በኢትዮጵያ እንደሌሎች መሰረታዊ መብቶች ሁሉ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለንብረት መብት እውቅና በመስጠት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በዚሁ መሰረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት፣ ንብረት የመያዝና በንብረቱ የመጠቀም፣ የሌሎችን መብት ሳይቃረን ንብረቱን የማስተላለፍ መብቶችን ሕገ መንግሥቱ አጎናጽፎታል፡፡ የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ለንብረቱ ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ እንደሚችልም በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አቃቢ ሕግ አቶ ዘላለም ከፋለ አብራርተዋል፡፡
የንብረት ሕግን እና የንብረት መብትን በተመለከተም አቶ ዘላለም እንዳሉት ንብረት እና ሕጉን ለመረዳት ንብረት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ተገቢ ነው:: የንብረት ትርጉሙም የራስ የሆነ ነገር ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ፍትሐብሄር ሕግ ስለንብረት ምንነት ያስቀመጠው ትርጉም ባይኖርም ከተለያዩ ጽሑፎች እና ስለንብረት ሕግ ከሚደነግገው የፍትሐብሄር ሕግ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ነገር ንብረት ለመባል በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል መሆን አለበት፡፡ ይህ በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ነገር ጠቃሚነት ያለው መሆን አለበት። በአጠቃላይ ንብረት ማለት በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና ዋጋ ያለው ማለት ነው።
ንብረት ማግኘት የሚቻለው በአራት አይነት መንገዶች ነው፡፡ እነዚህም በይዞታ፣ በግዥ፣ በስጦታ እና በውርስ እንደሆነ የአቃቢ ሕግ ባለሙያው ገልፀዋል፡፡ ለንብረቱ የባለቤትነት መብት በሕግ አግባብ ያገኘ ሰው የመሸጥ ፣ የማስተላለፍ እና የማውረስ መብት አብሮ ይኖራል፡፡
የንብረት ዓይነቶች ደግሞ ተንቀሳቃሽ ፣ ልዩ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ናቸው፡፡ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚባሉት ቴፕ፣ መጽሐፍ ፣ ቦርሳና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ንብረቶች ባለመብት ነኝ ለማለት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሳያስፈልጋቸው ይዞ መገኘት ብቻ በቂ ይሆናል፡፡
ልዩ ተንቀሳቃሽ የምንለው ደግሞ እንደ መኪና ያለ ንብረት ሲሆን ይህንን ንብረት ይዞ መገኘት ብቻ ግን ባለቤትነትን ስለማይገልፅ ማረጋገጫ ሊብሬ ሊኖረው ይገባል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ስንል ደግሞ መብቱን በመያዝ (ይዞታ) ፣ ስጦታም ፣ ግዥም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በሥሙ የተመዘገበ ሰነድ ያለው መሆን ይገባዋል፡፡
የአንድ ንብረት ባለቤት በንብረቱ ላይ ያለው ሥልጣን መሸጥ፣ ራሱ መገልገል፣ ለሌላ ለሦስተኛ ወገን በሥጦታ እና በውርስ ማስተላለፍ ይችላል፡፡ አንድ ሰው ንብረቱን ማስተላለፍ በፈለገበት ጊዜ ደግሞ በሥሙ የተመዘገበውን ቤት በሽያጭ የማስተላለፍ ከፈለገ ንብረቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ፣ መኪና ከሆነ ሊብሬ ማቅረብ እንደሚገባ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡ ለአብነት በሽያጭ የሚተላለፈው ቤት ከሆነ ባለቤትነትን ከሚረጋገጥበት ሰነድ ተጨማሪ በቀበሌው ቤቱ (ቦታው) መኖሩ፣ ከዕዳ ነጻ መሆኑ እና ለሌላ ሰው አለመተላለፉ መረጋገጥ አለበት፡፡
በተንቀሳቃሽ እና በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች መካከል ያሉ ልዩነቶች ሀብት ከሚገኝበት መንገድ አንጻር ንብረቶች የሚንቀሳቀሱ ወይም የማይንቀሳቀሱ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ በባለቤትነትም ሆነ በባለይዞታነት ለመያዝ ጥቅም ላይ የሚውሉባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት ተንቀሳቃሽ የሆኑ ንብረቶችን ባለቤት ለመሆን በማሰብ በማንኛውም ሕጋዊ መንገድ በእጃቸው ያደረጉ ሰዎች የንብረቱ ባለቤት ወይም ባለይዞታ መሆን እንደሚችሉ በፍትሐብሄር በአንቀጽ 1151 ስር ተመልክቷል፡፡
ሰዎች በይዞታ በሚይዙት ንብረት ላይ በብቸኝነት የማዘዝ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ይህ መብት ከባለሀብትነት መብት አንጻር ፍጹም ባለመሆኑ ንብረቱን በእጅ በማድረግ የመገልገል እና ፍሬውን የመጠቀም መብት ካልሆነ በስተቀር ዋነኛውን ንብረት በሽያጭም ሆነ በሌላ መንገድ ለሌላ ወገን አሳልፎ የመስጠት ወይም የመሸጥ መብት አይኖራቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በይዞታ የሚያዙ ንብረቶች የሌላ ሰው መብት በውስጣቸው ስለሚኖር ነው፡፡ ለምሳሌ አበዳሪ ለማስያዣነት የያዘውን ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚይዘው በውላቸው መሰረት እዳው ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ በመሆኑ እዳው ተከፍሎ ሳያልቅ ባለሀብቱ ንብረቱን የመሸጥ መብት አይኖረውም፡፡
በሌላ በኩል አንድ ንብረት /ሕንጻ/ በስሙ ግብር እየከፈለ በይዞታው ስር ያቆየ ሰው 15 አመት እስካልሞላው ድረስ ባለመብት ሊጠይቅ እና ሊወስድ እንደሚችል በሕግ ተቀምጧል፡፡ ንብረቱን ከመጠቀም በዘለለም ሊሸጠው እንደማይችል አቃቢ ሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም