“የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም” የሚለው የሩሲያውያን አባባል ዛሬ ላይ እንደ ዓለምም ሆነ እንደ ሀገር በሌላ ሰው ሐብት መበልጸግን አስበው ለተነሱ ሌቦች ታስቦ የተነገረ ንግርት ይመስላል፡፡ ዓለም ለሁለት ነጠብ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ የሀብት ምዝበራ የምትዳረገው በሙስና ነው፡፡ ይህም ከዓለም ጥቅል ዓመታዊ ገቢ ውስጥ አምስት በመቶ ድርሻን እንደሚይዝ የዓለም ባንክ በድረ ገጹ ያጋራው መረጃ ያሳያል፡፡
የሙስናን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ለመመልከት በሕዝባዊ አገልግሎት ዘርፍ ያለውን የሙስና ሁኔታ የሚከታተለውን የ’ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል’ መረጃ ማየት በቂ ይሆናል፡፡ ድርጅቱ በ2024 እ.አ.አ የ180 የዓለም ሀገራትን የሙስና ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በኢኮኖሚ ያደጉ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ግጭት የሌለባቸው ሀገራት በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ሙስና ያለባቸው በሚል ተጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ እና ሲንጋፖር ይጠቀሳሉ፡፡ በአፍሪካም ሲሸልስ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ቦትስዋና እና ሞሪሺየስ በዝቅተኛ ደረጃ ሙስና የሚፈፀምባቸው ሀገራት በመሆን ተለይተዋል፡፡
ሥር የሰደደ ሙስና ያለባቸው ሀገራት ተብለው በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተጠቀሱት ሀገራት ለችግሩ መንሰራፋት መሠረቱ ግጭት፣ ያላባራ ቀውስ፣ የአመለካከት እና የግንዛቤ ክፍተት መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን በ99ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ይህም ደረጃዋ ከፈረንጆቹ 2021 ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ሆኖ ተመላክቷል፡፡ ያም ሆኖ ከጎረቤት ሀገራት ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ስትነጻጸር በተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሆና ተነስታለች፡፡
የሙስና ትርጉም ስንት ነው?
ትራንሰፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሙስና በአደራ የተሰጠ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነው ይለዋል፡፡ አደራን አለመጠበቅ፣ እምነትን ማጉደል ወይም አለመታመን፤ በጉቦ፣ በምልጃ እና በአድሎ ሀቅን፣ ውሳኔን ወይም ፍትሕን ማዛበት ሲል የገለጸው ደግሞ የብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት ነው፡፡
በግል ወይም በቡድን፣ በፖለቲካ መሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ሥልጣንን እና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የሕዝብን ጥቅም እና ፍላጎት ለግል ጥቅም የማዋል ኢሥነ ምግባራዊ ድርጊት ብሎ የሚገልጸው ደግሞ የፌዴራል የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከል ነው፡፡ በተጨማሪም በመንግሥት ወይም በሕዝብ ሀብት እና ንብረት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ማጭበርበር መፈፀም፤ ሕግ እና ሥርዓትን በመጣስ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት እና በሃይማኖት ትስስር ላይ ተመርኩዞ አድሎ መፈፀም፣ ፍትሕን ማጓደል እና ሥልጣን እና ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ሕገ ወጥ ጥቅም ማግኛ ነው፡፡
የተዛባ አመለካከት እንደ ዋና ፈተና
በኢትዮጵያ ላለው የሙስና ችግር መስፋፋት ቀዳሚው ምክንያት ከሰዎች አመለካከት ጋር የተያያዘው ነው፡፡ ስስት፣ ሁሉንም ነገር ለኔ ባይነት፣ ሳይሠሩ በአቋራጭ ለመበልጸግ ከመፈለግም ባለፈ ሙስና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታይበት መንገድ ችግሩን ለመቆጣጠር ፈተና አድርጎታል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው አባባል ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ይሆናል፡፡ ይህም ሌቦች እንዲበረታቱ ሲያደርግ በአንጻሩ ሙሰኞችን ለማጋለጥ የሚሞክሩ አካላት እንደ ምቀኛ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲንሰራፋ በር ከፍቷል፡፡ ሌባን ደግፎ ንጹሀንን የሚኮንን አመለካከት ባለበት የሙስና ወንጀልን ማጋለጥ መመርመር እና አጥፊዎችን ለሕግ አቅርቦ ለማስቀጣት እንዳይቻል ፈተና መሆኑን የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከል አስታውቋል፡፡
የሙስና ተጽእኖ እስከ ምን?
ሙስና እና ሌሎች ብልሹ አሠራሮች በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ከማድረግ ጀምሮ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴው እንዲዳከም እንደሚያደርግ ያስነበበው ሙስና ላይ ጥናቶችን የሚያካሂደው ‘ኮራፕሽን ሪስክ ዶት ኦርግ’ (www.corruptionrisk.org) ነው፡፡ ሙስና በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የመንግሥትን አቅም ያዳክማል፡፡ ይህም አስፈላጊ የሆኑ የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እና የኅብረተሰቡን ተግዳሮቶች ለመፍታት እንዳይችል ያደርገዋል፡፡ እነዚህም ምክንያቶች በጊዜ ሂደት ሀገርን ወደ ግጭት እና ቀውስ ያስገባሉ፡፡
ሙስና የሕግ የበላይነት እንዲሸረሸር በማድረግም ከፍ ያለ ተጽእኖ አለው፡፡ ምክንያቱም በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሥልጣን እና ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ማንኛውንም ርምጃ ከመውሰዳቸው ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡
ለአካባቢ ጎጂ፤ ለሕዝብም ጠቃሚ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች የሚፈቀዱት ወይም የሚከናወኑት በጉቦና በሌሎች ብልሹ አሠራሮች በመሆኑ ሙስና የአካባቢ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ይታመናል፡፡
ተጠያቂነት ላይ …?
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሐኑ ጎሽም እንደገለጹት የሙስና ወንጀልን ለመከላከል፣ አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እና የተዘረፈውን ሐብት ለማስመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ኃላፊው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሙስና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በተለያየ መንገድ እየተፈጸመ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡
በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች የሚስተዋለውን የመሬት ወረራ ለችግሩ አሳሳቢነት ማሳያ አድርገው አንስተውታል፡፡ በባሕር ዳር በከተማ 22 ሺህ 464 አባል ያለው እና ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ በወሰዱ 936 የቤት ማኅበራት ላይ በፖሊስ እና በፍትሕ ቢሮ ቅንጅት በተደረገ ምርመራ አላግባብ የተወሰደ መሆኑ መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ ይህንንም ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን ማኅበሩ ፈርሶ ወደ መንግሥት ገቢ እንዲደረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በጎንደር ከተማ አስተዳደርም 37 ሺህ 861 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ አላግባብ መወሰዱን አቶ ብርሐኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የቦታ ወረራም 751 ግለሰቦች ተሳታፊ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ ሐብት የማስመለስ ሥራውም እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሙሰኞች በሙስና ተጠቃሚ ለመሆን ያሰቡትን ሕልም በማክሸፍ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ተሳታፊዎችን ሕጋዊ ርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ ሐብት የማስመለስ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለአብነት በ2017 ዓ.ም ስድስት ወራት ውስጥ ከፖሊስ ተጣርተው ከቀረቡ 752 የሙስና መዝገቦች መካከል በ223ቱ ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቀዋል፡፡ የባለፈውን ዓመት ጨምሮ 819 መዝገቦች ፍርድ ቤት ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት ኃላፊው፤ ከዚህ ውስጥ 89 ግለሰቦች ጥፋተኛ ተብለው ውሳኔ መተላለፉን ጠቁመዋል፡፡
ሐብት የማስመለስ ሥራው በተለያዩ ሕጋዊ መንገዶች ይፈጸማል ያሉት አቶ ብርሐኑ፣ ከክስ በፊት 337 ሚሊዮን 580 ሺህ 723 ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ 47 ሺህ 862 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ማስመለስ መቻሉንም ተጠቁሟል፡፡
