ለነዋሪዎች የቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት ማሕበራትን የማደራጀት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል። የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በሰጡት መግለጫ የነዋሪዎችን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል። ለአብነትም በመሠረተ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።
የከተማው ሕዝብ ከሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መካከል የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አቅርቦት አንዱ መሆኑን አቶ ጎሹ እንዳላማው አንስተዋል፤ ጥያቄውን ለመመለስ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ለተደራጁ ማሕበራት የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። በሕዳር ወር 2013 ዓ.ም በማሕበር መደራጀት እንዲቆም ከንቲባ ኮሚቴ ወስኖ እንደነበር በማስታወስም አሁን ላይ እገዳው ተነስቶ መደራጀት እንዲቻል ኮሚቴው መፍቀዱን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ጎሹ ማብራሪያ በቀጣይ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለመስጠት የከተማ አሥተዳደሩ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለጸጥታ መዋቅሩ አባላት እና ለከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ለማደራጀት የምዝገባ ዝግጅቱ ተጠናቋል። በአጭር ጊዜ የማደራጀቱ ሥራም ይጀመራል። ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫዎች የቤት መሥሪያ ቦታ መዘጋጀቱን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው ተናግረዋል።
አቶ ጎሹ እንዳስገነዘቡት ከንቲባ ኮሚቴው ከአምስት መቶ በላይ የቤት ማሕበራት እንዲደራጁ ፈቅዷል። አደረጃጀቱም በቤት ሥራ ማሕበር መመሪያ መሠረት የሚፈጸም በመሆኑ ከአሁን በፊት ይከሰቱ የነበሩ የአሠራር ችግሮች አይደገሙም። ማደራጀት ያለበት የማሕበራት ጽ/ቤት ብቻ በመሆኑ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ይሠራል ነው ያሉት። በመሆኑም መላው የከተማ ነዋሪዎች ከአደራጅ መሥሪያ ቤቱ እና ከኮሚቴዎች ውጪ የሚቀርብ አደረጃጀት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ከጉዳይ አስፈጻሚ ደላላ እንዲርቁና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የማደራጀት ሂደቱ በሦስት ምዕራፍ እንደሚከናወን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከሚያዝያ 06 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያ ለመንግሥት ሠራተኞች ከዚያም የፀጥታ አካላት እና የከተማዋ ነዋሪዎችን የማደራጀት ሥራው ይቀጥላል። ነዋሪዎች የሚተላለፈውን ማስታወቂያ በመከታተል በአካል ቀርበው እንዲደራጁም መልዕክት አስተላልፈዋል። በከተማዋ የሐሰተኛ መታወቂያን ለመከላከል በቀጣይ የዲጂታል መታወቂያ ለማዘጋጀት በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም ተናግዋል።
ከዚህ በፊት ዕውቅና የሌላቸው እና ተደራጅተው የተገኙ 936 ማሕበራት ሕግን ያልተከተሉ እና ስህተት ያለባቸው ሆነው መገኘታቸውን አቶ ጎሹ እንዳላማው ጠቅሰዋል። የሚጠየቁ አካላትም እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
ከአደራጅ መሥሪያ ቤቱ እና ኮሚቴዎች ውጪ የሚቀርብ አደረጃጀት ተቀባይነት እንደሌለው በማንሳት የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ለሠራተኞቻቸው መረጃ ሲሰጡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ተቀባይነት በሌላቸው ማሕበራት ተደራጅተው የተገኙ ነዋሪዎች ግን አሁን ላይ በተፈቀደው ማሕበር መደራጀት እንደሚችሉ ነው በመግለጫው የተገለፀው። በዚህም የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመፍታት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም