የአሜሪካ እና ኢራን ሰሞነኛ ሁኔታ

0
160

በቀደመ ስሟ ፋርስ በመባል ትታወቃለች።  በመካከለኛው እና በደቡብ እስያ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ የዐረብ መንግሥታት መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፤ ለምዕራባዊን ዛቻና ማስፈራሪያ የማትንበረከከው ኢራን። እስከ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚደርሰው ስፋቷ እና ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ኢራንን ጠቃሚ ሀገር አድርጓታል።

እ.አ.አ በ1979 ንጉሣዊው ሥርዓት ሲገለበጥ ኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ሆና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኃይማኖት መሪዎች ሀገሪቱን እየመሩ ነው። ኢራን የረዥም ጊዜ የስኮላርሺፕ (የውጪ ትምህርት ዕድል) ታሪክ ያላት ሀገር ናት። የዳበረ የስነ ጥበብ፣ ስነ ጽሑፍ፣ ግጥም፣ ሙዚቃ፣ ስነ ምግብ እና ስነ ሕንጻ ማዕከል ናት።

የጥንት ኢራናውያን በፍልስፍና እና በሕክምና ላይ ተደማጭነት እና ተቀባይነት ያላቸውን ጽሑፎች የጻፉ ሲሆን ለአብትም አልጀብራን (የሒሳብ ትምህርት ማዕከል እንደሆነ ልብ ይሏል) የፈጠረው ኢራናዊ የሒሳብ ሊቅ ነው። የኢራን ዩኒቨርሲቲዎች በመካከለኛዉ ምሥራቅ ውስጥ በጣም የተከበሩ መሆናቸውንም ሂስትሪ (www.history.com) ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል፡፡

ታዲያ ይህቺ ታሪካዊ ሀገር ስሟ በምዕራባዊያን በተለይም በአሜሪካ ዘንድ በጥሩ አይነሳም፤ ኢራን ሽብርተኝነትንና አሸባሪዎችን ትደግፋለች እንዲሁም ጅምላ ጨራሽ ኒውክሌር መሣሪያ እየሠራች ነው በሚል ውግዘት ደርሶባታል። እየደረሰባትም ነው፤ የማዕቀብ መአትም ወርዶባታል።

ይሁን እንጂ ኢራን “ኒውክሌር ለኃይል ማመንጫነት እና ለምርምር ያስፈልገኛል” በሚል የኑክሌር ኃይል ማበልጸጓን ቀጥላለች። ይህ ድርጊቷ ያልተዋጠላቸው ምዕራባዊያን በተለይም አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር ኃይልን ለጦር መሣሪያነት ለማዋል ነው የምታበለጽገው በሚል በርካታ ማዕቀቦችን ጥለውባታል።

እነዚህ ማዕቀቦች ታዲያ የኢራንን ኢኮኖሚ አሽመድምደውታል። ከዚህ በተጨማሪም የተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ዓለም አቀፍ የንግድ ተሳትፎዋን ቀንሷል። እንዲሁም   ዓለም አቀፍ ተቋማት አብረዋት እንዳይሠሩ በመደረጉ ሀገሪቱ እጅ ከዎርች ታስራለች፤ ኢራን ከዓለም አቀፍ ነዳጅ አምራች ሀገራት መካከል (ኦፔክ) አንዷ ብትሆንም በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ዜጎቿ ያን ያህል የደላ ሕይዎት አይኖሩም፤  በመካከለኛ የገቢ ደረጃ የሚገኙ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የእስራኤል – ሃማስ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ቀጥተኛ ግጭት የመፍጠር አደጋን አንዣቧል። በየመን ያሉት ሃውቲዎች እና በሊባኖስ ውስጥ ያሉት ሂዝቦላ ታጣቂ ቡድኖች በኢራን የሚደገፉ እነ በቀይ ባሕር እና በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ላይ የጦርነት ግንባሮችን ከፍተዋል።

እ.አ.አ ሚያዚያ 01 ቀን 2024 እስራኤል  ሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ሕንጻ ላይ  የአየር ጥቃት በመፈጸም ሁለት የኢራን ጄኔራሎችን እና አምስት የጦር አማካሪዎችን መግደሏን ተከትሎ ውጥረቱ ጨምሯል። ኢራን ከቀናት ቆይታ በኋላ ከሦስት መቶ በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤል ጥቃቶችን በመክፈት እስራኤል ላይ አጸፋዊ ጥቃት ፈጽማለች። ኢራን እስራኤልን በቀጥታ ስታጠቃ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ ጥቃቱን እስራኤል 99 በመቶ የሚሆነውን በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ በመታገዝ ማክሸፏን አስታውቃለች።

በባራክ ኦባማ ዘመን (እ.አ.አ 2015) ኢራን  የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን እንድትገድብ የሚያደርግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ወደ ሀገሪቱ ገብተው የኒውክሌር ማብላያዎቹ ከሲቪል ዓላማ ውጪ ለጦር መሣሪያ ማምረቻ አለመዋላቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይናን ያካተተ ስምምነት ተፈራርመው እንደነበር የሚታወስ ነው። ስምምነቱ ኢራን ኢኮኖሚዋን ካሽመደመደው ማዕቀብ በመጠኑም ቢሆን እፎይታን የሰጣት ነበር። ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ (እ.አ.አ በ2016) አሜሪካ ከስምምነቱ እንድታፈነግጥ አድርገዋል። ኢራንም የባለስቲክ ሚሳኤሎችን መሥራቷን አጠናክራ ቀጠለች። ይህ ተግባር ደግሞ ከሆነ  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ውሳኔ 2231 ይጥሳል ስትል ነው አሜሪካ የከሰሰችው።

ቢቢሲ እንደዘገበው ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢራን የኒውክሌር ቦምቦችን ለመሥራት የሚያገለግል የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት መገንባቷን አረጋግጧል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫ እያየለ መጥቷል፤ ሰሞነኛ ዓለም አቀፍ ጉዳይም ሆኗል።

እስራኤልም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ጽኑ ፍላጎት አላት፤ ይህንን ጉዳይም በተጠንቀቅ እንቅልፍ ሳትተኛ ነው የምትከታተለው። ምክንያቱም እስራኤል ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ካገኘች ደኅንነቷ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ታስባለችና ነው። አሁን ያለው የኢራን መንግሥትም እስራኤል የምትባል ሀገር በመካከለኛው ምሥራቅ እንደሌለች ነው የሚያምነው፡፡ ባለፈው ዓመት ኢራን በእስራኤል ላይ ላስወነጨፈችው የሚሳኤል ጥቃት አፀፋ እስራኤል ዋና ዒላማ ያደረገችው የኢራንን ኒውክሌር ጣቢያ መሆኑንም ልብ ይሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሰሞኑ በኋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታገኝ ለማድረግ እኛ እና አሜሪካ አንድ ነን” ሲሉ መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።

እ.አ.አ በግንቦት 2019 ኢራን እና የምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ለማጥቃት እየተዘጋጁ መሆናቸውን መረጃ ከወጣ በኋላ አሜሪካ ኢራንን ለመከላከል B-52 የተሰኙ የኒውክሌር አቅም ያላቸውን ቦምቦችን፣ የአውሮፕላን ተሸካሚ መሣሪያን እና ተጨማሪ  የሚሳኤል ባትሪዎችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አሰማርታለች።

ይሁንና በሆርሙዝ ባሕር (በፋርስ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ መካከል የሚገኝ የባሕር ዳርቻ) ዳርቻ ወይም አቅራቢያ ስድስት የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቦች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ለጥቃቱ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል። አሜሪካም ተጨማሪ ሁለት ሺህ 500 ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለማሰማራት ተገዳለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን   ከእስራኤልና አሜሪካ የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት እንደምትጠቀምባቸው ያስተዋወቀቻቸውን ምሥጢራዊ የሚሳኤል ከተሞችን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች፤ ኢራን ሚሳኤል ለማስቀመጥ ከምድር በታች የገነባቻቸውን ምሥጢራዊ ማቆያዎችንም ነው ለዓለም ዕወቁልኝ ያለችው። መጠነ ሰፊና በሀገሪቱ ተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ ሸለቆዎች መካከል የተገነቡ እነዚህ ከተሞች ባሊስቲክና ክሩዝ ሚሳኤሎችን ለማከማቸት እና ለመተኮስ ይውላሉ። ሰው አልባ አውሮፕላንና የአየር መቃወሚያ መሣሪያም እንደሚገኝባቸው ጭምር ነው የተገለጸው።

አሜሪካ በቅርቡ ቦምብ የጫኑ ስድስት ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖችን በኢራንና የመን አቅራቢያ ወደሚገኙ ወታደራዊ መቀመጫዎች ማስጠጋቷን የሀገሪቱን ባለሥልጣን መነገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሻን ፓርናል ኢራን ወይም አጋሮቿ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ፍላጎት የሚገዳደሩ ከሆነ ሕዝባቸውን ለመከላከል እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ካደረሱ ደግሞ ኢራን ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመጠቀም ትገደዳለች ሲሉ የቀድሞው የኢራን  ፓርላማ አፈ ጉባኤ ተናግረዋል።

እንዲህ እንዲህ እያለ ታዲያ የአሜሪካ እና ኢራን የቃላት ጦርነት እየጦዘ ነው፤  አንዱ በሌላው ላይ ከባድ ርምጃን እወስዳለሁ ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ለአብነትም የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የምትባለውን ካልፈጸመች በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ቦምብ እናወርድባታለን ሲሉ ዝተዋል፤ ኢራንም በሕንድ ውቅያኖስ ዲዬጎ ጋርሲያ በሚባል አካባቢ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈርን በቦምብ አጋየዋለሁ ስትል የአጸፋ ምላሽ መስጠቷን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

ታዲያ አሜሪካ እና ኢራን ከብዙ ዓመታት ውዝግብ እና ክስ በኋላ የኒውክሌር ኃይልን በተመለከተ ቀጥታ ውይይት እንደሚያደርጉ የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ አስታውቀዋል።

የአሜሪካ  ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ በዋሺንግተን እና ቴህራን መካከል የሚደረገው ውይይት  ስምምነት ላይ ካልተደረሰ “ለኢራን በጣም መጥፎ ቀን ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ድርድሩ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ መሆኑንም ነው ያሳወቁት።

ዶናልድ ትራምፕ በመጋቢት ወር በተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በኩል ለኢራን መሪ ለድርድር ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ደብዳቤ ልከው እንደነበር ነው ቢቢሲ የዘገበው። የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመገንባት አቅምን መግታት ለአሜሪካ እና አጋሮቿ ለዐሥርት ዓመታት የዘለቀ ቁልፍ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ ሆኖ መቆየቱን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here