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዘርፍ አንዱ የክልሉ መንግስት እና በተዋረድ ያሉ የመንግሥት አካላትን ወክሎ ከመከላከል  በተጨማሪ ለወንጀል ተጋላጭ ለሆኑ  እና በኢኮኖሚ ማነስ በፍርድ ተማት  ቀርበው መከላከል ማይችሉ ሴቶችን፣ አረጋዊያንን፣ አቅመ ደካሞችን እና ሕፃናትን እየወከለ በሚከሰሱበትም ሆነ በሚከሱበት ወቅት ወክሎ እንደሚከራከር ዳይሬክተሩ ጠቆመዋል፡፡

ሕግ በማርቀቅ ረገድ የክልሉ መንግሥት አዋጆች እና ደንቦች እንዲረቀቁ ሲፈልግ አልያም አቃቢ ሕግ በራሱ የማያሠሩ ሕጎች በሚኖሩ ጊዜ አጥንቶ ሕግ ያረቃል፡፡

አቃቢ ሕግ በበኩሉ የረቀቁ ሕጎች የሕግ ተዋረድን ጠብቀው ነው ወይ የረቀቁት? የረቀቁት ሕጎች ለሕግ እና ለሞራል ተቃራኒ አይደሉም? በማለት  ይመረምራል፡፡

አቶ መንበሩ እንደገለጹት በዚህ ዓመት  ብቻ ወደ አምስት አዋጆች በተገቢው መንገድ አርቅቆ ለአስተዳደር ምክር ቤቱ ልኮ በክልሉ ምክር ቤት ፀድቀዋል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት እንዲረጋገጥ፣ ሰብዓዊ መብት እንዲሁም ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ በማረጋገጥ ረገድ አላሰራ ያሉ በተለይ የተበታተኑ ሕጎችን ወደ አንድ የማጠቃለል እና ለአጠቃቀም ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

አቃቢ ሕግ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ከሚያደርግባቸው ውስጥ አንዱ የኢንቨስትመንት እና የትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጉዳዮች መሆናቸውንም አቶ መንበሩ አንስተዋል፡፡ ሕግ ሕግነቱ የሚረጋገጠውም ወደ ልማት ሲተረጎም በመሆኑ ልማትን በሚያፋጥን መልኩ መተርጎም ይገባል፡፡ በእነዚህና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና የመሬት አሰጣጥ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ በመሥራቱም በርካታ  ገንዘብ ማስቀረት መቻሉን ነው የገለፁት፡፡

በሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ ዘጠኝ ላይ “ማንኛውም ሰው ሕገ መንግሥቱን የማክበር እና ማስከበር ኃላፊነት ስለወደቀበት በሕግ ፈር እና በሕግ የተቃኘ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ዳይሬክተሩ ሕጉን መሰረት አድርገው አብራርተዋል፡፡  ይህ ከሆነ ደግሞ ሰው ሰው በመሆኑ የተሰጠውን መብት እንዲጠቀም እንደሚያስችለው ነው አቶ መንበሩ ያሳሰቡት፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here