የባህር ዳር ከተማን ለማዘመን እየተከናወነ ላለው የግንባታ ተግባር የልማት ተነሺዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።
በከተማዋ ከዋተር ፍሮንት እስከ ድብ አንበሳ ሆቴል ለሚገነባው አስፋልት መንገድ 138 የቀበሌ ቤት ሲኖሩ ለቆዩ የልማት ተነሺዋች በነፍስ ወከፍ 100 ካሬ ሜትር የቤት መስሪያ ቦታ እጣ የማውጣት መረሃ-ግብር ተከናውኗል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር መሰረተ ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የባህር ዳር ከተማን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ይበልጥ ምቹ ማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
በከተማዋ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን ሦስት ኪሎ ሜትሩን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማቱ በተለያየ አቅጣጫ የጣና ሀይቅን በመክፈት ንጹህ አየር ወደ ከተማዋ እንዲገባና ሃይቁን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ከዋተር ፍሮንት-ድብ አንበሳ ሆቴል 40 ሜትር ስፋት ያለው ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ በመገንባት ተጨማሪ የጣና ሀይቅ መዳረሻ የመክፈት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመንገድ ከፈታው ላይ በቀበሌ ቤት ሲኖሩ የቆዩ የልማት ተነሺዎች ለእያንዳንዳቸው የ100 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታና ፕላን ተሰርቶ ለመስጠት ዛሬ እጣ የማውጣት ስራ ተከናውኗል።
የልማት ተነሺዎች ከደሳሳ ቤት ወጥተው የራሳቸውን የተሻለ ቤት በመገንባት ወደ ሚኖሩበት የባለቤትነት መብት በመሸጋገራቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
እያደገ የመጣውን ፕሮጀክትን ባጭር ጊዜ የመገንባት አቅም በመጠቀም መንገዱን በጥራት በማስገንባት ለህዝብ ጥቅም እንደሚያውሉ አቶ ተሻገር ለኢዜአ አስታውቀዋል።
ከልማት ተነሺዎች መካከል ወይዘሮ የሺ ዋርካው፤ ከተማ አስተዳደሩ ቤት የመስሪያ ቦታ ባለቤት እንዲሆኑ በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበዋል።
የባህርዳር ከተማ ልማት የጋራችን በመሆኑ ሁላችንም ልንተባበርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
እኔ ከቀበሌ ቤት ወጥቼ መሸጥ፣ መለወጥና ተበድሬ መስራት የምችልበት ቦታ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል ያሉት ደግሞ ሌለኛዋ የልማት ተነሺ ወይዘሮ አድና በላይ ናቸው።
የከተማዋ ልማት የሁሉንም መልካም ፍቃድ የሚሻ መሆኑን ገልጸው፤ እርሳቸው ለከተማዋ ልማት ከኖሩበት ቤት መልቀቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም