አቶ በቀለ ሞላ በአብዛኛው ጊዜ ቀለል ያለ አለባበስ የሚመርጡ ግለሰብ ነበሩ። ልጆቻቸው ሲዘንጡ እሳቸው ትኩረታቸው ስራ ላይ ነበር። አቶ በቀለ ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ “እነሱ የሀብታም ልጅ ናቸው፤ እኔ ግን የድሃ ልጅ ነኝ” የሚል መልስ ይሰጡ እንደነበር ይነገራል።
አቶ በቀለ ሞላ ማን ነበሩ?፣ ለማደግ ምን ዋጋ ከፈሉ?
ከ16 ብር ንግድ ተነስተው 13 በተመሳሳይ ስም የሚጠሩ ሆቴሎችን ከፍተዋል። በኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ስም ያላቸው ስራ ፈጣሪ እና ታታሪ ሰው ነበሩ። ዋጋ ከፍለው ካሰቡበት ለመድረስ ብዙ ሰርተዋል። የትውልድ ዘመናቸው በ1905 ዓ.ም በአርሲ ነው።
ባልና ሚስት ከትዳር ሲለያዩ የበቀለ እናት ወ/ሮ አፀደ ሌላ ባል አግብተዉ ወደ ሐረርጌ ሄዱ። ሕጻኑ በቀለም አብሯቸዉ ሐረርጌ ገባ።
አቶ በቀለ 12 ዓመት ሲሞላቸዉ እናታቸዉ “ሂድና ሞጆ ያሉትን ዘመዶችህን ጠይቅ” ይሉና ለባቡር እና ለስንቅ የሚሆን 16 ጠገራ ብር ይሰጧቸዋል። ባቡር ለመሳፈር ወደ ድሬዳዋ ከመሄዳቸው በፊት ሐረር ከተማ ይቆዩና በብሩ እንቁላል ገዝተዉ አትርፈው መሸጥ ይጀምራሉ፤ ተሳካላቸው፤ በገበያው ውስጥ ታዋቂ እንቁላል ነጋዴ ሆኑ።
ከሐረር ተነስተዉ ሞጆ የገቡት የ16 ዓመቱ አቶ በቀለ እናታቸዉ የሰጧቸዉን 16 ጠገራ ብር 1000 አድርሰውት ነበር። ሞጆ እንደደረሱም ጊዜ አላጠፉም። ወዲያው የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፍተው ዕጣን፣ ሳሙና፣ መርፌ፣ ጨዉ እና ሌሎችንም ሸቀጦች መነገድ ጀመሩ። በተጓዳኝም ቅቤ፣ ማር፣ ጥራጥሬ፣ ጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ በመሳተፍና ጥሩ ገቢ ማፍራት ጀመሩ።
በዚህ መሐል ጣሊያን ኢትዮጵያ ገባ። የአቶ በቀለ ሕይወትም ፈተና ውስጥ ወደቀ። ጣሊያኖች “የውስጥ አርበኛ ነህ፤ አርበኞችን በገንዘብ ትረዳለህ” ብለው አሰሯቸዉ።
በ1933 ዓ.ም ጠላት ተሸንፎ ሲወጣ አቶ በቀለ የንግድ ሥራቸዉን ሻይ በመሸጥ እንደገና ጀመሩ። የሻይ ቤት ሥራቸው በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በባቡር የሚጓዙ መንገደኞችን በማገልገል ላይ ያተኮረ ነበር። ሻይ የሚጠጡ ደንበኞችን የበለጠ ለመሳብም “ሻይ የጠጣ ይከብራል፤ ጠጅ የጠጣ ይከስራል” እያሉ ማስታወቂያ በባቡር ጣቢያዉ ያስነግሩ ነበር።
ሥራዉ እየተሳካላቸው በመሄዱም ከሻይ ሥራ ወጥተው የመጀመሪያውን ዘመናዊ ሆቴል በ1941 ዓ.ም በዚያው በሞጆ አቋቋሙ።
ሆቴሉ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ እና ምሥራቅ የኢትዮጵያ ግዛቶች በባቡር ወይም በመኪና ለሚጓጓዙ መንገደኞች የሚያገለግሉ 21 የመኝታ ክፍሎች ነበሩት። የሆቴሉ ሥራ እየተሳካላቸዉ ሲሄድ በ1945 ዓ.ም መቂ ላይ፣ በ1951 ደብረ ዘይት እና በ1953 ሌላ የተሻሻለ ሆቴል በሞጆ ከተማ በመገንባት ቅርንጫፎቻቸውን ማስፋፋት ቀጠሉ።
