ጤናማ ምግብ የሰውነትን ደኅንነት እና ኃይልን ለመጠበቅ የሚያስፈልጉትን ንጥረ ነገሮች የሚያቀርቡ ናቸው። ውኃ፣ ካርቦሃይድሬት፣ ስብ፣ ፕሮቲን፣ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት ደግሞ ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብን የሚፈጥሩ ቁልፍ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡
በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ከአምሳ አምስት ቀናት ጾም በኋላ የፊታችን እሁድ (ሚያዚያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም) የትንሳኤ በዓል ይከበራል፡፡ በዓላትን ተከትሎ ብዙዎች ከወትሮው በተለዬ ማዕዳቸው ይቀየራል፡፡ በበዓላት ወቅት ኢትዮጵያዊያን ስጋ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ የዶሮ፣ የበግ፣ የፍየል፣ የበሬ ወይም የላም ስጋ፣ ቅቤ እና ወተት (የእንስሳት ተዋጽኦ) በየቤቱ አይጠፋም፡፡
እንደሚታወቀው አጽዋማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት ቅባት የበዛባቸውን እና መሰል ምግቦችን መመገብ እንዲሁም የአልኮል መጠጦችንና መጠጣት የተለመደ ነው።
እንዲሁም በዓላትን ምክንያት በማድረግ ጎረቤት ከጎረቤቱ፣ ዘመድ ከዘመዱ ይጠያየቃል፤ እንኳን አደረሳችሁም ይባባላል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ከቤት ጠግቦ ቢወጣም “ብሉ እንጂ፣ በዓል እኮ ነው እየተባለ የሞላውን ሆድ ማስጨነቅ የተለመደ ነው፡፡ መጠያየቁ እና ብሉልኝ ጠጡልኝ መባባሉ የሚያኮራ እና የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም ይዞት የሚመጣው መዘዝ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ ሰውነታችን ደግሞ ለበርካታ ቀናት በጾም ስላሳለፈ እና ከቅባት ርቆ ስለቆየ የበዓል ወቅት አመጋገብ ጥንቃቄ ካልተደረገበት መዘዝን ያስከትላል፡፡ ታዲያ የበዓል ጊዜ አመጋገባችን ምን መሆን አለበት በሚል ከስነ – ምግብ ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ባለሙያዋ ዕጩ ዶክተር (በስነ – ምግብ) ሜሮን ወርቁ ይባላሉ፤ በምኒልክ II የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ናቸው፡፡ ጤነኛ አመጋገብ ምንድን ነው ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንዲህ ነበር የመለሱልን፡፡ አንድ ሰው ጤናማ አመጋገብ ተመገበ የሚባለው በአንደኛ ደረጃ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን ሲመገብ፣ ሁለተኛ ለሰውነት የሚያስፈልገውን ትክክለኛውን መጠን በዕድሜ እና በሰውነት እንቅስቃሴ መሠረት ሲመገብ እና በሦስተኛ ደረጃም ለሰውነት ጠቃሚ ያልሆነውን ለአብነትም ቅባታማ እና ስኳርን ቀንሶ ሲመገብ ነው፡፡
የስነ ምግብ ባለሙያዋ እንደሚሉት እ.አ.አ በ2022 በኢትዮጵያ የምግብ አመጋገብ መመሪያ ይፋ ተደርጓል፡፡ በመመሪያው መሠረትም አንድ ሰው ጤናማ አመጋገብ ተመገበ የሚባለው በአንድ ጊዜ የምግብ ፕሮግራሙ ላይ (ምሳ፣ ቁርስ ወይም እራት ሊሆን ይችላል) ቢያንስ አራት የተለያዩ የምግብ ዘሮችን መመገብ ሲችል ነው፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ቀን የምግብ ሰዓት ስድስት የምግብ ዘሮችን እና አይነቶችን ማካተት ሲችል ነው፡፡ እነሱም የእህል፣ የጥራጥሬ፣ የቅባት (ተልባ፣ ሱፍ፣ …)፣ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የዘይት ዘሮችን ሲያካትት ነው፡፡ ከእነዚህ የምግብ አይነቶች አራቱን በአንድ ጊዜ ወይም በአንድ ቀን ደግሞ ስድስቱን ማካተት ሲችል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የስነ – ምግብ ባለሙያዋ ሜሮን ወርቁ እንዳሉት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል መፈረጅ ባይቻልም አብዛኛው ሕብረተሰብ በበዓላት ወቅት የእንስሳትን ተዋጽኦ እና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በብዛት ይመገባል፡፡ በመሆኑም የበዓል ወቅት አመጋገብ ጤናማ አመጋገብ ስላልሆነ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመክራሉ፡፡ ባለሙያዋ እንዳሉት በበዓላት ጊዜ የስጋ ተዋጽኦ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ የእህልና የጥራጥሬ ዘሮችን ማዕዳችን ላይ ማካተት ጠቃሚ ነው፡፡
እንደ ስነ ምግብ ባለሙያዋ ማብራሪያ ጤናማ አመጋገብ የማይመገብ ሰው በቂ የሆነ የማይክሮ ኒውትረንት (በአነስተኛ መጠን ሰውነታችን የሚፈልጋቸው ንጥረ ነገሮች) አያገኝም፡፡ በዚሕም ሕጻናት የመቀጨጭ እና መቀንጨር ያጋጥማቸዋል፡፡ ከአካላዊ ጉዳቱ ባለፈ ለአዕምሯዊ ጉዳትም ይዳረጋሉ፡፡ በሺታ የመከላከል አቅምንም ያዳክማል፡፡ በተቃራኒው ከመጠን በላይ መመገብ ደግሞ ለደም ግፊት እና ለስኳር በሽታዎች እንደሚያጋልጡ ባለሙያዋ አስገንዝበዋል፡፡
የስነ- ምግብ ባለሙያዋ እንደሚሉት በበዓላት ጊዜ አልኮል እና ጣፋጭ ምግቦች ለጤና ጎጂ በመሆናቸው ባይወሰዱ ይመከራል፡፡ እንዲሁም ጥሬ ስጋን መመገብ ለተለያዩ በሺታዎች ስለሚዳርግ ሰዎች ከመመገብ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡ ምግብን ለብዙ ሰዓታት ማብሰልም በምግቡ ውስጥ ያለውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ስለሚያጠፋው ይህ ሁኔታ መስተካከል ይገባዋል፡፡ በተለይ ዶሮ ሲሠራ ዘይትን ለብዙ ሰዓት ማንተክተክ እና ማብሰል ለጤና ጠንቅ እንደሆነ ነው የስነ ምግብ ባለሙያዋ ያስረዱት፡፡ እንዲሁም ሸክላ ጥብስ አሠራሩ ጤነኛ ስላለሆነ ሰዎች ይህን ምግብ ከመመገብ መቆጠብ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ውኃን በብዛት መጠጣት ለጤና ጠቃሚ በመሆኑ ከአልኮክል ይልቅ ሕብረተሰቡ ውኃን በብዛት ቢጠጣ እንደሚያተርፍ ጠቁመዋል፡፡
ሆዳችን ከሚችለው በላይ እንዲሸከም ማድረግ፣ ከመጠን በላይ መመገብ፣ ቅባት የበዛበትን ምግብ መደጋገም፣ የእንስሳት ተዋጽኦን ማብዛት እና መሰል አመጋብ ለምግብ እንሽርሽሪት መታወክ ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡ በተለይ በበዓላት ወቅት መሰል አመጋገብ ይዘወተራል፤ ሰውነታችን ደግሞ ከቅባት ርቆ የቆዬ ነው፡፡ በመሆኑም በበዓላት ወቅት በብዛት የሚከሰቱ ሕመሞች ከአመጋብ ጋር የሚከሰቱ መሆናቸውን በማንሳት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉ ነው የስነ ምግብ ባለሙያዋ ያስገነዘቡት፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም