የበልግ ሰብል ልማት ከየት ወዴት?

0
253

ኢትዮጵያ በምግብ ሰብል ራሷን ለመቻል፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከመኸር ሰብል በተጨማሪ ለበልግ ሰብል ልማት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።

ምጣኔ ሀብቷንም ሆነ የምግብ ፍጆታዋን በግብርናው ዘርፍ የመሠረተችው ኢትዮጵያ አብዛኛውን ምርት ከምታገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ደግሞ የአማራ ክልል ነው። ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃም ይህን ነው የሚያረጋግጠው፤ ክልሉ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከ33 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለው ልብ ይሏል፡፡

ክልሉ ይህን አበርክቶውን ለማሳደግም ሆነ ምርታማነትን ለመጨመር ታዲያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በዝናብ ብቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚመረትባቸው አካባቢዎች የሚገኙበት እንደመሆኑም የአካባቢዎቹን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የሰብል ምርት በሁለት የዝናብ ወቅቶች ይከናወናል፤  የመኸር ወቅት ሰብል ልማት ዋናው ሲሆን ሌላው ደግሞ የበልግ ወቅት የሰብል ልማት ነው፡፡ ወቅቱ የበልግ ሰብል የሚለማበት ነው፤ የምሥራቅ አማራ አካባቢዎች (ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች) ደግሞ ዋና ዋናዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች ናቸው።

የበልግ ውቅት የግብርና ሥራን በተመለከተም በኩር ጋዜጣ አርሶ አደሮችን አነጋግራለች፤ አርሶ አደር ፀጋ አከለ አንዱ ሲሆኑ የሰሜን ወሎ ዞን አንጎት ወረዳ ቀበሌ 03 ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ በስልክ እንደነገሩን በመኸር፣ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በበልግ ወራት በማምረት ቤተሰባቸውን ከመመገብ አልፈው ምርቱን ለገበያ ያቀርባሉ። በዘንድሮው የበልግ ወቅትም በአንድ ሔክታር መሬት ላይ ገብስ እና ስንዴ ለማልማት ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ከዚያም ኮምፖስት በመጨመር ዘርተው አብቅለዋል። አሁን ላይ ያለው ቡቃያም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ኃይሉ ካሳው በአንድ ሔክታር መሬታቸውን አርሰው እና አለስልሰው በበልግ ዘር እንደሸፈኑ ነግረውናል። ምንም እንኳን ዝናቡ ዘግይቶ የገባ ቢሆንም አሁን ላይ የበልጉ አየር ንብረት ጥሩ በመሆኑ ማሳቸውን በዘር ሸፍነዋል። የሚዘንበውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የመኸር እርሻ እያረሱ እና እያዘጋጁ ነው።

የተሻለ ምርት ለማግኘትም የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያከናወኑ እደሚገኙ (ማረም፣ ከተባይ መከላል እና መሰል የጥበቃ ሥራዎች) የተናገሩት አርሶ አደሩ በሁለት ሔክታር መሬታቸው ስንዴ እና ገብስ ዘርተው እየተንከባከቡ መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ የግብርና ባለሙያዎች ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተሉ እገዛ ያደርጉላቸዋል። ለብዙ ዓመታትም የተፈጥሮ ማዳበሪያን ወይም ኮምፖስት ይጠቀማሉ። ይህም የአፈር ለምነቱን ከመጠበቅ ባለፈ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በዚህ ዓመትም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በብዛት አዘጋጅተው በመጠቀም ዘርም በወቅቱ ዘርተዋል። ይህም የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን ለመቀነስ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

የበልግ አብቃይ ከሆኑት አካባዎች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው አንጎት ወረዳ አንዱ ነው፤ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ተስፋ ጌታቸው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት የበልግ ወቅት ሰብሎችን ለማምረት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተው አምስት ሺህ 405 ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል። አንድ ሺህ 550 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል። ከዚህ በተጨማሪም 132 ሺህ 400  ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልፀዋል። ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም በሥራው እየተሳተፉ ነው።

ኃላፊው እንዳሉት የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች  ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ ይገኛል። በተመሳሳይ ከበልግ ሰብል ልማት ጎን ለጎን የመኸር ሥራ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው። በበልግ ወቅት ከለማው ሰብልም 113 ሺህ 500 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጽ/ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ተገኘ አባተ ለበልግ ሰብል ልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ነግረውናል። ለአብነትም የእርሻ ድግግሞሽ፣ ማሳን በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት፣ የአፈር ማዳበሪያን ማቅረብ እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይገኙበታል።

እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በልግ አብቃይ ናቸው። በዋናነት ደግሞ አንጎት፣ ጋዞ፣ ዋድላ፣ ግዳን፣ ጉባላፍቶ እና ላስታ ወረዳዎች በበልግ ወቅት ከፍተኛ የሰብል ልማት የሚታይባቸው ናቸው።

በዞኑ በ2017 የበልግ ወቅት 32 ሺህ 573 ሔክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 25 ሺህ 901 ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ኃላፊው አስረድተዋል።

ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉት የግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጎን በመሆን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አቶ ተገኘ ተናግረዋል። የዝናብ ስርጭቱ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት ኃላፊው ይህም የተሻለ ምርት ለማግኘት ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ከመምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በዞኑ በበልግ ወራት ከተሸፈነው ሰብል ከሰባት መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት  ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ክልሉ በሦስት ዋና ዋና ወቅቶች (በመኸር፣ በበጋ መስኖ እና በበልግ ወቅቶች) ሰብል በማልማት ይታወቃል። ይህም ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱ ብሎም ለውጪ ገበያ በማቅረብ ለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻን ይዟል። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራያ በበልግ ወራት በዋናነት ገብስ፣ ስንዴ፣ ማሾ፣ ጤፍ እና የጥራጥሬ ሰብሎች ይመረታሉ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ እንዳስታወቀው በ2017 ዓ.ም የበልግ ወቅት 240 ሺህ ሔክታር መሬት በማረስ ከተለያዩ ሰብሎች አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን  ኩንታል ምርት ለማምረት አቅዶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም የእርሻ ሥራው ሙሉ ለሙሉ በድግግሞሽ ታርሶ የሰብል ዘር እየተከናወነ እንደሚገኝ ዶክተር ማንደፍሮ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ በደቡብ ወሎ ዞን ከ16 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን በአብነት ያነሱት ዳይሬክተሩ ዕቅዱን ለማሳካት “አርሶ አደሩ ወቅቱን የዋጁ ተግባራትን መከተል ይገባዋል” ብለዋል። አረምን በወቅቱ ማረም፣ ሰብሉን ከተባይ መከላከል፣ ማሳውን መፈተሽ፣ … እና መሰል ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱንም ገልፀዋል።

ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው አመራር እና የግብርና ባለሙያ አርሶ አደሩን ማማከር፣ ማገዝ፣ ዘመናዊ አሠራሮችን እንዲተገበሩ ማገዝ እና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ አሠራሮችን እንዲተገብር ሙያዊ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በተመሳሳይ ለአርሶ አደሮች ወቅታዊ መረጃ እና የምክር አገልግሎት፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን እንዲከተሉ እና ግብዓትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የበልግ ዝናብ ሥርጭት ዘግይቶ ሊገባ እና አልፎ አልፎም ፈጥኖ ሊወጣ ይችላል፤ በመሆኑም ችግሩን ታሳቢ በማድረግ ፈጥነው ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን መዝራት “ከአርሶ አደሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው” ብለዋል።

ዶክተር ማንደፍሮ እንዳስገነዘቡት በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ እየዘነበ ነው፤ በመሆኑም በልግ አልሚ አርሶ አደሮች በአግባቡ ውኃ አቁረው በመያዝ ሊጠቀሙበት ይገባል።

የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር እዳስታወቀው በ2017 የበልግ እርሻ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ከ98 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። እስከ አሁንም ከ400 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል።

ከሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት የማሕበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ታርሷል። ለበልግ ልማቱ ዕቅድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲቀርብ ተደርጓል።

ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት አርሶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች በስፋት በማሳተፍ በበጋ መስኖ፣ በመኸር እና በበልግ እርሻ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ እየተመረተ መሆኑንም መረጃው አክሏል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያ መረጃ መሠረት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለእርሻ ምቹ የሆነ ዝናብ እየዘነበ ነው። በመሆኑም በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተመላክቷል።።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here