ሙስናን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!

0
86

“ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል” የተሰኜ ድርጅት ኢትዮጵያን በሙስና ካለም አገራት በ99ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የሙስና ችግር መስፋፋት ቀዳሚው ምክንያትም ከሰዎች አመለካከት ጋር የተያያዘው ኾኖ ይገኛል፡፡   “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፤ ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ…” የሚሉት አባባሎች ችግሩ ካመለካከት ዝንፈት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ይህን መሰሉ የተዛባ አመለካከት ሌቦች እንዲበረታቱ፣ ባንጻሩም ሙሰኞችን ለማጋለጥ የሚሞክሩ አካላት እንደ ምቀኛ እንዲታዩ በማድረግ ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲንሰራፋ በር ከፍቷል፡፡

ሙስና የሚያደርሰው ጥፋት ውስብስብና ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ያዳክማል፤ የሕግ የበላይነት እንዲሸረሸር ምክንያት ይሆናል፡፡ ሙስና ባለበት አገር ለአካባቢ ጎጂ የሆኑ፤ ለሕዝብም ጠቃሚ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች በጉቦና በሌሎች ብልሹ አሠራሮች ይፈቀዳሉ፤ ይከናወናሉ፡፡ በዚህ የተነሳም ሙስና የአካባቢ ጉዳት እስከማስከተል ሊደርስ ይችላል፡፡

ሙስና  የመንግሥትን አቅም በማዳከም አስፈላጊ የሆኑ የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እና የኅብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እንዳይችል ያደርገዋል፡፡ መንግሥት አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዲሁም የኅብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች መመለስ ሲሳነው ደግሞ፣ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ችግር ወደመሆን ስለሚሸጋገር በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዳይኖር  ያደርጋል፡፡

ከዚህ እውነታ በመነሳትም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ያገኜነው መረጃ እንደሚጠቁመው የሙስና ወንጀልን ለመከላከል፣ አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እና የተዘረፈውን ሐብት ለማስመለስ የክልሉ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከፍትሕ ቢሮ እና ከክልሉ ፖሊስ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማት  አገልግሎታቸውን ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ታግዘው  እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ገቢን፣ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድን፣ መሬትን በካዳስተር የመመዝገብ ጅምርን ላብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በላቡ በወዙ ማደርን የሚመርጥ፣ ባንጻሩም ያልደከመበትን ሀብት የሚጸየፍ ፈሪሃ ፈጣሪ ያደረበት ትውልድ በመገንባት ረገድ ሁሉም  ቤተ እምነቶች  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችሉ ዘንድም  ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም በተደራሽነታቸው ልክ ስለ ሙስናን ምንነት፣ ተጽእኖ እና ሁለንተናዊ ጉዳት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡

ሙስናን የመከላከል፣ አጥፊውን በሕግ የመጠየቅም ሆነ የተመዘበረውን ሀብት የማስመለስ ተግባር ላንድ ተቋም ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ እናም በጋራ ለመሥራት ስምምነት መደረጉ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መልካም ርምጃ ነው፡፡ አሠራሮችን ማዘመንም  አገልግሎት አሰጣጥን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ ማኅበረሰቡ ለሚፈልገው ነጻ አገልግሎት የሚጠየቀውን የእጅ መንሻ የሚያስቀር በመሆኑ ተቋማት አገልግሎታቸውን በዘመናዊ መንገድ ለመስጠት በጀመሩት ጥረት  መግፋት ይኖርባቸዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ሙስና እንዳይፈጸም ለመከላከልም ሆነ ተፈጽሞ ሲገኝ አጥፊውን በሕግ ለመጠየቅ፣ ብሎም የተመዘበረውን ሀብት ለማስመለስ የሕዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም  ችግሩን ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት፡፡ ሙስና እየተፈጸመ መሆኑን ሲረዳም ሆነ ጥርጣሬ ሲያድርበት  ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ እና አጥፊውን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት በንቃት መሳተፍ  ይኖርበታል፡፡

ተተኪውን ትውልድ በሥነ ምግባር አንጾ ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትም የችግሩን ምንጭ በማድረቅ ረገድ የሚጫዎተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት የሚጫዎቱት ሚና የማይተካ ስለሆነ ከተቋማቱ ጋር ለመሥራት የተጀመረው ጥረትም ሌላው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው፡፡

መገናኛ ብዙኃንም ሙስናን በመከላከል ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫዎቱ መሆናቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ እናም እነዚህ የሕዝብ እና የመንግሥት አንደበቶች  በተደራሽነታቸው ልክ ስለ ሙስናን ምንነት፣ ተጽእኖ እና ሁለንተናዊ ጉዳት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ  እየተተገበረ ያለው ቅንጅታዊ አሠራር የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here