ከዓለም ዋንጫ እና ከአውሮፓ ዋንጫ ቀጥሎ የብዙ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን ቀልብ የሚስበው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ::
የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለቱን የስፔን ኃያላን ክለቦች ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎናን፣ ሁለቱን የእንግሊዝ ክለቦች አርሴናል እና አስቶንቪላን፣ ሁለቱን የጀርመን ክለቦች ባየር ሙኒክንና ቦሩሲያ ዶርትሙንድን፣ እንዲሁም የፈረንሳዩን ፒኤስጂ እና የጣሊያኑን ኢንተር ሚላን በሩብ ፍፃሜው አፋልሞ አሁን ላይ አራቱን የግማሽ ፍፃሜ ተፈላሚዎችን አሳውቋል::
የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ከእንግሊዙ አስቶን ቪላ ጋር ባደረጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ ፒኤስጂዎች 5 ለ 4 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፈው ለግማሽ ፍፃሜው ቀርበዋል::
የስፔኑ ባርሴሎና እና የጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድም ባደረጓቸው የደርሶ መልስ ሁለት ጨዋታዎች ካታሎናዊያኑ በ5 ለ 3 የድምር ውጤት የግማሽ ፍፃሜውን የተሳትፎ ትኬት ቆርጠዋል::
የጀርመኑ ባየር ሙኒክና የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ባደረጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎችም የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የ4 ለ 3 ድልን አስመዝግቦ ለግማሽ ፍፃሜው የደረሰ የጣሊያን ክለብ ለመሆን ችሏል::
በብዙ የእግር ኳስ ተመልካቾች ዘንድ ትኩረት ስቦ የነበረው የእንግሊዙ አርሴናል እና የስፔኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ንጉሥ ሪያል ማድሪድ ጨዋታ በኤምሬትስ መድፈኞቹን የ3 ለ 0 ባለድል ቢያደረጋቸውም፣ የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ባለ ድሎቹ ሪያልማድሪዶች በሜዳቸው ሳንቲያጐ ቤርናቢዩ የጨዋታውን ውጤት ቀልብሰው ለ16ኛ ዋንጫቸው በግማሽ ፍፃሜው ይሳተፋሉ የሚሉ ግምቶች ትኩረትን ስበው ነበር::
ሎስ ብላንኮዎቹ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት በተሰጣቸው እና የአርሴናሎችን የሦስት ለባዶ የአሸናፊነት ድል ቀልብሰው ለቀጣይ ፍልሚያ ይቀርቡበታል በተባለው ጨዋታ የመድፈኞቹ መድፍ ዝግ የነበረውን የሳንቲያጐ ቤርናቢዩ ስታዲየም ጣሪያ በሁለት ለአንድ ጣፋጭ ድል አስከፍቶታል::
ኃያሉ የስፔን ክለብ ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጭ የተሸነፈባቸውን የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በሜዳው በመቀልበስ ለቀጣይ ድል የሚያደርገው መንደርደር ከሰሜን ለንደኑ አርሴናል ጋር የሚሠራ አልሆነም:: ጭራሽ በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት የሁለት ለአንድ ሽንፈትን እንዲቀምስ ተገዷል::
ሪያል ማድሪድ በ15 ዋንጫዎች ያሸበረቀበትንና ንግሥናውን የደፋበትን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ደጋግሞ እጅ የሰጠው ለእንግሊዙ የሰሜን ለንደን ክለብ አርሴናል ብቻ ነው:: በርካታ ከዋክብትን (ጋላክቲኮ) በማሠባሠብ የሚታወቀው ሪያል ማድሪድ ብዙ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በማሳካት በሚታወቁት ጣሊያናዊው አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ እና የክለቡ ኘሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ እየተመሩ በውጤት አልባው አርሴናል ከጉዟቸው ተደናቅፈዋል::
የቀድሞው የአርሴናል ኮከብ ቲዬሪ ዳንኤል ሄነሪ የሳንቲያጐ ቤርናቢዩ ፍልሚያ ከመካሄዱ በፊት “ብዙ የአውሮፓ ክለቦች ሪያል ማድሪድን ይፈሩታል፤ ሪያል ማድሪዶች ደግሞ አርሴናሎችን ይፈራሉ” ያለበት አስተያየቱ ፍሬ የያዘለት መስሏል:: ሌላኛው የቀድሞው የአርሴናል አማካይ ሴስክ ፋብሪጋስም”የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች በዛቻ ማሸነፍ የሚቻል ቢመስላቸውም ጨዋታውን ግን አያሸንፉም” የሚል የራሱን ግምት አስቀምጦ ነበር::
ቪኒሺየስ ጁኒየር፣ ኪሊያን ምባፔ እና ጁዲ ቤሊንግሃምን የመሳሰሉ የመጪው ዘመን የእግር ኳስ ኮከቦች የአርሴናሎችን የሦስት ለዜሮ ድል ቀልብሰው ደጋፊዎቻቸውን ጮቤ እንደሚያስረግጡ ቃል ቢገቡም፣ ዝግ በነበረው የቤርናቢዩ ስታዲየም ጣሪያ ሥር በስፔናው የአርሴናል ግብ ጠባቂ ዴቪድ ራያ መረብ ላይ ማሳረፍ የቻሉት የግብ ብዛት ግን አንድ ብቻ ሆኖ ተመዝግቧል::
አርሴናል በደርሶ መልስ ውጤት ሪያል ማድሪድን 5 ለ 1 ሲያሽንፍ በኤምሬትስ ሁለት ድንቅ የቅጣት ምቶችን ወደ ግብነት ከቀየረው እንግሊዛዊው ዴክላን ራይስ በተጨማሪ ስፔናዊው ሜኖ፣ እንግሊዛዊው ሳካ እና ብራዚላዊው ማርቲኔሊ ደግሞ ቀሪ ሦስት ግቦችን በስማቸው አስመዝግበዋል:: የሪያል ማድሪዶችን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ደግሞ ቪኒሺየስ ጁኒየር ነው::
ሻምፒዮንስ ሊጉ በሩብ ፍፃሜው ባስመለከተን ውጤት መሠረት የስፔን ክለቦች በባርሴሎና፣ ፈረንሳይ በፒኤስጂ፣ ጣሊያን በኢንተር ሚላን እና እንግሊዝ ደግሞ በአርሴናል ተወክለው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ይሆናል:: አምስቱ ታላላቅ ሊጐች ከሚባሉት ውስጥ በግማሽ ፍፃሜው ተወካይ ያጡት የጀርመን ክለቦች ብቻ ሆነዋል::
በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በግማሽ ፍፃሜው ከሚሳተፉት አራት ክለቦች ውስጥ ባርሴሎናዎች ለአምስት ጊዜ እ.አ.አ በ1992፣ በ2006፣ በ2009፣ በ2011 እና በ2015 ዋንጫውን ከፍ አድርገዋል:: ኢንተር ሚላኖችም በ1964፣ በ1965 እና በ2010 ለሦስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ባለ ድል ናቸው::
የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ እና የእንግሊዙ አርሴናል ግን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አላሳኩም:: አርሴናሎች እ.አ.አ በ2006 ከባርሴሎና ጋር ለፍፃሜ ቀርበው ባርሴሎናዎች ሁለት ለአንድ አሸንፈው የዋንጫው ባለ ድል ከሆኑበት ጨዋታ የተሻለ ውጤት አስመዝግበው አያውቁም::
በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ምንም የአሸናፊነት ታሪክ የሌላቸው አርሴናል እና ፒኤስጂ እርስ በርስ የሚፋለሙ ይሆናሉ:: የአምስት ጊዜ ባለ ክብሮቹ ባርሴሎናዎች ደግሞ ከሦስት ጊዜ ባለክብሮቹ ኢንተር ሚላኖች ጋር እንዲፋለሙ መርሃ ግብር ወጥቶላቸዋል::
አዲስ የአጨዋወት መርሃ ግብርን ያስመለከተን የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማንን ባለ ድል አድርጐ እንደሚጠናቀቅ በቅርቡ የምናውቅ ይሆናል:: እርስዎስ ከባርሴሎና፣ ከኢንተር ሚላን፣ ከአርሴናል እና ከፒኤስጂ ማን ዋንጫውን ያሳካል ይላሉ?::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም