ርቀት ያልገደበው ጥምረት

0
127

ኢራን ደገፍ ከሚባሉት በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ክልል ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ርቀት ያልገደበው የትግል ጥምረት በፈረንጆቹ አጠራር ‘አክሲስ ኦፍ ረዚዝታንስ’ በአማርኛ የአርበኝነት ጥምረት ልንለው የሚችል ትስስር  በኢራን አጋርነት ተፈጥሯል።

በኢራን የተካሄደው የ1971 ዓ.ም አብዮት የፈጠረው አዲሱ አስተዳዳር በአሜሪካ እና እስራኤል ዙሪያ  የተከተለው የውጭ ፖሊሲ ፍፁም የመካከለኛው ምሥራቅን ፖለቲካዊ እውነታ ለውጦታል። ኢራን ከአብዮቱ በፊት ወዳጆቿ የነበሩትን አሜሪካን እና እስራኤልን በጠላትነት በመፈረጅ ከምእራባውያኑ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች። ይህም ኢራንን እና አጋሮቿን በማያባራ የግጭት እና የትርምስ አዙሪት ውስጥ አስገብቷቸዋል።

በሌላ በኩል በ1972 ዓ.ም ሳዳም መሯ ኢራቅ በኢራን ላይ የፈፀመችው ወረራ ኢራንን እና አጋሮቿን ተከታታይነት ባላቸው የደህንነት፣ የኢኮኖሚያዊ እና የማህበረሰባዊ ስጋት እና ችግሮች እንዲከበቡ አስተዋፅኦ አድርጓል። ኢራን እስራኤልን እንደ ትልቅ ስጋት ስለቆጠረች የቅድመ መከላከል ስትራተጂ ተፈፃሚ ማድረግ ጀመረች። በመሆኑም ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ለመፋለም የታጠቁ ቡድኖችን ማስታጠቅ እና በጋራ አላማ የማደራጀት ተነሳሽነቱን ወስዳ በየአጋጣሚው ከሚነሱ የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሀገራት ታጣቂዎች ጋር ግንኙነቷን ፈጥራ እስከዛሬ በህቡእ ትሰራለች። ከሊባኖሱ ሂዝቦላህ፣ ከኢራቁ ታጣቂ ቡድን እና ከየመኑ ሐውቲ ጀርባ ኢራን በስውር አለች ተብላ ትታማለች።

በ1974 ዓ.ም እስራኤል ሊባኖስን መውረሯን ተከትሎ የተመሰረተው ሂዝቦላህ በኢራን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያገኘ በቀጣናው ባለ ፈርጣማ ክንድ አማፂ እስከመሆን የተደራጀ የጥምረቱ አንደኛው አካል ነው። ይህ ታጣቂ ቡድን ሊባኖስን ከእስራኤል ለመታደግ በሚል አላማ በተጨማሪ ፀረ አሜሪካ እና እስራኤል አቋም ወደሚል አስፍቷል። ባለፈው ሳምንት በታሪክ አምድ ክፍል አንድ ዝግጅት ላይ የሂዝቦላን አመሰራረት በተመለከተ አስነብበን ነበር ለቀጣዩ በቀጠሮ የተለያየነው፣ አሁን ቀጣዩን ክፍል እነሆ።

የየመኑ ሐውቲ

ሐውቲ፣ የየመን ታጣቂ ቡድን በ1970ዎቹ የተመሰረተ ሲሆን ስሙም ከቡድኑ መስራች ሁሴን በድረዲን ሐውቲ የተወሰደ ነው። ሐውቲዎች፣ ዛይዲ የተባሉ የየመን  ሺያ እስላማዊ የፖለቲካ እና ወታደራዊ  ቡድን ነው። አንሳር አላህ “የአምላክ ወዳጆች” በሚል መደበኛ ስም የሚታወቁት ሐውቲዎች ድርጅት ሐውቲ በ1980ዎቹ የመን ውስጥ የተመሰረተ ድርጅት ነው።

በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ሐውቲ በሰብአዊ መብት ረገጣ፣ ንፁሃንን ኢላማ ማድረግን እና ሕፃናትን ለውትድርና በመጠቀም ረገድ አለማቀፍ ውግዘት ደርሶበታል። በአንዳንድ ሀገራት ዘንድ ሐውቲ እንደ አሸባሪ የተፈረጀ ቡድን ነው። ይሁን እንጂ በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት ይነገራል። በመሆኑም ሐውቲዎች የኢራን መራሹ አክሲስ ኦፍ ረዚዝታንስ አካል እንደሆኑ በስፋት ይታሰብ ነበር።

በዛይዲ ሀይማኖታዊ መሪው ሁሴን አል ሁቲ መሪነት ሐውቲ በወቅቱ በሙስና እና ከሳውዲ አረቢያ እና አሜሪካ ጋር ወዳጅ በመሆናቸው ይኮነኑ የነበሩትን የቀድሞውን የየመን ፕሬዚደንት  አሊ አብዱላህ ሳላህን የሚቃወም ንቅናቄ ሆኖ ተከሰተ። በተለይ በአረቡ አብዮት ወቅት በየመን የተነሳውን የጎዳና ላይ አመፅ የመሩት ሐውቲዎች ነበሩ።

በ1995 ዓ.ም የሊባኖሱ የሻያ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድርጅት በሂዝቦላ ተፅእኖ ሐውቲዎች መደበኛ የሆነውን ፀረ አሜሪካ ፣ እስራኤል እና አይሁድ መፈክሩን ይፋ አድርጓል። አክሲሱን በይፋ መቀላቀሉን ግልፅ ባደረገበት 1990ዎቹ ውስጥ የትጥቅ ትግሉን በማካሄድ የኢራን አጋር የሳኡዲ ባላንጣ በመሆን ለመካከለኛው ምስራቅ  አስጊ ቡድን እስከመሆን ጠንክሯል።

ከሳላህ መንግሥት ጋር ፍልሚያ የጀመረው ሐውቲ መሪው በመንግሥት ኃይሎች እጅ እንዲሰጥ የቀረበለትን ጥያቄ የተቃወመው የቡድኑ መሪ አል ሐውቲ በ1994 ዓ.ም ተገድሏል። በእርሱም እግር ወንድሙ አብዱል ማሊክ አል ሐውቲ የመሪነቱን ቦታ ተረክቦ ረጅም ጊዜ ቡድኑን መርቷል። ድርጅቱ በጎዳና ተቃውሞዎች እና አመፆች በመሳተፍ እና ሌላ የየመን የተቃውሞ ቡድኖችን በማስተባበር በየመን አብዮት ውስጥ ተሳታፊ ነበር።

ከሳውዲ አረቢያ ጋር ጥል የሆኑት የሐውቲ ቡድኖች የሺያ ሙስሊሞችን ሚወክል መሆኑ የኢራን ተፈጥሮአዊ ወዳጅ አድርጓቸዋል። ከ20 ሺህ በላይ ሰራዊት እዳለው የሚገመተው የሐውቲ ጣጣቂ ቡድን በሳውዲ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት አስወግዶ ዋና ከተማዋን ሰንአን ጨምሮ አብዛኛውን የየመን ክልል እና የቀይ ባህርን አካባቢ ተቆጣጥሮ ይገኛል።

ሐውቲዎች በቅርቡ በአሜሪካ እና በእንግሊዝ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። ምክንያታቸውም እስራኤል በጋዛውያን ላይ እያደረሰችው ያለውን ጥቃት በተመለከተ አጸፋዊ ምላሽ እንደኆነ በመግለፅ ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ከጋዛ ጦርነት ተከትሎ ነበር የተለያየ መጠን ያላቸውን ሚሳይሎች እና ድሮኖችን በመጠቀም በቀይ ባህር አካባቢ የሚደረገውን መርከብ እንቅስቃሴ በማስተጓጎል ወደ እስራኤል በቀጥታ በመተኮስ ተቃውሞውን እያሳየ ይገኛል። ይህ ድርጊት ከአሜሪካ እና ወዳጆቿ ጋር አላትሞታል። በሌላም በኩል አሜሪካ ይህ የሐውቲ ድርጊት በአስቸኳይ እስካልቆመ ድረስ እጄን ከኢራን አላነሳም እያለች ነው። ኢራን ከጀርባ ትረዳዋለች የሚል እምነት ስላላት ኢራንን ለመበቀል ማስጠንቀቂየ እየሰጠች ለምትገኘው አሜሪካም ኢራን ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥታለች።

የኢራቅ እስላማዊ አርበኝነት

ሌላው የጥምረቱ አካል ብቅ ያለው ከወደ ኢራቅ ነበር። የኢራቅ እስላማዊ ረዚዝታንስ ይባላል፣ ከኢራን ጋር ትስስር ያላቸው የሻይት ሙስሊሞች ቡድን ከባድ ተገዳዳሪ ሆኖ የተነሳው በ1993 ዓ.ም አሜሪካ መራሹ ወረራ በኢራቅ ላይ መደረጉን ተከትሎ ከ10 ሺህ ያለፈ ታጣቂዎች ያሉት እስከ መሆን አድጓል። ዋና ኢላማው በኢራቅ እና በሶሪያ የከተሙ የአሜሪካ ሀይሎችን ማጥቃት ላይ ያተኮረ ሲሆን ቡድኑ ይፋ እንዳደረገው አላማቸው እስራኤል በጋዛ ላይ ያደረገቸውን ጥቃቶች እና የአሜሪካ ኃይሎች ወደ ኢራቅ እና አካባቢው የመሰማራታቸውን ተግባር ለመቃወም ነበር። ይህ አቋምም በእስራኤል እና የጋዛ ጦርነት ላይ ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡

አክሲስ ኦፍ ረዚዝታንስ በሚል የሚታወቀው ኢራን ደገፉ የትግል ጥምረት ታዲያ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር በተናጠል እና በመናበብ እየተፋለመ ይገኛል። በአሜሪካ እና በእስራኤል እንዲሁም በእንግሊዝ መርከቦች ላይ ሀውቲ ጥቃት መፈፀሙ እና የምእራባውያን ምላሽ ስለዚህ ጥምረት የሚናገረው ሚስጢር አለ። አሜሪካ የሐውቲ ጥቃት የማይቆም ከሆነ ኢራን ተረኛ የቅጣቷ ሰለባ እንደምትሆን ታስጠነቅቃለች፤ ኢራን በበኩሏ አፀፋው እንደሚከብድ ትገልፃለች። መካከለኛው ምሥራቅ እንደዚህ በውጥረት ውስጥ ቀጥሏል፣ መጪውን አብረን እናየዋለን። ሰላም።

(መሠት ቸኮል)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here