ሁለት ዓመታትን ሊያስቆጥር ቀናት የቀሩት የሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት መቋጫ ያገኘ ይመስላል፤ ለዚህ ደግሞ ድርድር ሳይሆን አንደኛዉ ተፋላሚ ወገን (የወታደራዊው መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጦር) እያስቆጠረዉ የሚገኘው ነጥብ ጦርነቱን ማን እንደሚያሸንፍ የሚጠቁም በመሆኑ ነው:: ሰሞኑን እየታየ ያለው የጦርነት ውጤት አዝማሚያም የማታ የማታ ድሉ ለሱዳን ጦር አዛዥ ለጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ያጋደለ ይመስላል::
ለዚህም ዋናው አብነት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አር ኤስ ኤፍ) ከካርቱም ማፈግፈጉን ማመኑ ነው:: የአይን እማኞችም ይህንኑ ነው ያረጋገጡት::
በሌላ በኩል ድል የተቆጠረባቸው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ መሪ ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሚቲ) “ከሱዳን ዋና ከተማ የወጣሁት ለታክቲክ ነው፤ ከካርቱም የወጣሁት ተጠናክሬ ለመመለስ ነው̋” ብለዋል:: ጄኔራሉ ከሱዳን ጦር ጋር የሚደረገው ውጊያ እንዳላበቃም ነው ያስጠነቀቁት::
አልጀዚራ እንደዘገበው ሄሜቲ በመባል የሚታወቁት ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ በቴሌግራም መተግበሪያቸው ላይ በላኩት የድምጽ መልዕክት ̋እውነት ነው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በኦምዱርማን እንደገና ቦታ ለመያዝ ከካርቱም መውጣት ነበረብን። ይህ በአመራሩ የተወሰደ የጋራ የታክቲክ ውሳኔ ነበር” ብለዋል:: “ድርድር ወይም ስምምነቶች አሉ ብለው የሚያስቡ ሁሉ ተሳስተዋል፤ ከእነሱ ጋር ስምምነትም ሆነ ውይይት የለንም:: በጦር መሣሪያ ቋንቋ ብቻ እንነጋገራለን’’ ሲሉም ነው በመልዕክታቸው የተደመጡት።
የሄሜቲ አስተያየት የመጣው የሱዳን ጦር ቀደም ሲል ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ ጥቃት ለመሰንዘር ይጠቀምበት የነበረውን በኦምዱርማን (የካርቱም መንትያ ከተማ በመባል የምትታወቀው) የሚገኘውን ማዕከል በመቆጣጠር የተገኘውን ውጤት ማጠናከሩን በቀጠለበት ወቅት ነው። አር ኤስ ኤፍ (የሄሜቲ ጦር) አሁንም በኦምዱርማን የተወሰኑ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን ጦሩ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት፣ በጦርነት የተጎዳውን አውሮፕላን ማረፊያ እና ሌሎች በከተማዋ መሃል የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ኋላ እንደማይል ቃል ገብተዋል። “ይቅር አንልም፤ አንደራደርም:: ድሉ የሚጠናቀቀው የመጨረሻው አማፂ ከሱዳን የመጨረሻ ጥግ ሲጠፋ ብቻ ነው” ብለዋል። አል – ቡርሃን የኢድ አል ፈጥርን በዓል ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት የድሉ ደስታ ሙሉ የሚሆነው የመጨረሻው አማፂ ቡድን ከሱዳን ምድር ተጠራርጎ ሲወጣ ወይም ሲወገድ ነው:: ጦርነቱ በሀገርና በሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ያነሱት ጄኔራሉ “ሰማዕቶቻችንን ቸል አንልም” ብለዋል::
ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ አል ቡርሃን በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ሲገኙ ይህ የመጀመሪያቸው ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል:: የርስ በእርስ ጦርነቱ የጀመረ ሰሞን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የካርቱምን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥሮ ነበር። የአል ቡርሃን መንግሥትም መቀመጫውን በቀይ ባሕር ወደሚገኘው ፖርት ሱዳን ለማዞር ተገዶ እንደነበር ነው ቢቢሲ በዘገባው ያስታወሰው::
ከጎርጎሮሲያኑ ሚያዚያ 2023 ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ መካከል ነበር የርስ በርስ ጦርነቱ የተጀመረው:: ጦርነቱ የተጀመረበት ዋነኛ ምክንያት የስልጣን ሽኩቻ ነበር:: በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2021 በሱዳን ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ መሪ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ሥልጣን ተጋርተው ነበር:: ሆኖም ‘ሁለት የታጠቀ ኃይል ሊኖር አይገባም፤ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በሱዳን ጦር ሥር ሊካተት ይገባል’ በሚለው ጉዳይ ሁለቱ ጄኔራሎች ሊግባቡ ባለመቻላቸው ጦር ተማዘዋል:: ሕዝቡን ለመከራ ዳርገዋል፤ ሀገሪቱንም ቁልቁል ለቀዋታል::
ግጭቱ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ በማስከተሉ በሀገሪቱ የምግብ፣ የውኃ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች እጥረት ተከስቷል። በሱዳን ያለው የውስጥ መፈናቀል በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛው እንደሆነ ነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተረጋገጠው። በጦርነቱ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ቤታቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ተገደዋል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሀገራት ሸሽተዋል። እ.አ.አ በጥቅምት 2024 እንደተረጋገጠው ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ ነበር የተሰደዱት::
በጦርነቱ ሲቪሎችን ዒላማ ያደረጉ እና በሰብዓዊ ሠራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን የሚገልጹ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ወጥተዋል። ግጭቱ በሱዳን ያለውን የፖለቲካ ክፍተት በማባባስ ወደ ሲቪል አገዛዝ የሚደረገውን ሽግግር አጨልሞታል። ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ በርካታ ሙከራዎችም አልተሳኩም።
በሀገሪቱ ቢያንስ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች በጦርነቱ ሕይዎታቸውን እንዳጡ ቢቢሲ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አመላክቷል:: ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው ደግሞ 15 ሚሊዮን ገደማ ያህል ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ የመሠረተ ልማት ተቋማት ወድመዋል:: ዜጎች ለከፋ ችግር፣ ረሃብና ሰቆቃ ተዳርገዋል፤ 30 ሚሊዮን ሱዳናዊያን ሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
በሱዳን በአምስት አካባቢዎች ረሃብ መከሰቱንና እስከ ግንቦት ወር ድረስም በተጨማሪ አምስት አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችል ዓለም አቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤፍ አር ሲ) መግለጹ ይታወቃል::
የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴዉ በሪፖርቱ በካዳህ፣ ሜሊት፣ አል ፋሺር፣ ታዊሻ እና አል ላይት በተባሉ አምስት አካባቢዎች በግንቦት ወር ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል።
ዓለም አቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤፍአርሲ) ለሱዳናውያን የከፋ ረሃብ ውስጥ መግባት የሀገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቆ ነበር:: ይሁንና የሱዳን ጦር በተመድ የሚደገፈው የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ ያወጣውን ሪፖርት ተቃውሟል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ጦር የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን ትደግፋለች በሚል ክስ ሰንዝሯል:: ይህም በተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች እና በአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ተዓማኒነት ያለው ነው ብሏል። ቀደም ሲል አሜሪካ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል በማለት ወንጅላው እንደነበር የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተፈጠረው አዲስ ጥምረት ወደ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን በመሸጋገር ክልላዊ ግጭት እንዳይፈጠር ስጋት መፍጠሩን ተንታኞች መናገራቸውን አልጀዚራ በዘገባው ጠቁሟል::
ጥምረቱ በየካቲት ወር በሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (SPLM-N) እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (አር ኤስ ኤፍ) መካከል የተፈጠረ ጥምረት ሲሆን ጥምረቱ አሁን ያለውን የአል ቡርሃንን አመራር የሚገዳደር ሊሆን እንደሚችል ነው የተገለጸው።
የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (SPLM-N) በአብደል አዚዝ አል ሂሉ የሚመራ የታጠቀ ኃይል ነው:: ከሱዳን ጦር ጋር ለዓመታት ሲዋጋ ቆይቷል:: የደቡብ ኮርዶፋን እና የብሉ ናይል ግዛቶችን የሚቆጣጠር ሲሆን ሁለቱም አካባቢዎች በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ላይ ይገኛሉ።
ተንታኞች እንዳሉት የሱዳን ጦር የደቡብ ሱዳን ሚሊሻዎችን በመደገፍ የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄን (SPLM-N) እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን (RSF) በጋራ በሚጋሩት የሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ድንበር ላይ በመዋጋት ምላሽ እየሰጠ ነው።
በተያያዘም ቻድ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን ትደግፋለች በሚል ከሱዳን ጦር በኩል ቅሬታ ቀርቦባታል:: ቻድ አር ኤስ ኤፍን እንደምትደግፍ በአደባባይ ብትክድም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ የጦር መሣሪያ ለማቅረብ ቻድን እንደምትጠቀም ዘገባዎች ያመለክታሉ:: ይህን ተከትሎም ቻድ ቀጥተኛ እርዳታ ትሰጣለች የሚል ውንጀላ ከሱዳን ቀርቦባታል። ውንጀላው ተባብሶም አንድ የሱዳን ከፍተኛ ጄኔራል በቻድ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝተዋል:: ቻድም ዛቻውን “የጦርነት አዋጅ” በማለት የጠራችው ሲሆን በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ምላሽ እሰጣለሁ ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል::
ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ በሱዳን ያለው ጦርነት ተባብሶ ቀጣናዊ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል::
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም