የዓለም ጤና ቀን

0
123
Mother holding her newborn baby at hospital after cesarean section- Buenos Aires - Argentina

ጤናማ እናቶችና ሕጻናት የጤናማ ቤተሰብ ብሎም ማሕበረሰብ መሠረት ናቸው፡፡ እ.አ.አ ሚያዚያ 7 ቀን 2025 የሚከበረው የዓለም ጤና ቀን  የእናቶችና የአራስ ሕጻናትን ጤና መጠበቅ ትኩረቱን አድርጎ ይከበራል፡፡ የዘንድሮዉ የዓለም ጤና ቀን  “ጤናማ ጅምሮች የነገ ተስፋዎች”  በሚል መሪ ሃሳብ  ስለ እናቶች እና አራስ ሕጻናት ጤና አጠባበቅ ለአንድ ዓመት ግንዛቤ በመፍጠር ይቆያል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መንግሥታት እና በጤና ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመከላክል ጥረት እንዲያደርጉ ያግዛል። ያበረታታልም።

ከዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ድርጅቱ እና አጋሮቹ ጤናማ እርግዝናን እና ወሊድን እንዲሁም የተሻለ የድህረ ወሊድን ጤንነት ለመደገፍ ጠቃሚ መረጃዎችን በማጋራት ዓመቱን ሙሉ ይከርማሉ፡፡ እያንዳንዷ እናት እና ሕጻናት በሕይዎት እንዲቆዩ ለማድረግ ደግሞ ይህ ተግባር ወሳኝ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2020 ወደ 287 ሺህ የሚጠጉ ሴቶች በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት ሞተዋል። በዚህ ዓመት በየቀኑ 800 የሚጠጉ ሴቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነበር የሞቱት። በ2020 ከሁሉም የእናቶች ሞት 95 በመቶ የሚሆነው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት መከሰቱን ነው የዓለም የጤና ድርጅት የገለጸው፡፡

ሕጻናት ከተወለዱ በኋላ ያለው የመጀመሪያ ወር  ለህልውናቸው በጣም ወሳኝ ወቅት ነው። ይሁንና እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት እ.አ.አ በ2022 በመጀመሪያዎቹ 28 ቀናት ውስጥ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሕጻናት ሕይወታቸውን አጥተዋል። በየቀኑም ወደ ስድስት ሺህ 500 የሚጠጉ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ሞት ተከስቷል፡፡ ይህም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕጻናት ሞት 47 በመቶ ያህሉን ይይዛል።

ያም ሆኖ እ.አ.አ ከ1990 ጀምሮ ዓለም በሕፃናት ህልውና ላይ ትልቅ ዕድገት ማሳየቷን ድርጅቱ ዕወቁልኝ ብሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ1990 አምስት ሚሊዮን ከነበረው የአራስ ሕጻናት ሞት በ2022 ወደ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዝቅ ብሏል።

ሀገራት እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ የእናቶችንና የአራስ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ግብ ተቀምሮላቸዋል፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ 64 ሀገራት አስቸኳይ ርምጃ ካልወሰዱ በቀር በተጠቀሰው ጊዜ የዘላቂ ልማት ግቦችን በመፈጸም የአራስ ሕፃናትን ቅነሳን   ያሳካሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት፣ ደቡባዊ እና መካከለኛው እስያ በአራስ ሕፃናት ሞት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ በ2022 በሕይወት ከተወለዱ ከአንድ ሺህ  ሕጻናት መካከል 27 ሞት ሲመዘገብ በመካከለኛዉ እና በደቡብ እስያ ደግሞ በሕይወት ከተወለዱ አንድ ሺህ ሕጻናት ውስጥ 21ዱ ለህልፈት ተዳርገዋል። አብዛኛው የአራስ ሕጻናት ሞት 75 በመቶው የሚከሰተው በተወለዱ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡

በዚህም በዓለም ላይ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ይሞታሉ ማለት ነው።

እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ሕጻናት በተወለዱ የመጀመሪያ ወር ውስጥ የመሞት ዕድላቸው ዝቅተኛ የሟች ቁጥር ካላቸው አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ በ11 እጥፍ ይበልጣል። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው አብዛኛዎቹ አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ሞት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ እንደሚከሰት ነው፡፡

አራስ ሕጻናትን ለሞት የሚዳርጋቸው ምክንያቶች በርካታ ናቸው፡፡ እነሱም ከ37 ሳምንታት እርግዝና በፊት የተወለዱ ሕፃናት የአካል ክፍሎቻቸው ሙሉ በሙሉ ሊዳብሩ ስለማይችሉ ለሞት የተጋለጡ ናቸው፡፡ እንዲሁም ዝቅተኛ የልደት ክብደት ኖሯቸው የተወለዱ ሕፃናትም ሕይዎታቸው አደጋ ላይ ነው፡፡ አንድ ሕፃን በተወለደበት ጊዜ ወይም ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቂ ኦክስጅን ሳያገኝ ሲቀር የአንጎል ጉዳት ወይም ሞት ሊያስከትልበት ይችላል፡፡ በሕፃኑ አንገት ላይ የእምብርት መጠምጠምን እና  መታነቅን ያስከትላል፡፡ ከባድ የደም ኢንፌክሽን (ብግነት) ለአራስ ሕፃናት ሞት ዋነኛ መንስኤ ሊሆን ይችላል። የማጅራት ገትር በሽታ የአንጎል እና የአከርካሪ ኢንፌክሽን በማስከተል ለሞት ሊዳርግ ይችላል። የሳንባ ምች ወይም የሳንባ ኢንፌክሽን በተለይ ለአራስ ሕፃናት አደገኛ ነው።

ጨቅላ ሕፃናት ሲወለዱ ከአካል ክፍል መዋቅሮች መጓደል ጋር ከተወለዱ ወይም ከሌሎች የአካል ክፍሎች ችግሮች ጋር ሲወለዱ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡

አንዳንድ ሕፃናትም በምግብ እንሽርሽሪት ሥርዓታቸው ላይ እክል ያለባቸው ሆነው ከተወለዱ እና በፍጥነት ካልታከሙ ይሞታሉ። ሌላው ድንገተኛ የጨቅላ ህፃናት ሞት(SIDS) ሲሆን ይህ ከአንድ ዓመት በታች በሆኑ የጨቅላ ሕጻናት ላይ የሚከሰት የሞት አደጋ ምክንያቱ በትክክል ባይታወቅም አንዳንድ አራስ ሕጻናትን በሆድ ወይም በጎን ማስተኛት፣ የሙቀት መጨመር ወይም ቀደም ሲል ሕጻኑ የሞተ ወንድም ወይም እህት ከነበረው አደጋው ሊከሰት እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት አለማግኘት ለእናቶች እና ለአራስ ሕፃናት ሞት አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲሁም ከባድ ደም መፍሰስ (በአብዛኛው ከወሊድ በኋላ የሚከሰት)፣ ብዙውን ጊዜ ከወሊድ በኋላ በሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች፣ በእርግዝና ወቅት በሚከሰት  ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከመውለድ  ጋር የሚመጡ ችግሮች እና ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ በማስወረድ ምክንያት የእናቶች ሞት ይከሰታል፡፡

ጥራት ያለው የጤና እንክብካቤ ማግኘት ለእናቶች እና ለአራስ ሕፃናት ሞት መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በቅድመ ወሊድ እና በድህረ ወሊድ እንክብካቤ፣ በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች መውለድ  የእናቶችንና እና የአራስ ሕፃናትን በሕይዎት የመቆየት ዕድል ይጨምራል፡፡ በመሆኑም አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ ለ24 ሰዓታት  በጤና ተቋም ውስጥ መቆየት አለባቸው፡፡ ይህም የሚሆነው በጤናቸው ላይ ውስብስብ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉበት በጣም ወሳኝ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ብዙ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ከሆስፒታል ቀድመው በመውጣታቸው፣ ችግር ሲያጋጥም ተመልሶ ወደ ጤና ተቋማት ለመግባት ከዘገዩ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።

አዲስ የተወለዱ ሕፃናት  የጤና አደጋዎችን ለመቀነስ ተጨማሪ ትኩረት እና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የታመመ አዲስ የተወለደ ሕፃን በቤት ውስጥ ከታወቀ፣ ቤተሰቡ ሕፃኑን የሚንከባከበው ሆስፒታል ወይም ተቋም በማፈላለግ መረዳት አለበት።

በአጠቃላይ የእናቶችን እና የአራስ ሕጻናትን ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም ጤና ቀን መሪ ሃሳብ ግቡን እንዲመታ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ጠይቋል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here