ሀገርን በምክክር የማጽናት ጥሪ ቀረበ

0
101

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የወኪል መረጣ አካሂዷል::

ዐሥር የማኅበረሰብ ክፍሎች እና አምስት ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የምክክር መድረክ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጠናክሩ ሐሳቦች መሰንዘራቸውን ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

አቶ መላኩ በላይ ከተሳታፊዎች መካከል አንዱ ናቸው::ግጭት ወይም ጦርነት እልቂትን፣ የኢኮኖሚ ውድቀትን እና የማኅበራዊ መስተጋብር ልልነትን ከማስከተል ያለፈ ለሰላም አማራጭ ሆኖ እንደማያውቅ ይናገራሉ፡፡

አሁን ካለው የሰላም መደፍረስ ወጥቶ በሰላም ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የግጭት ምንጮችን ለይቶ በትጋት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል::ለዚህም የሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል::“እኛ ሀገር በተደጋጋሚ ወደ ቀውስ አዙሪት እንድትገባ ያደረጉ ምክንያቶችን ለይተን ለኮሚሽኑ አቅርበናል፤ ውጤቱም መልካም እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

“የአማራ ክልል ሕዝብ ስለ ሀገራችን ይመለከተናል ብሎ ወቅታዊ ችግር ሳይበግረው በመገኘቱ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም” ያሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረሥላሴ ናቸው::የቆዩ አለመግባባቶች እና ችግሮች ዛሬ ላለው የትጥቅ ትግል ምክንያት አድርገው አንስተዋል::የትጥቅ ትግል ትንንሽ ጊዜያዊ ድሎችን ይሰጥ እንደሆን እንጂ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም ብለዋል::ሰላምን ሊሰጥ የሚችለው ሕዝቡ ቁጭ ብሎ በስክነት መነጋገር እና መመካከር ሲችል፣ ስለ ሀገራቸው የነገ ዕጣ ፈንታ በጋራ መወሰን ሲችል ነው ብለዋል::ይህንንም ዕውን ለማድረግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ አቅም እንደሚሆን፣ ችግሮችን ቀርፎም ሀገራዊ ሰላምን እንደሚያመጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል::

ሀገር በምክክር የቀደመ ሰላሟ ይመለሳል ብለው በምክክር ሂደቱ የተሳተፉ አካላትን ያመሰገኑት ደግሞ ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሀሙድ ድሪር ናቸው::አሁንም በምክክር ሂደቱ ያላመኑ፣ ዳር ቆመው መሳሪያ ያነገቡ እና በእርስ በርስ ግጭት ፍላጎትን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወደ ሰላም መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሚዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here