“… ግጭቶቹ የልጆቻችንን ዕድል ክፉኛ እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ይገባል”

0
194

የትምህርት ቤቶች አለመከፈት፣ ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎችም በተረጋጋ ሥነ ልቦና መማር አለመቻላቸው፣ የመምህራን ከስጋት ነጻ ሆነው ትውልድ የማፍራት ሥራቸውን አለማከናወናቸው ዛሬም ቀዳሚ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የትምህርት ጉዳይ ምንም እንኳ በከፍተኛ ደረጃ እየተፈተነ ያለው በአማራ ክልል ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ቢሆንም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነ ቁጥራዊ አኃዞች ያሳያሉ፡፡

በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት እንደ ሀገር በዚህ ዓመት ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎች ማረጋገጫ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒሥቴር መረጃ ያሳያል፡፡ በአማራ ክልልም ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፤ ከሦስት ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ጌታሁን ፈንቴ የጸጥታ ችግሩ በዞኑ 840 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም 630 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት እንዲርቁ ሆነዋል፡፡ 621 ትምህርት ቤቶችም ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በማስተማር ላይ የሚገኙት 156 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ አሁንም ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይቶች መቀጠላቸው ተጠቁሟል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን በበኩሉ በዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር ያቀደው 732 ሺህ ተማሪዎችን ነው፡፡ እንደ ዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደስታ አሥራቴ ገለጻ እስካሁን ማሳካት የተቻለው 199 ሺህ 220 ተማሪዎችን ብቻ ነው፡፡

በአማራ ክልል በተካሄደው “ትምህርት ለትውልድ!” ንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የትምህርት ቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በትምህርት ዘርፉ ያለውን ችግር በተገቢው መረዳት እና ለመፍትሔው በጋራ መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ የምሁራንን አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር የትምህርት አመራሮች መምህራንን መከታተል እና በተሟላ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

የተማሪዎች ምዝገባ እስከ መጋቢት 30 ድረስ እንደሚቀጥል ኃላፊዋ አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም መሪዎች በቀሩት ቀናት ሕዝቡን ለትምህርት በማነሳሳት ልጆች እንዲማሩ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ትልቁ መፍትሔ ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት እና አብሮ መሥራት መሆኑንም ተናግረዋል። የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት፣ ኅብረተሰቡ ትምህርት ቤቶችን እንዲጠብቅ ማድረግ እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ አሁናዊ ትምህርቱ በመምህራን መስዋዕትነት ጭምር መቀጠሉን ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ፣ መምህራን ሥራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት የሚሆኑ አካላት መወገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን ጥበቃ እንዲደረግ እና ትምህርት ቤቶችን ከግጭት ነጻ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ መምህራንም ማኅበረሰቡን ማስረዳት፣ ማሳመን እና ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ በኩል ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትም ችግሮቻቸውን በሃሳብ የበላይነት መፍታትን በማስቀደም እየተፈጠረ ያለውን የትውልድ ክፍተት ለመሙላት ባለ ድርሻ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተማሪ እና ትምህርት ቤትን መያዣ አድርጎ መታገል እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄው ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒሥትሩ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ “ትምህርት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ እና ሰብዓዊ የልጆች መብት ነው” ብለዋል፡፡ ትምህርት ሕጻናት የወደፊት ነጋቸውን የሚገነቡበት፣ ችሎታቸውን የሚከፍቱበት፣ ከዕድሎች ጋር የሚገናኙበት  ድልድይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ሀገራት የሚካሄዱ ግጭቶች ወይም ጦርነቶች የትምህርትን የሕጻናት ሰብዓዊ መብትነት እየጣሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ችግሩ ሕጻናት በትምህርት ሊያገኙ የሚችሉትን የወደፊት ዕድል የሚያጨናግፍ ሆኖ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ይህም የትጥቅ ትግል ትምህርት ቤቶች እንዲወድሙ፣ መምህራን እንዲፈናቀሉ እና እንዲገደሉ፣ የሕዝብ ማኅበራዊ ትስስር እና መዋቅር እንዲላላ ብሎም እንዲፈርስ፣ የሕጻናትን እና የወጣቶችን የወደፊት ብሩሕ ተስፋ እንዲደበዝዝ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የግጭቱ መዘዝ ውጤት ከዛሬ ይልቅ ነገ የከፋ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ተወላጅ ሕጻናት በሌሎች ክልሎች ካሉ እኩዮቻቸው ጋር መወዳደር እና መፎካከር በማይችሉበት ደረጃ ላይ መገኘታቸው ሁሉንም ሊኮረኩር እንደሚገባ ፕሮፌሰር ብርሐኑ አስገንዝበዋል፡፡

ትምህርት ለአንድ ዓመት  እና ከሁለት ዓመት  በላይ ሲቋረጥ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና እጅግ ከባድ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሐኑ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ወደ ትምህርት ቢመለሱም እንኳ የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጫና ትምህርት በመቀበል አቅማቸው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በግጭት ወቅት ያለፈውን ይዘት ለማካካስም ፈታኝ ይሆናል ነው ያሉት፡፡ ዛሬ በግጭት ምክንያት ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሕጻናት ትምህርታቸውን ቢቀጥሉም እንኳ በዕድሜ ካነሱ ታናናሾቻቸው ጋር መማራቸው ተጎጂ ያደርጋቸዋል፡፡

ሚኒሥትሩ በአማራ ክልል በጦርነቱ የፈረሱ 45 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዓመትም በግጭት የተጎዱትን ጨምሮ 17 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል፤ የመጠናቀቂያ ጊዜያቸውም ከአንድ ዓመት በፊት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሐኑ “ግጭቶችን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም እንኳ ባንችል ቢያንስ ግጭቶቹ የልጆቻችንን የወደፊት ዕድል ክፉኛ እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ይገባል” ብለዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በግጭት ውስጥ ላሉ እና በችግሩ ላለፉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለየ አትኩሮት ሰጠቶ እንደሚሠራ ሚኒሥትሩ አረጋግጠዋል፡፡

በግጭት የፈረሱ ትምህርት ቤቶችንም መልሶ ከመገንባት ባለፈ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ፍላጎትን ከፋይናንስ አቅም ጋር በማጣጣም እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የወላጆች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሚናም ከፍተኛ በመሆኑ የትምህርት ዘርፉ ግድግዳ ሆኖ ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

በግጭቶች ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የወደቀውን ትምህርት ለመታደግ በግጭት ላይ ያሉ አካላት እንቅፋት ከመሆን ይልቅ ደጀን ሊሆኑ እንደሚገባም ሚኒሥትሩ ጠይቀዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ማብራሪያ  በጦርነት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ትምህርት ማስጀመር እና ማስቀጠልን እንደ ጦርነት ማስቆሚያ አማራጭ አድርገው መጠቀማቸውን ነው፡፡ በዚህም ትምህርት ቤት በተገኙ ተማሪዎች ላይ የሰላምን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉ አስተምህሮቶችን በማስተጋባት ቀስ በቀስ ግጭት እየቀነሰ ሄዶ ሰላምን ለማረጋገጥ ተጠቅመውበታል፡፡ የእኛም አሁናዊ መርህ ትምህርትን የሰላም መንገድ አድርጎ መጠቀም ሊሆን ይበባል የሚል ነው፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመጋቢት 22  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here