የበዓል ወቅት ግብይት

0
117

በበዓል ወቅት የስጦታዎች፣ ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦች እና ሌሎች ግብይቶች ከሌሎች ጊዜያት በተለዬ የሚከናወንበት ነው። በበዓላት ወቅት ግብይት ይጨምራል፣ ሕብረተሰቡም ለበዓል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለመግዛት ወደ ግብይት ማዕከላት ይወጣል፣ በግብይት ቦታዎች መጨናነቅ እና መገፋፋት ይነግሳል። በዚያው ልክም የዋጋ ንረት ሊከሰት ይችላል፡፡

ብልሆች ታዲያ ይህንን በመረዳት ቀድመው መሠረታዊ ምርቶችን በመግዛት ለበዓል ይዘጋጃሉ። ከነዚህ ግለሰቦች መካከል ወ/ሮ አዳነች ተገኘ ተጠቃሽ ናቸው። ወ/ሮ አዳነች በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግምጃ ቤት ከተማ በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው እንደሚሠሩ በስልክ ነግረውናል። በዓል ከመድረሱ በፊት ቀድመው ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በመግዛት ከተጋነነ ዋጋ እና መሠል ችግሮች እንደሚድኑ አጫውተውናል።

ወይዘሮዋ እንደነገሩን ከ2003 ዓ.ም ጀምረው በአገው ግምጃ ቤት ሸማች ማሕበር አባል ናቸው፤ አብዛኛዎቹን የፍጆታ ምርቶችንም በሸማች ማሕበሩ በኩል ያገኛሉ፡፡ በመጪው እሁድ ለሚከበረው ለትንሳኤ በዓል ደግሞ 50 ኪሎ ግራም ጤፍ በሦስት ወር የሚከፈል ወስደዋል። በተመሳሳይ ዘይት፣ የፊኖ ዱቄት እና ስኳርም አግኝተዋል።

ከገበያው ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ቅናሽ እንዳለው በማንሳትም ምርቶችም ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው ብለዋል። ይህን ተከትሎ ታዲያ በሸማች ማሕበራት ምርት መምጣቱ ሲታወቅ በነጋዴው ዘንድ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ ነው ትዝብታቸውን ያጋሩን። ሸማች ማሕበሩ እያደረገው ላለው አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረቡት ወ/ሮ አዳነች ነጋዴዎችም በተጋነነ ዋጋ ባለመሸጥ ሕዝባቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

ሌላው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግምጃ ቤት ከተማ  የሚኖሩት እና ሐሳባቸውን ለበኩር ጋዜጣ ያጋሩት አቶ አድነው ዘለቀ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የኑሮ ውድነቱ እና የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና እርሳቸውን ጨምሮ የሰዎችን ሕይወት እየፈተነ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ መፍትሔ ደግሞ የሸማች ማሕበራት መቋቋሙ እና መጠናከሩ በእጅጉ አስፈላጊ  መሆኑን ነው የእርሳቸውን ተጠቃሚነት አብነት አድርገው ያስረዱት።

አቶ አድነው  እንዳሉት በሸማች ማሕበሩ ከ12 ዓመታት በላይ አባል ሆነው የኢንዱስትሪ እና የሰብል ምርቶችን እየገዙ ሲጠቀሙ ኖረዋል። አሁንም ጤፍ፣ ፊኖ ዱቄት፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ሳሙና እና ሌሎች ምርቶችን በመግዛት ይጠቀማሉ።  ለመጪው የፋሲካ (የትንሳኤ) በዓልም በሦስት ወር የሚከፈል 100 ኪሎ ግራም (አንድ ኩንታል) ጤፍ ወስደዋል።

በተመሳሳይ በሕብረት ሥራ ማሕበሩ በኩል የሚቀርቡ ምርቶች ከነጋዴዎች ጋር ሲወዳደር መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ አለው፤ ለአብነትም አንድ ኪሎ ግራም ስኳር ከ150 እስከ 160 ብር በገበያ እየተሸጠ ሲሆን በሸማች ማሕበሩ በኩል ግን 127 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል። ይህም ሸማች ማሕበሩ ገበያን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ ነው በማሳያነት የጠቀሱት።

ለሸማቹ ማሕበረሰብ የተለያዩ ምርቶችን እያቀረበ መሆኑን የነገሩን ደግሞ በአንክሻ ጓጉሳ ወረዳ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ጽ/ቤት አገው ግምጃ ቤት ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበር  የጽ/ቤት ኃላፊ አበበ መኩሪያው ናቸው። ኃላፊው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት የሕብረት ሥራ ማሕበሩ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በሚፈለገው ጊዜና መጠን ያቀርባል፤ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት በመቆጣጠር ለሸማቹ በተመጣጣኝ  ዋጋ ያቀርባል፡፡ በአጠቃላይ ሸማቹ ማሕበረሰብ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዝ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የአርሶ አደሩን ምርት አጓጉዞ ለማምጣት ፈታኝ ቢያደርገውም ችግሩን ተቋቁሞ እየተሠራ ነው። ማሕበሩ ለሸማቹ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ሳሙና፣ ፊኖ ዱቄት እና ሌሎችን ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል።

ከአሁን በፊት አንድ ሺህ ኩንታል ጤፍ እና 175 ኩንታል በቆሎ ለመንግሥት ሠራተኛው በሦስት ዙር እንዲከፍሉ ተደርጉ መሰጠቱን ተናግረዋል። ይህም እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ለሚቸገረው ማሕበረሰብ ፋታ ይሰጣል ነው ያሉት። በዚህ ወቅትም የትንሳኤ (የፋሲካ) በዓልን ምክንያት በማድረግ 220 ኩንታል ጤፍ እና 66 ኩንታል ስኳር ቀርቦ ለተጠቃሚው ተሠራጭቷል። 50 ኩንታል የፊኖ ዱቄት እና ሰባት ሺህ ሊትር ዘይት ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል ነው ያሉት። በቀጣይም ሌሎች ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን አክለዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሕብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አብርሃም ዳኛው እንደተናገሩት የሕብረት ሥራ ማሕበራት ማሕበረሰቡ በተናጠል መፍታት ያልቻላቸውን ችግሮች ለመፍታት የተቋቋሙ ናቸው። የሕብረት ሥራ ማሕበራት በተለይም ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በማቃለል የንግድ ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ቁልፍ ድርሻ አላቸው። የሕብረት ሥራ ማሕበራት ሻጭ እና ሸማችን የሚያገናኙ አይነተኛ ድልድይ ናቸው ብለዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ 29 የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት ይገኛሉ። ለሸማቹ ማሕበረሰብ የገበያ ጉድለት ያለባቸውን የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ጤፍ፣ በቆሎ፣ አተር፣ ሽንብራ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ሳሙና እና ሌሎች ማሕበረሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶችን እያቀረቡ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ለአብነትም በዚህ ዓመት በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች 150 ሺህ ኩንታል የተለያዩ ምርቶችን በመግዛት ለማሕበረሰቡ ማቅረብ መቻሉን አንስተዋል።

በተመሳሳይ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማሕበራት የተትረፈረፈ ምርት ካለባቸው አካባቢዎች እጥረት ወደ አለባቸው አካባቢዎች የማጓጓዝ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከብሔረሰብ አስተዳደሩ የሕብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው አሁን ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት የምግብ ዘይት በመሆኑ 22 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ተመድቦ ግብይት ለመፈፀም ከአምራች ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል። ለጤፍ ደግሞ በ198 ሚሊዮን 712 ሺህ ብር ግዢ ተፈፅሞ በተመጣጣኝ ዋጋ በሦስት ጊዜ ክፍያ እንዲገዙ ተደርጓል፤ 1000 ኩንታል የሚሆን የስኳር ምርትም ግዢ ተፈፅሞ ለሸማቹ ደርሷል። ቀይ ሽንኩርት ከሚመረትበት አካባቢ ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ ነው።

ኃላፊው አቶ አብርሃም የምርት አቅርቦቱን በብዛትም ሆነ በጥራት ለማቅረብ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ  ንግድ መምሪያ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል። ማሕበረሰቡ ግብይቱን ራሱ ካቋቋማቸው መሠረታዊ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ጋር  ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። ይህም በተመጣጠነ ዋጋ እንዲገዛ እና ገበያው እንዲረጋጋ ከማድረግ ባለፈ የማሕበሩን ገንዘብ ያሳድጋል።

እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ጤናማ የሆነ የንግድ ሥርዓት መዘርጋት፣ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን እና ደላሎችን መቆጣጠር፣ በቂ ምርት ማምረት እና የሕብረት ሥራ ማሕበራትን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ለበዓል ገበያ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፤ የቢሮው ኃላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ በቂ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። የግብዓት አቅርቦት የሚያቀርቡ አካላት አስቀድመው ተለይተው ሥራ መሠራቱንም አመላክተዋል።

ለዚህም በሁሉም አካባቢ በቂ ሥራ መከናወኑን አስታውሰዋል፤ የተመረተው ምርት ጤናማ በሆነ የግብይት ሥርዓት እንዲመራ ከመደበኛ ገበያዎች በተጨማሪ ጊዜያዊ የገበያ ማዕከላት መዘጋጀታውንም አስታውቀዋል።

በተዘጋጁት ገበያዎች ሸማቾች በቅርበት ምርት ማግኘት እንደሚችሉም አንስተዋል። ግብይቱ ደላላ ሳይገባበት ሸማቹ በቀጥታ እንዲያገኝ እየተሠራ ነው ብለዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here