ከቤት ማኅበራት ጋር በተገናኘ “የቤት ማኅበር እናደራጃችኋለን” በሚል ከግለሰቦች ተወስዶ የነበረውን 243 ሚሊዮን 586 ሺህ 853 ብር ማስመለስ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡ 11 ሚሊዮን 262 ሺህ 940 ብር ደግሞ የተዘረፈን ሐብት ለማስመለስ በተጣለው ቅጣት ገቢ የተደረገ የገንዘብ መጠን መሆኑን አቶ ብርሐኑ ጠቁመዋል፡፡ 66 ሚሊዮን 785 ሺህ 303 ብር በኤግዚቢትነት ተይዞ በፍርድ ቤት እንዲወረስ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ተስፋ የተጣለባቸው ማምከኛዎች
የሙስና ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል እና ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የክልሉ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከፍትሕ ቢሮ እና ከክልሉ ፖሊስ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ይህ መሆኑ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? የሚለውን በፍትሕ ቢሮ የጸረ ሙስና ወንጀል አቃቤ ሕግ ፍቃዴ ምስጋናው ያብራራሉ፡፡ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ሕግ የኔ የሚሉት መዝገብ እንዳይኖራቸው፣ ይልቁንም ጉዳዩን በጋራ እንዲሠሩ የሚያበረታታ መሆኑን ቀዳሚው አበርክቶ አድርገው አንስተዋል፡፡ አቃቤ ሕጉ ቀድሞ በነበረው አሠራር ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ጉዳዩን ወደ አቃቤ ሕግ ከመራ በኋላ በጉዳዩ ላይ የፖሊስ ቸልተኝነት ይስተዋል እንደ ነበር አንስተዋል፡፡ አሁናዊ ቅንጅቱ ግን ጥፋተኛውን ከማስቀጣት ጀምሮ ሐብቱን እስከማስመለስ የሚደርስ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህም መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡበት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የሙስና ችግር ስፋት ምን ደረጃ እንዳለ የሚመለሰው በጥናት እንደሆነ ያስታወቁት ደግሞ የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ናቸው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሙስናን ለመከላከል፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ፈጻሚዎችንም በሕግ ጥፋተኛ ለማስባል እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከሙስና የመውጫው ዋናው መንገድ አሠራሮችን ማዘመን እንደሆነ ታምኖ በርካታ ተቋማት አገልግሎትን በኦንላይን እየሰጡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ገቢዎችን፣ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድን፣ መሬትን በካዳስተር የመመዝገብ ጅምርን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡ ይህም አሠራሮች ከእጅ ንክኪ ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ ማኅበረሰቡ ለሚፈልገው መንግሥታዊ ነጻ አገልግሎት የሚጠየቀውን የእጅ መንሻ የሚያስቀር እንደሚሆን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡ ሕዝቡም አገልግሎትን በገንዘብ ከማግኘት ይልቅ በመብቱ እንዲገለገል ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ሙስና እየተፈጸመ መሆኑን ጥርጣሬ በሚያይበት ወቅት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ እና ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ማስረጃ በመሆን ሙስናን መከላከል እንደሚቻልም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ ይህንንም በትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባር ክበባትን በማቋቋም ተማሪዎች በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮችም በትውልድ ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ መገናኛ ብዙኃን በተደራሽነታቸው ልክ ስለ ሙስናን ምንነት፣ ተጽእኖ እና ሁለንተናዊ ጉዳት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ጥምረትም ሙስና ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ እነዚህ ተግባራት በእኔነት ስሜት አጠናክሮ በማስቀጠል ሙስናን መከላከል ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም