ሰዎች ራሳቸውን ለምን ያጠፋሉ?

0
139

በመላው ዓለም በሚገኙ ወጣቶች በሦስተኛ ደረጃ የተመዘገበው  የሞት መንስኤ ራስን ማጥፋት እንደሆነ እ.አ.አ በ2022  የኢትዮጵያ ሕክምና ማሕበር በድረ-ገጹ ያወጣው   መረጃ ያሳያል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ቢያንስ 700 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉ መረጃው አመላክቷል:: ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ድርጊቱ ሚፈጸመው ከ75 በመቶ (ከሦስት አራተኛ) በላይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ነው::

በምሥራቅ አፍሪካ በየዓመቱ እራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎች ቁጥር  ከአንድ መቶ ሺህ ሕዝብ ከ5 ነጥብ 02 እስከ 15 ነጥብ 71 በመቶ (ከአምስት ሺህ እስከ 15 ሺህ) እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ማሕበሩ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ያለው ዓመታዊ ራስን የማጥፋት መጠን ደግሞ በዓመት ከአንድ መቶ ሺህ ሕዝብ ዘጠን ነጥብ 63 በመቶ (ዘጠኝ ሺህ ያህል) ሲሆን ይህም በየቀኑ 30 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ ማለት ነው።

ራስን በማጥፋት ዙሪያ በቂ በሚባል ደረጃ ጥናቶች እና ምርምሮች አለመደረጋቸው፣ ማኅበረሰቡ ስለ ጉዳዩ ያለው እውቀት ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም ራስን ማጥፋት እንደ ችግር አለመወራቱ የበርካቶች ሞት መንስኤ ሆኖ ተደብቆ እንደሚያልፍ ቢቢሲ በ2023 እ.አ.አ ያወጣው ዘገባ ያሳያል።

አንድ የቤተሰብ አባል ራሱን ሲያጠፋ “ሰዎች ምን ይሉኛል?” በሚል ፍራቻ የሞቱን መንስኤ ይደብቃል፣ አልያም ሌላ ምክንያት ለመስጠት ይሞክራል። ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። ስለጉዳዩ በግልጽ አለመወራቱ ደግሞ አንድ ሰው ራሱን ሲያጠፋ ሰዎች “ለምን?” ብለው እንዳይጠይቁና ከሌሎች ተሞክሮዎች እንዳይማሩ እንደሚያደርግ ዘገባው ጠቁሟል::

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች ውስጥ 20 ከመቶ የሚሆኑት በፀረ ተባይ ወይም በጦር መሳሪያ ወይም ራሳቸውን በመስቀል ነው።

የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት  ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው  እንደገለጹት  ከሥነ ልቦና አንጻር ሰዎች ራሳቸውን ከሚያጠፋባቸው ምክንያቶች አንዱ “እኔ የማልገባ እና የማልፈለግ ሰው ነኝ” ብለው ማሰባቸው ነው። ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋትም ገፊ   ምክንያቶች አሉ:: ለአብነት ከመርህ እና ሥርዓት አልባነት ጋር ተያይዞ  በሚደረግ ከፍተኛ ቁጥጥር  ለመኖር መሰላቸት /ኑሮን እንደ  እስር ቤት መቁጠር/  ተጠቃሽ ነው::

በሌላ መልኩ ሰዎች ራሳቸውን ማስተዳደር ሳይችሉ ሲቀሩ ሸክም የመሆን እና ያለመፈለግ ስሜት ሲፈጠርባቸው ፣ ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እና በራሳቸውም ይሁን በሌሎች ዘንድ ፋይዳ እንደሌላቸው ሲያስቡ ራስን ለማጥፋት ይነሳሳሉ::  ይህ ስሜት ደግሞ  ሁልጊዜም ከባድ  ነው::

ራሳቸውን ለማጥፋት ከሞከሩ እና ካጠፉ ሰዎች 90 ከመቶ ገደማ በተለያዩ አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮ የሚሰቃዩ ናቸው። ለምሳሌ ከድብርት ሕመም ዐበይት ምልክቶች አንዱ ራስን የማጥፋት ሃሳብ እና ሙከራ ነው።  በቤተሰብ መሃል ያሉ አለመግባባቶች፣ በልጅነት ወቅት በቤተሰብ በኩል ችላ መባል፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች፣ ቤተሰቦቻቸውን በአፍላነታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ማጣት፣ ከአሳዳጊዎቻቸው ጋር በመልካም ግንኙነት  አለማደግ … ራስን ለማጥፋት ተጋላጭ ያደርጋል::

እንደ ዘርፉ ባለሙያ ማብራሪያ ታዳጊዎች እና አፍላ ወጣቶች ችግሮችን የመፍታት ብቃታቸው በሚገባ ስላልዳበረ ራስ ማጥፋትን ከዚህ ጫና ማምለጫ አድርገው ሊጠቀሙ ይችላሉ:: እነዚህ ስንክሳሮች በአዋቂነት ዘመን በሚኖሩ ውጣ ውረዶች ከተዳፈኑ እየተገለጡ ሊረብሹ ይችላሉ::

ለተለያዩ የአዕምሮ ሕመሞችም ቆስቋሽ ምክንያቶች ሊሆኑና አለፍ ሲልም ራስን በማጥፋት ስሜት ሊናጡ ይችላሉ:: ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ራሳቸውን በመጉዳት ጭንቀት እና ንዴታቸውን ከማብረድ ባለፈ  በሌላ መንገድ  መረጋጋት አይችሉም::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ  ይህ ጉዳይ  የሰዕብና ችግር ድህረ አደጋ ሰቀቀን ሕመሞች ላይ ሊታይ ይችላል::

ዶ/ር እስጢፋኖስ እንደሚገልፁት የሰዎችን የአዕምሮ ጤና ከሚጎዱ ምክንያቶች አንዱ ማሕበራዊ ኩነቶች ናቸው::  ጦርነት፣ መፈናቀል እና አለመረጋጋት ደግሞ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው:: እነዚህን ክስተቶች ተከትሎም ሰዎችን ስጋት ላይ በመጣል እና ተስፋ  ከማስቆረጥ አለፍ ሲልም ለተጓዳኝ ሱሶች በማጋለጥ የአዕምሮ ሕመም እና ራስን ለማጥፋት ሊያጋልጡ ይችላሉ።

ሕክምናውን በተመለከተም ዶ/ር እስጢፋኖስ ሲያብራሩ በመድኃኒት በተለይም ተጓዳኝ የአዕምሮ ሕመሞችን ለማከም  የተለያዩ የሥነ ልቦና ሕክምናዎች  አሉ:: ለአብነትም ማሕበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እገዛን ፈልገው የመጡ ሰዎች ችግራቸውን በእነሱ ቦታ ሁኖ መመልከት ያሻል::

ሁሉንም ራስን የማጥፋት ምልክቶችን በአንክሮ በመመልከት እና ያለወቀሳ አዳምጦ ወደ ባለሙያ እንዲሄዱ ማድረግም ብልህነት እንደሆነ የጤና ባለሙያው ምክራቸውን ለግሰዋል::

ብዙዎቹ የመንግሥት እና የግል ሆስፒታሎች የአዕምሮ ሕክምና ስለሚሰጡ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በሚኖሩበት ወቅት ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ እንደሚያስፈልግም ዶ/ር እስጢፋኖስ አስገንዝበዋል::

ድምጻዊያኑ ዘሪቱ ከበደ፣ አብነት አጎናፍር እና ጆኒ ራጋ በጋራ በኤሊያስ መልካ አቀናባሪነት ለሕዝብ ከበቁ የጥበብ ሥራዎች መካከል “ኑር ባታምንም” የሚለውን  ሥራ ራስን ከማጥፋት ጋር በተያያዘ ጥልቅ መልዕክት እና ፍልስፍና ያለበት እንደሆነ ባለሙያው አንስተዋል:: አርቲስቶቹ የምድርን በውጣ ውረድ የታጀበ  ኑሮን ቃኝተውበታል፤ እውነት ነው ሥነ-ፍጥረት  ወደ ምድር ለመምጣት ፈቃድ ተጠይቆበት እንዳልሆነ በጥበብ ሥራቸው ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፤ እኛም ራስን ከማጥፋት ጋር አያይዘው ካነሱት  የድምጻዊያኑ ሥራ  ቀንጨብ አድርገን ማጠቃለያ አድርገናል::

ብትወድቅ ብትከፋም የያዘችህ ቤትህ ዓለም፣ ሳታሰናብት መሰናበት በራስ የለም።

መች መብቴ ብለህ ወደህ  መርጠህ መጣህባት፣ መብት ነው ብላለች አንተን ማኖር መች ከበዳት::

የዛሬ ሕይወትህ ባይሞቅም፣ ነገም ካንተ ውጭ አይደምቅም::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here