በየአመቱ የሚካሄደው የዘንድሮው የባሕል ስፖርቶች ውድድር “ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በማእከላዊ ኢትዮጵያ ሆሳእና ከተማ ተካሂዷል፡፡
ውድድሩ በባህል ስፖርቶች ለ22ኛ ጊዜ በባህል ፌስቲቫል ለ18ኛ ጊዜም ተከናውኗል፡፡
ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት ሰባት በተከናወነው 22ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 18ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል 11 ክልሎች ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊም ሆነዋል፡፡ የትግራይ ክልል እና ሶማሌ ክልል አልተሳተፉም፡፡
ከ1380 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሲሆኑ ውድድሩ በ11 የስፖርት አይነቶች ተከናውኗል፡፡
የውድድሩ አስተናጋጅ ከተማ ሆሳእና በሁለት ቦታዎች ውድድሩን ስታስተናግድ የቤት ውስጥ ስፖርቶች በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ፣ ከቤት ውጭ የሚከናወኑትን ደግሞ በአብዬ ሄርሳ ስታድዬም አስናድታለች፡፡
ስፖርተኞች ለከፍተኛ ወጪ እንዳይዳረጉ በማሰብ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እና አዘጋጁ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ የሉዑካን ቡድን አባላትን በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ማደሪያ በማመቻቸትም ውድድሩን የተሳለጠ ማድረግ ችለዋል፡፡
በውድድሩ የመክፈቻ ቀን ተገኝተው ውድድሩን የከፈቱት የባህልና ስፖርት ሚንስቴር ስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ መክዩ መሀመድ በኢትዮጵያ ከ293 በላይ ባሕላዊ ስፖርቶች እንደሚገኙ ገልፀው ህግና ደንብ የወጣላቸው እና ውድድር የሚደረግባቸው ግን 11 ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሚንስትር ዴኤታው አዳዲስ ስፖርቶችን በመመዝገብ ህግና ስርዓቶችን በማርቀቅ ወደ ውድድር የማምጣት ሥራ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡
ከፍተኛ ፉክክር የታየባቸው ውድድሮች
ለወትሮው ቢሆን በባህል ስፖርቶች ወድድር የአማራ ክልል በፍፁም የበላይነት እንደሚያሸንፉ የሚገመት ነበር፡፡
በአማራ ክልል ከተዘጋጁት 22 ውድድሮች በ19ኙ በማሸነፉ ቅድመ ግምት እንዲያገኝ ረድቶታል፡፡
ይሁን እንጂ በዘንድሮው ውድድር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተፎካካሪ ሆነው መቅረባቸውን አሳዩ፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤት ውስጥ ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊ መሆኑንም አረጋግጠ፡፡
ኦሮሚያ ክልል በፈረስ ውድድሮች አሸናፊ ሲሆን በገና ውድድርም የወንጫ ባለቤት ሆኗል፤ የአማራ ክልል በትግል ሴቶች አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን በትግል ወንዶች ግን በአዲስ አበባ ተሸንፏል፡፡
በቀስት ውድድሮች በወንዶች አማራ ክልል አሸናፊ ሆኗል፣ በሴቶች ኦሮሚያ፣ በድብልቅ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድል አድርገዋል፡፡
የውድድሩን አጠቃላይ አሸናፊ የለየው ውድድር የኩርቦ ስፖርት ነበር፡፡
የኩርቦ ስፖርትን አማራ ክልል በፍጹም የበላይነት ሲደመድም በሁለቱም ፆታ እና በድብልቅ በማሸነፍ በመጨረሻው የውድድር ቀን አሸናፊ ሆነ፡፡ አማራ ክልል ነጥቡን 57 በማድረስ ቀዳሚ ሲሆን ከፍተኛ ፉክክር ያሳዩት ኦሮሚያ 56 አዲስ አበባ 53 ነጥብ በመያዘ ተከታትለው ጨርሰዋል፡፡
ትኩረት የሚያስፈልገው የአማራ ክልል ውጤት
አማራ ክልል ከ90 በላይ የልኡካን ቡድን አባላትን ይዞ ነበር ሆሳእና ከተማ የገባው፡፡
ሉዐካን ቡድኑ ወደ ሆሳእና ከማቅናቱ በፊት ለ10 ቀናት ብቻ ልምምድ አብሮ ሰርቷል፡፡
የውስጥ ውድድር ባለመከናወኑም አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ባለፉት ጊዜያት ስኬታቸው የተጠሩ ናቸው፡፡
ወደ ውድድር ከተገባ በኋላ በርካታ የውስጥ ውድድሮችን ያደረጉት እና ለታዳጊዎች ትኩረት በመስጠት የሰሩት አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ አዳዲስ ህፃናትን ወደ ባህል ስፖርት ከማምጣት ባለፈ በውድድሮች በልዩነት ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ይህ በቤት ውስጥ ውድድሮች ጐልቶ ታይቷል፡፡
የአማራ ክልል ተወዳዳሪዎች “የውስጥ ውድድር ካደረግን ሶሶት አመት አልፎናል” ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በዘንድሮው በወድድሮች እና ባለፉት ጊዜያት የበላይነታቸው ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ልዑካን ቡድንን የመሩት አቶ አዱኛ ይግዛው የተወዳዳሪዎችን ሀሳብ የተጋሩ ሲሆን ወቅታው የሰላም ችግር ውድድር ለማድረግ ፈታኝ በመሆኑ በክልል የባህል ስፖርት ውድድሮች ከተከናወኑ ረጅም ጊዜያት እንዳለፉ ተናግረዋል፡፡
አቶ አዱኛ አዳዲስ ተወዳዳሪዎችን ለማግኘት ውድድር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ኘሬዘዳንት አቶ አፈወርቅ ተፈራ “ውጤታችን አሸናፊ እንደሆንን የሚገልፅ ቢሆንም በብዙ ውድድሮች የበላይነት ተወስዶብናል” ብለዋል፡፡
ኘሬዘዳንቱ ታዳጊዎች ስልጠና እና ውድድር መዘርጋት ላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብዙ ተሞክሮ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
“ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ህብረብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው 18ኛውን የባህል ፌስቲቫል ባህልና እሴቶቹን በበቂ ዝግጅት በማስተዋወቅ ኦሮሚያ ክልል የዋንጫ ተሻላሚ ሆኗል፡፡
የፀባይ ዋንጫ ደቡብ ኢትዮጵያ አሸንፏል በውድድሩ የመዝጊያ ቀንም ተወዳዳሪዎች፣ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
ውድድሩም 23 ተኛውን የባህል ስፖርት ውድድርና 19ኛውን የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ሀረር ከተማ እንድታስተናግድ በመምረጥ ተዘግቷል፡፡
(ታሪኩ ዐይኔዋ)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም