አርሶ አደሮች በስብጥር ግብርና ተጠቃሚ ሆነዋል

0
91

የመስኖ አውታርን በመጠቀም በአንድ ማሳ ውስጥ ስብጥር ግብርናን በመተግበራቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የውኃ እና መሬት ሀብት ጥናት እና ምርምር ማዕከል ደግሞ የዝናብ ውኃን ሳይጠብቁ በመስኖ ልማት በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ፣ የስብጥር ግብርናንም እንዲተገብሩ እንዳገዛቸው ጠቁመዋል፡፡

በወረዳው ቆጋ የመስኖ አውታርን ተጠቅመው በአንድ ማሳ ላይ ስብጥር ግብርናን በመተግበር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ የውኃና መሬት ሀብት ማዕከል /ዋተር ዴቭ/ በተለያዩ ጊዜያት ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል።

በቆጋ መስኖ ልማት በግብርና ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ዳሳሽ ደምል አንዷ ናቸው፡፡ የመስኖ ኘሮጀክቱ ወደ ልማት ከመግባቱ አስቀድሞ የዝናብ ውኃን ጠብቀው ያመርቱ እንደነበር አስታውሰዋል፤ በአሁኑ ወቅት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ባደረገላቸው ድጋፍ ደግሞ  በመስኖ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሯ እንዳሉት ከዚህ በፊት የክረምት ወራትን ጠብቀው ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍና የመሳሰሉ ሰብሎችን ያመርቱ ነበር፤ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከሆኑ በኋላ ደግሞ ቋሚ ፍራፍሬና አትክልቶችን በማልማት ተጨማሪ ጥቅም እያገኙ ነው፡፡

ሌላዋ በስብጥር ግብርና ዙሪያ  ያገኙትን ስልጠና ወደ ተግባር በመቀየር በአቦካዶ እና በቡና ተክል ውስጥ ቅመማ ቅመሞችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ወርቅነሽ አበረ ናቸው፡፡ አርሶ አደሯ እንደተናገሩት በቋሚ ፍራፍሬ ልማት ውስጥ ኮረሪማ፣ ጤናዳም እና ዝንጅብል  በማሰባጠር እያለሙ ነው፡፡

“ያለን መሬት በጣም ውስን ነው፤ በመሆኑም አንድን ማሳ ለአንድ የልማት አይነት ብቻ ማዋል ሀብትን ማባከን ነው፡፡ አሁን ባገኘሁት ግንዛቤ የስብጥር ግብርናን በመተግበር በአንድ ማሳ ላይ አቦካዶ ተክልን እጠቀማለሁ፡፡ በስሩ ደግሞ ሰብሎችን አትክልቶችንና ቅመማ ቅመሞችን በማልማት ተጠቃሚ ሆኛለሁ” ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ዘውዱ ወርቁ ናቸው፡፡

የጥናት እና ምርምር ማዕከሉ ለዓመታት የአርሶ አደሮችን የመስኖ አጠቃቀም ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አርሶ አደሮችም በቋሚ ተክሎቻቸው ውስጥ ሌሎች ሰብሎችን እና አትክልቶችን እንዲሁም ቅመማ ቅመሞችን አሰባጥረው ማልማትን እንዲለማመዱ ስልጠና በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረጉን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

በሰሜን ሜጫ ወረዳ የቀበሌ ሰብል ልማት ባለሙያ ሻሽቱ ጫኔ የስብጥር ግብርና ልማትን አስመልክቶ በሰለጠኑ አርሶ አደሮች ላይ ተግባራዊ ለውጥ መታየቱን ለአሚኮ አስረድተዋል፡፡ ልማቱ ወደ ሌሎች ከባቢዎችና አርሶ አደሮች መስፋፋት እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡

የውኃና መሬት ሃብት ስልጠና እና ምርምር ማዕከል ም/ዳይሬክተር ጠና አላምረው (ዶ/ር) ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች በሰጡት የአቅም ግንባታ ሥራ ሰብልን በስብጥር ማልማት ልማድ ሆኗል ብለዋል፡፡

በስብጥር ግብርና ልማት በተፈጥሮ ማዳበርያ ዝግጅትና በውኃ አጠቃቀም ቆጋን የተሞክሮ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ ይዞ ከአርሶ አደሮች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ማዕከሉ አስታውቋል።

(እያያው ተስፋሁን)

በኲር የመጋቢት 29  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here