ኢንቨስትመንት ምን ምቹ ሁኔታ ይፈልጋል?

0
123

ኢትዮጵያ ሰፊ አና  ሁሉን አብቃይ ለም መሬትን ከምቹ የአየር ንብረት ጋር አጣምራ ይዛለች፡፡ ይህም ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት እንድትሰጥ ሲያደርጋት የዘርፉ ከ80 በመቶ በላይ ከውጭ ከተላኩ ምርቶች/የኤክስፖርት/ ገቢ ማግኛነቱ እና የ85 በመቶ የሥራ ዕድል መፍጠሪያነቱ ለኢንቨስትመንቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መነቃቃት ከፍተኛውን አበርክቶ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እሴትን ጨምሮ ለማቅረብ፤ ለዚህም ሁሉንም ጥሬ ግብዓቶች ተጠቅመው ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ሁኔታዎችን እያመቻቸች ትገኛለች፡፡ በተለያዩ ክልሎች የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትርያል ፓርክ ግንባታ፣ ከኀይል አቅርቦት መቆራረጥ ጋር የተገናኘውን የዘርፉን ችግር ለመፍታት የኅይል ማከፋፈያ ግንባታ ማከናወን እና ሌሎችም ጎታች ማነቆዎችን በቴክኖሎጂ ለመፍታት እየተከናወኑ  ያሉ ሥራዎች ለትኩረቱ ማሳያዎች ሆነው ይነሳሉ፡፡

ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በግጭት ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል መንግስትም ለዘላቂ ሰላም ሰላማዊ አማራጮች እንዲፈጠሩ እያከናወነ  ካለው ሥራ ጎን ለጎን የክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞኗ ኮምቦልቻ ከተማ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ካሉ አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 124 ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ከተማዋ ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ ገለጻ ከእነዚህ ውስጥ 57ቱ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች  ሲሆኑ፡ ሌሎቹ በአነስተኛ ደረጃ የሚፈረጁ ናቸው፡፡

ፋብሪካዎቹ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈ ሀገርን ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እስከ መታደግ የሚደርስ አበርክቶ እየተወጡ መሆኑን ከንቲባው ማሳያዎችን እያነሱ ያስረዳሉ፡፡ ከተማዋ ለኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት በኢንዱስትሪ መንደርነት እንድትታወቅ ከማድረጉም በላይ ለሀገር ውስጥ ከፍተኛ ተኪ ምርት እየተመረተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተተከናወነው ሥራ በ2016 በጀት ዓመት 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ባለፈው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከተቻለው ምርት ውስጥ 48 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከ10 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውም ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሐብቶች ኮምቦልቻን ማደጊያቸው እና በሀገሪቱ አሻራቸውን ማሳረፊያ ምርጫቸው እንዲያደርጉ ከንቲባው ጥሪ አድርገዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም የኢንቨስትመንት ቦታን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት በከፍተኛ ትጋት ላይ ይገኛል፡፡  “ምን ምቹ ሁኔታ አለ?” ብለው ለሚጠይቁ ባለሐብቶችም  አጥጋቢ ምላሽ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደርም እምቅ ሐብቶችን በመለየት እና በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ እና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ቡድን መሪ አበራ ገበየሁ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ሆልቲካልቸር እና የአገልግሎት ዘርፍ ባለሐብቶች እንዲሠማሩባቸው የተለዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ናቸው፡፡

በ2017 ዓ.ም በአዲስ እና በነባር 202 ባለሐብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ ምልመላ መደረጉን አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 67 ባለሐብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህም ለስድስት ሺህ 138 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ታምኗል፡፡ ነባሮችን በማጠናከር፣ ሥራ ያቆሙትን ወደ ሥራ በመመለስ እና አዳዲሶችን ወደ ምርት በማስገባት ለ334 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አቶ አበራ ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ 22 ፋብሪካዎች ተኪ ምርት በማምረት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡ እነዚህም አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አቶ አበራ ጠቁመዋል፡፡

አሁንም ብሄረሰብ አስተዳደሩን ማደጊያቸው፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና ሀገርን ከከፍተኛ ወጭ መታደግ በሚያስችሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ቀዳሚ መዳረሻቸው አድርገው ለሚመጡ አልሚዎች በቂ ቦታ ማዘጋጀቱን አቶ አበራ አስታውቀዋል። ነገር ግን የኅይል ማነስ እና መቆራረጥ የነባር እና የአዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ፈተና ሆኖ ዛሬም ጥያቄው መቀጠሉን አስታውቀዋል። የኅይል ችግሩ ባለሐብቶች የወሰዱትን ቦታ በወቅቱ አልምተው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዳይወጡ ከማድረጉም በላይ መምሪያው ባለሐብቶች የወሰዱትን ቦታ ለታለመላቸው አላማ ማዋል አለማዋላቸውን ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል እክል እንደሆነበት አስታውቀዋል።  ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አቶ አበራ ያነሱት ፋብሪካዎች ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ እንዲሠሩ  የመብራት ኀይል ምክረ ሐሳብ እያቀረበ መሆኑን በማስታወቅ ነው፡፡ ይህንንም ሰበብ በማድረግ ብዙ ባለሐብቶች ግንባታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዘግተው መቀመጣቸውን ጠቁመዉ ነገር ግን መምሪያው በእርምት እርምጃ ለማስተካከል እንደሚሠራ  ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ የሰላም ሁኔታው ደግሞ ሌላው የኢንቨስትመንቱ ማነቆ መሆኑን ሃላፊዉ አንስተዋል። በብሄረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ ፋብሪካዎች ጥሬ ግብዓት በአብዛኛው የሚያገኙት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ከጎንደር አካባቢዎች በመሆኑ የሰላም ችግሩ የፈጠረው ስጋት ፋብሪካዎች ዘላቂነት ባለው መንገድ ወደማምረት እንዳይገቡ እያደረጋቸው ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በነባር እና አዲስ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ግምገማ እና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት የተገኙት የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ ክልሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ማሰማራት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማበረታታት የክልሉ መንግሥት በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች በ3 ሺህ 260 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ዞን በመከለል 27 ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ከ2014 ዓ.ም ወዲህ 510 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደ ምርት መግባታቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ባለፉት ወራት ብቻ 111 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መሸጋገራቸው ተመላክቷል፡፡ የመሠረተ ልማት መማሟላት እና በዘርፉ የሚታዩ ሌሎች ችግሮችን ተከታትሎ መፍታት መቻሉ ደግሞ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች መነቃቃት ዋና ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች መነቃቃት ምን ያስገኘው ለውጥ አለ? የሚለውንም መመለስ ይገባል፡፡ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በ2014 በጀት ዓመት ከነበረው 49 ነጥብ 4 በመቶ አሁን ላይ ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ጫና ማቃለል ይችላል፡፡ ከ91 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አሁን ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል፡፡ ለዚህም በውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ባለሐብቶች ቀዳሚ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆነው በአርአያነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተሞክሮን መቅሰም ተገቢ ነው፡፡

ኢንቨስትመንትን የዕድገታቸው ምሰሶ አድርገው የሠሩ ሀገራት የተረጋጋ እና ሊገመት የሚችል የንግድ አካባቢን የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አልሚዎችን ለመሳብ እንደ ምቹ አጋጣሚ መጠቀማቸውን የህንዱ ጃዬን ዩኒቨርሲቲ (jainuniversity.ac.in) የመረጃ አውታር አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የኢንዱስትሪዎችን ባህሪ ለይቶ በጥሬ እቃ ግብዓት እንዳይፈተኑ ምርቶችን ቀጥታ ከአምራቾች እንዲረከቡ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ መረጃው አመላክቷል፡፡ ይህም የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በማድረግ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል፡፡

ሃገራቱ ፖለቲካዊ መረጋጋትን ሌላው ለኢንቨስትመታቸው ዕድገት አድርገው ተጠቅመዋል፡፡ ይህም ባለሐብቶች በሚያለሙበት አካባቢ እምነት ኖሯቸው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሠማሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራው በዘላቂነት እንዲቀጥል፣ ወጥ የሆነ ምርታማነትን በማረጋገጥ በምርት አቅርቦት ሊያጋጥም የሚችልን የኑሮ ውድነት ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡

ከሌሎች ሀገራት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከባለሀብቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ደግሞ ጠንካራ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመፍጠር ብሎም ለማበረታታ ተጠቅመውበታል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የሀገር ገጽታ ግንባታ ዋናው መዳረሻ ይሆናል፡፡

ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ደግሞ ሀገርን ለባለሐብቶች ብቸኛ መዳረሻ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም አሁን ያሉትን ልዩነቶች በንግግር እና ድርድር ለመፍታት ቁርጠኝነትን ማሳየት ይገባል፡፡ ያኔ ኢንቨስትመንቱ ይዟቸው በሚመጣቸው ዕድሎች ሥራ አጥነትን በእጅጉ መቀነስ፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ዜጎችን ከፈታኝ ሕይወት እንዲወጡ ማድረግ እንደሚቻል መረጃው አመላክቷል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here