ፍጥነት ማስቀነሻዉ

0
77

በአሜሪካ ፔንስላቫንያ ግዛት የሞንትጐሞሪ ከተማ ባለስልጣናት አሽከርካሪዎች ፍጥነት እንዲቀንሱ ለማስቻል በጐዳናዎች ላይ የተጠማዘዘ (ዚግዛግ)ቅርፅ ቀለም በመቀባት አዲስ ስልት ማስተዋወቃቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

በከተማዋ አውራ ጐዳና ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠማዘዘ ቅርፅ ያለው በግራጫ ቀለም የተቀባ መስመሮችን የተመለከቱ አሽከርካሪዎች ግራ መጋባታቸው ነው የተጠቆመው:: ለዚህም ቀደም ብሎ የነበረው ቀጥታ መስመር በጠመዝማዛ መተካቱን ነው በምክንያትነት ያነሱት:: አሽከርካሪዎችም በሰካራም  የተቀቡ በሚመስሉ ጠመዝማዛ መስመሮች በተለመዱት ቀጥ ያሉ መስመሮች መተካታቸው ግርታን እንደፈጠረባቸው ነው ያረጋገጡት::

የከተማዋ ባለስልጣናት በአንዳንድ የማዘጋጃ ቤት መንገዶች ላይ በፍጥነት በማሽከርከር ሊከሰት የሚችል አደጋን ለማስቀረት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ነው ያብራሩት::

የከተማዋ ፓሊስም ፍጥነት ባልተፈቀደባቸው ጐዳናዎች ላይ በፈጥነት የሚከንፉትን የሚያረጋጋ ርምጃ መሆኑን ነው ያበሰረው፡ በማህበራዊ ድረ ገፆችም ለተነሱ ቅሬታዎች በሰጠው ምላሽም የኗሪዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የተሻለ አማራጭ ርምጃ መሆኑ ነው በአፅንኦት  የተሰመረበት::

የመንገድ ደህንነት ክትትል ምክትል ኃላፊ አኔት ሎንግ አዲስ የተቀቡት ጠመዝማዛ መስመሮች በዘፈቀደ የተቀቡ እንደሚመስሉ ጠቁመው  ጠመዝማዛ የትራፊክ መስመሩ ሆን ተብሎ ታቅዶ መቀየሩን አረጋግጠዋል::

ቀደም ብሎ የፍጥነት መቆጣጠሪያ “ራዳር”፣ የፓሊስ ተሽከርካሪዎችን በየጐዳናዎች ዳር በማቆም ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውጤታማ አለመሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ በመጨረሻ ጠመዝማዛ ወይም በሞገድ ንድፉ መስመሮችን መቀባት ተግባራዊ የማድረግ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ነው ያስታወቁት::

አዲሱ አሽከርካሪዎችን በፍጥነት ከመንዳት ይገታል፣  ይገድባል፣ ያሳስባል በሚል ተግባራዊ የሆነውን ጠመዝማዛ የትራፊክ  መስመር የተመለከቱ ኗሪዎች በርካታ የነቀፌታ አስተያቶችን መስጠታቸውም ተጠቁሟል:: ሆኖም የከተማዋ ባለስልጣናት አሽከርካሪዎች ከአዲሱ የትራፊክ መስመር ጋር እንዲላመዱ አጋዥ ምልክቶች በተወሰነ ርቀት እንዲተከሉ ማድረጋቸው ነው በማደማደሚያነት በድረ ገጹ የሰፈረው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here