ይህንን ጥረታቸውን የተረዱት በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኀይለ ሥላሴ ላንጋኖ የሚገኘውን በቀለ ሞላ ሆቴልን በድንገት ሄደው ጎበኙ። ንጉሠ ነገሥቱ እየተሰጠ ባለው አገልገሎት በጣም ተደሰቱ።
በቀለ ሞላ የውጪ አገሩን የአሠራር ልምድ ቢቀስሙ ላገራቸው የተሻለ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ በሚል ወደ አውሮፓ ተጉዘው በሆቴል የሙያ መስክ ያለውን የአሠራር ባህል ጎብኝተው እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል። እንደተጠበቀውም ከጉብኝታቸው በኋላ አሠራራቸውን ዘመናዊ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ከሞጆ እስከ ሞያሌ፣ ከወላይታ እስከ ባሌ፣ ከአዋሽ እስከ ጅቡቲ ቅርንጫፍ ሆቴሎችን ከፈቱ።
በቀለ ሞላ ከገነቧቸው ታዋቂ የሆቴል ቅርንጫፎቻቸው መካከል በሞጆ፣ መቂ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ ላንጋኖ፣ አዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ ሞያሌ፣ ወላይታ፣ ባሌ ጎባ፣ ናዝሬት፣ አዋሽ፣ ድሬዳዋ፣ ጅቡቲ፣ደብረ ዘይት እና በአዲስ አበባ የሚገኙት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በቀለ ሞላ ለዚህ ትጋታቸውና ለሆቴል ኢንዱስትሪ መስፋፋት ላደረጉት አበርክቶ ከቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ጀምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ዓለም አቀፍ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።
በኢትዮጵያ በሆቴሎች እና በቱሪዝም የሥራ ዘርፍ ፋና ወጊ በመሆን ሀገራቸውን ለበርካታ ዓመታት አገልግለው መጋቢት 22 ቀን 1992 ዓ.ም በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አሻራቸው በምድር ፍሬ እየሰጠ አለ፡፡ ታሪካቸው ከኢትዮጵያ ሆቴል እና ቱሪዝም ጋር ተያይዞ ይነሳል። ስለ ሥራ ፈጠራ እና ዋጋ ከፍሎ ስለ ማደግ ሲታሰብ በቀለ ሞላ ስማቸው እንዲጠቀስ የሚያስገድድ ቅርሳቸውን አስቀምጠው አልፈዋል።
የዛሬው ትውልድስ? ምቹ ባልሆኑ ጊዜያት ለዛሬ መልካም መንገድ የሚጠርጉ ሰዎች ውስን ናቸው። በአክሱም፣ በላሊበላ፣ በአድዋ እና በሌሎች ቀደምት ታሪኮች ኩራት የማይሰማው ሰው ኢትዮጵያዊ ካልሆነ ብቻ ነው። ባለፈው መኩራት ተገቢ ነገር ነው። ጥያቄው እኔስ ምን ለትውልድ የሚተርፍ ነገር ሰራሁ የሚለው ነው።
በቴዎድሮስ፣ በበላይ፣ በምኒሊክ፣ በዮሐንስ፣ በአብዲሳ አጋ፣ በኡመር ሰመተር፣ በንጉሥ ሚካኤል እና ሌሎች መሪዎች እና ጀግኖች መመካት ለዚህ ትውልድ ምን ይበጀዋል፤ እሱም እንደ ቀደምት መኩሪያዎቹ መልካም አሻራውን ካላስቀመጠ?
አሻራህ ምንድን ነው? ለስምህ መጠሪያ ምን አስቀምጠሃል? ከሞትህ በኋላ እስከ ስንት ዓመት ድረስ ሰዎች ያስታውሱሃል?
ቻይናዊው ቢሊየነር ጃክማ “ነቲንግ ኢዝ ፎር ፍሪ (አንድም ነገር በነጻ አይገኝም) ይላል። ለስማችን መጠሪያ የሚሆን አሻራ ማስቀመጥ ከፈለግን የስነ ልቦና ባለሙያው ካርል ዩንግ እንደሚለው ከባዱን መስመር መምረጥ አለብን። ዩንግ “ትልቁ ጉዳያችሁ በምትፈሩት ነገር ውስጥ ነው” ሲለን አሻራ ማስቀመጥ ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳናል።
አብዛኛው ሰው በሞተ በ40 እና 80 ቀኑ ቤተሰቦቹ ሊረሱት ጫፍ ይደርሳሉ። ብዙዎቹ ይህ የሞተ ሰው ማን እንደሆነ አያውቁም። ጎረቤቶቹ እና የመንደር ሰዎች የስራ ባልደረቦቹ በቀናት ውስጥ ረስተውታል።
ለምን ረሱት? የሚታይ፣ የሚጨበጥ፣ የሚያነጋግር አሻራ ስላልነበረው ነው። ጥላሁን ገሰሰ ሞቷል፡፡ ማዲንጎ አፈወርቅ እና ጸጋዬ ገብረመድኅን ሞተዋል። ሌሎችም በተለያዩ የስራ መስክ የነበሩ ሰዎች ሞተዋል። ባስቀመጡት አሻራ ግን ዛሬም አብረውን አሉ። የጥላሁን ሞት መለየት እንጂ ከስራው የተነሳ ሕያው ነው። በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ሙዚቃውን ሳልሰማው አልውልም፤ ጥላሁን አልሞተም የሚሉት ለዚህ ነው።
መለወጥን፣ አሻራ ማስቀመጥን፣ ሕያው ሆኖ መኖርን የማይፈልግ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። ድመት በጣም ስጋ ይወዳል አሉ። ቀዝቃዛ ውኃ ከመፍራቱ የተነሳ ሐይቅ ዳር ሄዶ አሳ ለመብላት ሲጠብቅ ውሎ ሳይበላ ይመለሳል። አሳው “አያ ድመት ና እንጅ ከሐይቁ አውጥተህ ብላኝ” እያለ እንዲለምነው ይፈልጋል ልበል? እሱ ቅዝቃዜ ፈርቶ ሲመለከተው ውሎ ርቦት ይመጣል። ድመቱ የሚፈልገው የአሳ ስጋ መብላት ነው። በተግባር ግን እግሩን ሐይቅ ውስጥ መክተት አይፈልግም። መለወጥ እየፈለጉ የሚገባውን ዋጋ አለመክፈል ማለት ነው። ምግብ መብላት የሚፈልግ ሰው የምግቡን ዋጋ ያህል ብር መክፈል አለበት። ካልከፈለ በርሀብ ይቀጣል። ወይም ክብሩን ሸጦ ለምኖ በልቶ ያድር ይሆናል።
ጥሩ ሕይወት መኖር የብዙዎቻችን ፍላጎት ነው። ለምንፈልገው ነገር ዋጋ ስለማንከፍል በምኞት ሕይወታችን ያልፋል። በቀብራችን አለት እንኳን ኖሮ ኖሮ ሞተ የሚል ፍሬ አልባ ታሪካችን ነው የሚነበበው፤ መጣ፤ ተመልሶ ሄደ የሚል ብቻ።
ባይናንስ ድረገጽ ለስኬት የሚከፈሉ ዋጋዎችን በዝርዝር አስቀምጧል። የቁሳቁስ፣ ፋሽን፣ አልባሳት ፍላጎቶች ሩቅ ለሚጓዝ ሕልመኛ ሰው አይሆኑም። እነዚህ ጊዜያዊ ደስታ የሚፈጥሩ ነገሮች ወደ ኋላ መቅረታቸው ጥሩ ህይዎት ለመኖር ሲባል መስዋእት ይቀርባሉ። ቢሊዬነሩ፣ የኢንቨስትመንት እና ሰብዕና ግንባታ መጽሐፍ ደራሲው ሮበርት ኪዮሳኪ “ደሃዎች የቅንጦት ቁሶችን መጀመሪያ ይገዛሉ፤ ሀብታሞች ግን በኋላ” እንደሚለው የብዙዎቻችን ሕይወት አካሄድ እንዲያ ነው። ደሀዎች እና ብዙ ርቀት የሚሻገር ሕልም የሌላቸው ሰዎች ሰውነታቸው በጌጣጌጥ ያሸበረቀ ነው። አንገታቸው ሁሉ ወርቅ ነው። ቤታቸው በውድ እቃዎች የተሞላ ነው። ደሀዎች በወጣትነት እና የመስሪያ እድሜያቸው እቃ መግዛት እና ማጌጥን ያስቀድማሉ። በመቆጠቢያ ጊዜያቸው ጊዜያዊ ነገሮችን በማድረግ እና በመልበስ ገንዘባቸውን ያባክናሉ። ትኩረታቸው ፍሬ በማያፈራ ፍጆታ ያልፋል፡፡ ገንዘባቸው እና ጉልበታቸው ሲገባደድ ለመስራት ያስባሉ። ሀብታሞች ግን ገንዘባቸውን ለኢንቨስትመንት ያውሉታል። ተጨማሪ ገንዘብ ለመስራት ይጠቀሙበታል። በኋላ እነሱ ተቀምጠው ገንዘባቸው ገንዘብ ይሰራል። ደሀዎች ሲመሽ ይሯሯጧሉ፡፡
በሮበርት አገላለጽ ሀብታሞች ለታላቅነት በሚያደርጉት ጉዞ የቁሳቁስ እና አልባሳት ምኞታቸውን ለነገ ዓላማቸው መቃናት ሲሉ መስዋእት ያደርጉታል። በሀገራችን የተገላቢጦሽ መስሎ የሚታየኝ ሌላ ነገርም አለ። በብዙ አጋጣሚዎች የምናየው የአንድ የተማረ ወጣት ጉዞ ይህን ይመስላል። በ18 ዓመት ፍቅር፣ እስከ 24 ትምህርት፣ በ28 ትዳር፣ ቀጥሎ ልጅ ማሳደግ እና መሥራትን ይመስላል። ወጣቱ አፍላ የሥራ ጊዜው ከ20 እስከ 30 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ነው። ይህ ጊዜ ግን በመዝናናት፣ በጊዜያዊ ተግባራት እና የተሻለ ስራ ለመስራት በሚደረግ ሙከራ የሚባክን ነው። መዝናናት ብዙ ጊዜ በወጣትነት እድሜ የሚከወን ተግባር ነው። ከልጆች በኋላ መዝናናት አይታሰብም። ሮጦ የመስሪያው ጊዜ በከንቱ ይባክናል። ኑሮ እና ሕይወት ሲከብድ 30ዎች እድሜ መጨረሻ እና አጋማሽ ላይ ብዙ ሰዎች ይባንናሉ። በከንቱ የባከነው ጊዜ ይጸጽታቸዋል። ጥቂቶች መስመር ቀይረው ጥሩ ይጓዛሉ። ብዙኀኑ ግን በኀላፊነት እና ቤተሰብ በመምራት ጫና ይጎብጣሉ።
ናፖሊዮን ሂል “ትላልቅ ስኬቶች የትላልቅ መስዋእቶች ውጤት ናቸው” ይላል። ስኬት ለማንም ሰው ቀላል አይደለም። በቀላሉም አልተገኘም። ሰው የድካሙን ፍሬ ይበላል ተብሎ በቅዱሳን መጻሕፍት እንደተጻፈው ሁሉ ብዙ መስዋእት የሚያቀርቡ ሰዎች ፍሬያቸውም የበዛ ይሆናል። ስኬት አጋጣሚ አይደለም፤ በጽናት እና ትጋት የመጓዝ፤ ተገቢውን ዋጋ የመክፈል ውጤት እንጂ:: ታዋቂው ቦክሰኛ ሙሀመድ አሊ “በየደቂቃው የማደርገው ልምምድ በጣም ያስጠላኛል፤ ነገር ግን ለራሴ አሁን ብትሰቃይና የሕይወት ዘመን አሸናፊ ሆነህ ብትኖር ይሻልሃል እለዋለሁ” ብሏል። አሸናፊነት በነሲብ አይገኝም፤ ዋጋ መከፈል አለበት።
ጊዜ ሌላው ወደ እድገት በሚደረግ ጉዞ መስዋእት የሚሆን የሰው ልጆች ድንቅ ስጦታ ነው። በተጨማሪም ስኬት ላይ የደረሱ ሰዎች ወጣትነታቸውን፣ ትዳራቸውን፣ ጤናቸውን፣ ደህንነታቸውን፣ አቅማቸውን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ጊዜያዊ ደስታቸውን፣ ምቾታቸውን፣ ማንነታቸውን እና ሰዎችን በማጣት ለተሻለ ሕይወት ሲሉ ሰውተዋል።በዚህም የመንፈስ፣ የጊዜ እና የገንዘብ ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ የሚችሉበት የሕይወት መስመር ውስጥ መግባት ችለዋል። አንተስ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነህ?
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም