ሀገራት ከተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት መውጣት ተስኗቸው ሰብዓዊ ጉዳቱ ሲጨምርባቸው፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩ በከፍተኛ ደረጃ ሲላላባቸው፣ ምጣኔ ሐብታቸው ደቆ ከተወዳዳሪነት እንዲወጡ ሲያደርጋቸው እና የሀገራቸው ገጽታ በዓለም ዐደባባይ ክፉኛ ሊጠለሽባቸው መሆኑን ሲያስቡ ሀገራዊ የምክክር መድረክን በመውጫ መንገድነት ያደርጋሉ፤ ተጠቅመውበትም ሰላማቸውን የመለሱት በርካቶች ናቸው፡፡
እሲያ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ላቲን አሜሪካ… ምክክርን የሰላማቸው ማረጋገጫ፣ የዜጎቻቸው ስቃይ ማብቂያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በርካቶች በውጤታማነት ሲጠቅሱ፣ እንደ የመን ያሉት ደግሞ ሂደቱን በክሽፈት አጠናቀው ዜጎቻቸውን ለመከራ ዳርገዋል፡፡
ኢትዮጵያም ሀገራዊ የምክክር መድረክን ከተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት የመውጫ መንገድ አድርጋ ለዜጎቿ እፎይታን ለመስጠት እየሠራች ትገኛለች፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ 13ኛ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉን ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ቀናት በአማራ ክልል አካሂዷል፡፡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱም አሥር የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ሴቶች፣ ዕድሮች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ መምህራን… ከተሳታፊዎች መካከል ናቸው፡፡
አምስት ባለድርሻ አካላትም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ባካሄደው ክልላዊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ ናቸው፡፡ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማኅበራት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና በመጀመሪያው ዙር ምክክር ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተመረጡ የወረዳ ማኅበረሰብ ወኪሎች ይገኙበታል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ደረጀ ቦጋለ አንዱ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገር ወደ ተሻለ መንገድ እንድትመጣ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ሲመላለስ የነበረው ሐሳብ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እርሳቸውም የወከላቸው የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት ነው ያሉትን ሐሳብ በነጻነት እንደገለጹ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሐሳቦችም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ እና የእኩልነት ምድር እንድትሆን፣ ዜጎቿም በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ስንቅ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የአማራ ክልልን ጥንታዊ ወግ፣ ባህል እና እሴት የሚመልሱ እና የሚያጠናክሩ ሐሣቦች መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ መልካሙ ታደሰ ተፈናቃይን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ ሌላው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ግለሰቡ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በ2010 ዓ.ም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው አሁንም በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡ እየደረሰባቸው ያለው ችግር በሀገራዊ ምክክሩ እንደሚፈታ ሙሉ እምነትን አሳድረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች፣ አሁን እና ወደ ፊት ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ምክንያቶች ያለምንም ክልከላ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡ አማራ ክልልን ጨምሮ ሀገር ሰላም መሆን አለባት ያሉት ተሳታፊው፣ ለዚህም በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት “ወገኔ መሰቃየት በቃው!” ብለው ልዩነቶቻቸውን በምክክር መፍታትን ሊያስቀድሙ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ወይዘሮ አሚናት ሁሴን ሌላዋ የምክክር ሂደቱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ እስካሁን የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ለበርካቶች ሞት፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ ንብረት ውድመት እና ለማኅበራዊ መስተጋብር ትስስር መላላት መዳረጋቸውን አንስተዋል፡፡ የሰላም መደፍረስ በተለይም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የተመለከቱትን መነሻ አድርገው አስታውቀዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወነ ባለው ሂደት ተሳታፊ በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው፡፡ ሰላምን ያመጣሉ ያሏቸውን ሐሳቦችም በነጻነት እንደሰነዘሩ ገልጸዋል፡፡ በአጀንዳ ማሰባሰቡ እና በወኪል መረጣው የተመለከቱት አካሄድ በምክክር ኮሚሽኑ የመጨረሻ ውጤት ትልቅ ተስፋን እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም ሲቋቋም ሦስት መሠረታዊ ዓላማዎችን አንግቦ መነሳቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ/ዶ/ር/ አስታውቀዋል፡፡ ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት ቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ በሕዝብ እና በመንግሥት እንዲሁም በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል የጸና እምነት መፍጠር ሌላኛው የሀገራዊ ምክክሩ ግብ መዳረሻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ባኮረፍን እና በተቆጣን ቁጥር ጠብመንጃ ይዞ ጫካ መግባትን በማስቀረት ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህልን ማዳበር ሦስተኛው የኮሚሽኑ ዓላማ አድርገው ዶ/ር ዮናስ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ኩራት እና መመኪያ የመሆኗ መነሾ ዓድዋ ነው፡፡ ድሉ ቋንቋን፣ ብሄርን፣ ሃይማኖትን… ሳይለይ በአንድነት የተገኘ መሆኑ የተምሳሌትነታችን መገለጫ ለመሆን መብቃቱን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ሌላኛው የኢትዮጵያውያን ሕብረት ውጤት ነው ያሉት የሕዳሴውን ግድብ ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት የሕብረታችን ውጤት ሆነው የተመዘገቡ ዓለም አቀፋዊ ድሎቻችንን ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይም በመድገም ሦስተኛውን ዓድዋ እውን ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡ “በቤተሰብ መሀል ፀብ ሲፈጠር ሰው እንዴት ዝም ይላል!?” ሲሉ አሳሳቢነቱን አንስተው ሁሉም ለሰላም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ኢትዮጵያ ለዘመናት እርስ በእርስ በመደማማት ሕይወት ከመጥፋት፣ አካል ከመጉደል፣ ልጆቿ በስደት እንዲንገላቱ ከማድረግ፣ በከፋ ድህነት ውስጥ እንድትቆይ ከማድረግ ውጪ አንዳች ያተረፈችው ነገር እንደሌለ አስምረውበታል፡፡ ለዚህም ከገባችበት የእርስ በእርስ የግጭት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ምክክር የመጨረሻው ወሳኝ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽነር መላኩ “ወንድም ወገኑን ገድሎ ጀግንነት የለም!” ብለዋል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ አማኝ ሕዝብ ባለበት ሀገር ለእልቂት ቅድሚያ ቦታ መስጠት ተገቢ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡ “ሁሉም ነገር ተሰጥቶን የሁሉም ነገር ባለቤቶች ሆነን ሳለ ዛሬ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች የሁሉም ነገር ጭራ እንድንሆን አድርጎናል” ብለዋል፡፡
እናቶች የሚያለቅሱበት ዘመን እንዲያበቃ እና ወላጆች ወልደው መና የሚቀሩበት ጊዜ እንዲያከትም ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ግጭት ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም የትልቅነት እና የሥልጣኔ መገለጫ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር አንስተዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ግጭት እንዲቆም ሁሉም “በቃ!” ከማለት ጀምሮ በመነጋገር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለማዋለድ የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ይህም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት በመገንባት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚያደርግ ነው፡፡
እንደ ኮሚሽነር መላኩ በእስር ላይ ያሉ፣ በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ እና በውጪ ሀገራት በስደት ላይ ያሉ ወገኖችን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለማሳተፍ የተጠናከረ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ ሐሳባቸውን የሚሰጡበት አማራጭ ለመዘረጋትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት በመኖር እና ባለመኖር ሁለት ምርጫዎች ላይ መገኘታቸውን ገልጸው ሀገራዊ ምክክር ዋናው መፍትሔ መሆኑን አስምረው የተናገሩት ደግሞ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ባለፉት ዘመናት ያጋጠሙ ችግሮች በርካታ እሴቶቻችንን ሸርሽሮ ያለፈ በመሆኑ ምርጫችን ሰላምን በመነጋገር መፍታት እንደሆነ ጠቁመዋል። “አሁን በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ከፍ የሚለው ፓርቲ፣ ግለሰብ ወይም ድርጅት ሳይሆን ኢትዮጵያ ናት!” በማለት የምክክርን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን የተለያዩ ፍላጎቶች በምክክሩ ይዘው በመቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“በየዘመኑ የተነሱብንን ወራሪዎች በአባቶቻችን ጥበብ፣ በእናቶቻችን ሀገር ወዳድነት እና ጸሎት፣ በወጣቶቻችን ጥንካሬ አሸንፈን ዛሬም ባለ ሀገር ነን” ያሉት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው ኢትዮጵያውያን በበርካታ ጉዳዮች ላይ በአንድ ልብ መክረው እና ተግባብተው በመሰለፋቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአንጻሩ ኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለመግባባቶች እና የሃሳብ ልዩነቶች ጎልተው የሚታዩባት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የሆነው የሃሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን የምንፈታበት መንገድ ከምክክር ይልቅ የኅይል አማራጭ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳያነት አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ በኢትዮጵያ የሀገር ምሥረታ እና ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን፣ ለኢትዮጵያም መገለጫ የሆኑ የባሕል፣ የቅርስ እና የታሪክ ምሰሶዎችን ማቆም የቻለ ታልቅ ሕዝብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች እየሰፉ በመምጣታቸው፣ የሃሳብ ልዩነቶችን በኀይል አማራጭ ለመፍታት ጥረቶች መደረጋቸው የሀገር ባለውለታ የሆነው ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን አክለዋል፡፡
በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መገለላቸውን፣ ሴቶች በውስብስብ ችግር ውስጥ እንዲያልፉ መገደዳቸውን፣ በርካታ ወጣቶች ሕልማቸውን ይዘው ለመቀመጥ ወይም ወደ ጫካ ለመግባት መገፋፋታቸውን እና ከፍተኛ ሃብት መውደሙን አስታውሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከመነጋገር፣ ከመደማመጥ እና ከመመካከር ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን መክረዋል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን ተደርጎ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ ያሉ ታጣቂ ወገኖችን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች አሁንም ሁሉን አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም