የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ

0
102

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በጋሞጐፋ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ አቅራቢያ ነው የሚገኘው – ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ::

የፓርኩ ክልል ስፋቱ 514 ኪሎ ሜትር እጥፍ ወይም ደግሞ 51400 ሄክታር ተለክቷል::

የፓርኩ ቀጠና በአባያ እና ጫሞ ኃይቆች መካከል ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 505 ኪሎ ሜትር፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ዋና ከተማ አዋሳ ደግሞ 275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው::

በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ቀጣና የሚገኝ ብዝሃህይወትን ለመጠበቅ በፓርክነት እውቅና እንዲሰጠው የተጠየቀው ከ1967 እስከ 1972 ዓ.ም ድረስ ነበር:: በኃላም በ1991 እ.አ.አ በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ድንበሮቹ ተለይተው እውቅና አግኝቷል::

የፓርኩ መገኛ ከመሬት ወለል ዝቅተኛው 1108 ሜትር ከፍተኛው 1650  ሆኖ ተለክቷል:: አማካይ ዓመታዊ የሙቀት መጠኑ 21 ዲግሪ ሴሊሽየስ ነው::

ዓመታዊ ዓማካይ የዝናብ መጠኑም 900 ሚ.ሜ ተለክቷል፤ ዝናብ የሚጥልባቸው ወራት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ያሉት  ናቸው::

የነጭሳር ፓርክ ካለው አጠቃላይ ስፋት 15% በውኃ የተሸፈነ ነው:: ለዚህም በስተሰሜን ቀጣና 1160 ሄክታር የያዘው የአባያ ኃይቅ እና በደቡብ 350 ሄክታር በተንጣለለው የጫሞ ኃይቅ መሸፈኑ ነው በአብነትነት የተጠቀሰው:: ከነዚህ የውኃ አካላት በተጨማሪ የቁልፎ እና ሰር ማሌ ወንዝን በጉያው አቅፎ ይዟል – ፓርኩ::

በፓርኩ መልካምድራዊ አቀማመጥ፣ ከፍታ ያላቸው በሳር የተሸፈኑ ሜዳዎች ይበዙበታል:: አነስተኛ ኮርብታዎቹ በቁጥቋጦ የተሸፈኑ ናቸው:: በሜዳማ እና ከፍ ባሉ ተዳፋታማ አቀበቶች ረዣዥም ቅርንጫፋቸው ሰፋፊ ዛፎች ችምችም ብለው ይታያሉ::

በፓርኩ ክልል በሚገኙ ኃይቆች እና ወንዞች ዓሳዎች እና ዓዞዎች መገኘታቸውም ተጠቁሟል::

በፓርኩ ክልል ከዱር እንስሳት አንበሳ፣ አቦሸማኔ፣ የሜዳ አህያ፣  ጉማሬ፣ የሜዳ ፍይል  እና ዝንጀሮ የሚገኙበት ሲሆን  ከሁሉም በላይ የዓዞ መገኛ ብቻ ሳይሆን መገበያያም ጭምር  ነው::

በፓርኩ 333 የአእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙም ተመዝግቧል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ ሳፋሪ ቡኪንግ እና ቪዚት ኢትዮጵያ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here