ወሳኞቹ ቀሪ ጊዜያት

0
93

ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ሲከታተሉት የቆዩት ትምህርት የሚጠናቀቀው ተማሪዎች በዓመቱ ምን ያህል ብቁ ነበሩ? የሚለውን በፈተና በማረጋገጥ ነው:: በልጅነት አዕምሯቸው የነገ መዳረሻቸውን ቀድመው የተነበዩ፣ ለግባቸው ስኬትም ትምህርት ቤት አዘውትሮ ከመሄድ ጀምሮ የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት በመከታተል፣ ከትምህርት ውጪ ያሉ ጊዜያትንም ለጥናት በማዋል ይከርማሉ::

በእርግጥ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያጋጠሙ፣ እያጋጠሙ ያሉ እና መፍትሔ የራቃቸው በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ከሌሎች ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተዳምረው  ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል:: ቀድሞውኑ በሰሜኑ ጦርነት ወጥነት ከነበረው የተማሪ ምዝገባ፣ የትምህርት አጀማመር እና የፈተና አሰጣጥ ውጪ ሆኖ የቆየው አማራ ክልል አሁንም ጦሱ አልለቀቀውም:: ክልሉ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በግጭት አዙሪት ውስጥ ይገኛል:: ባለፈው ዓመት እንደ ምሥራቅ እና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ከአንድ ሺህ በታች ተማሪዎችን ለፈተና አስቀምጠዋል:: ምዕራብ ጎጃም ዞን ደግሞ በየትኛውም የትምህርት ቤት ደረጃ አንድም ተማሪ  ያላስፈተነ ሆኖ ይነሳል::

የጸጥታ ችግሩ አሁንም የመማር ማስተማሩ ፈተና ሆኖ ዘልቋል:: በክልሉ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች አልሄዱም:: የተማሪ ምዝገባው አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል:: ያም ሆኖ እስካሁን በትምህርት ላይ ያሉትን ተማሪዎች በማብቃት ለትምህርት ምዘና (ፈተና) ብቁ ለማድረግ በበርካታ አካባቢዎች ዝግጅት ተጀምሯል::

የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ በ2017 ዓ.ም 4 ሺህ 429 ተማሪዎችን ለማስፈተን እየሠራ መሆኑን የ2017 ዓ.ም የትምህርት ንቅናቄ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማን ባካሄደበት ወቅት አስታውቋል:: ፈተናው በበይነ መረብ ታግዞ ይሰጣል ያለው መምሪያው ለዚህም ከወዲሁ ተማሪዎችን በክህሎት እና በሥነ ልቦና ከማዘጋጀት ጀምሮ  ለ‘አይሲቲ’ ባለሙያዎች እና ለትምህርት ቤት አመራሮች የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ገልጿል::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም በዓመቱ የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ስድስት ሺህ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያስፈትናል:: የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትበይን ባንቲሁን ለበኲር ጋዜጣ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም በሰጡት መረጃ የቤተ መጽሐፍት አገልግሎትን በሁሉም ቀናት ክፍት በማድረግ ለተማሪዎች የተሻለ ውጤት መመዝገብ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው:: የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት  በተለየ መንገድ እንዲሠጥ ክትትል እየተደረገም ነው ብለዋል:: የሁሉም የትምህርት አይነት ይዘቶች በወቅቱ እና አግባቡ እንዲሸፈኑ፣ ፈተናን በበይነ መረብ ለሚወስዱ ተፈታኝ ተማሪዎች መሠረታዊ የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲኖራቸው በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት መደረጉንም አስታውቀዋል::

“በተማሪ ምዝገባ ያልተሳካውን በውጤት እናካክስ” በሚል መርህ የተጀመረው ሥራ በበርካታ አካባቢዎች በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ናቸው:: የጸጥታ ስጋት ፈተና የሆነባቸው ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የቤተ መጻሕፍት አገልግሎትን እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል:: ቤተ መጻሕፍት ቤቶችን ቅዳሜ እና እሁድ ክፍት በማድረግ ተማሪዎች ይበልጥ እንዲዘጋጁ እያደረጉ ያሉ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ውስን አለመሆኑን ገልጸዋል:: ለአስፈላጊ የትምህርት አይነቶች የተሻሉ መምህራንን በመመልመል ተማሪዎችን የማብቃት ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል:: ቅዳሜ እና እሁድ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርት መስጫ ቀናት ሆነው እየተሠራባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል::

እኛም ተማሪዎች በትምህርት ምዘና ውጤታማ ለመሆን በቀሪ ጊዜያት እንዴት እና በምን አይነት መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች  ያገኘናቸውን ውጤታማ የፈተና ዝግጅት አካሄዶችን እንጠቁማለን::

‘ብሪቲሽ ካውንስል’ የመረጃ አውታር በዓመቱ ሲሰጥ የነበረው ትምህርት ፍሬ አፍርቶ ግቡ ያማረ እንዲሆን በትምህርት ቤት፣ በዞን፣ በወረዳ፣ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ምዘናዎችን በበቂ ሁኔታ ማሳካት ይገባል:: ለዚህም ፈተናዎችን በከፍተኛ ውጤት ለማለፍ  ይበጃሉ ያላቸውን ሐሳቦች አካፍሏል::

እንደ ካውንስሉ መረጃ ከሆነ የፈተናው ቀን ከመድረሱ በፊት ያሉት ሁለት ወራት ለክለሳ ቢሆኑ ተመራጭ ነው:: ነገር ግን የብዙዎች ልምድ ፈተናው ሊደርስ ቀናት ሲቀሩት እንደ አዲስ ወደ ማጥናት ይገባሉ:: ይህ ደግሞ ተማሪዎችን ለጭንቀት፣ ለውጥረት እና ቤተሰብ ለሚፈልጋቸው ተልዕኮ ይሁንታን እንዲነፍጉ በማድረግ በቤተሰብ ግንኙነት ላይ መሻከርን ያመጣል::

አሁን ያለንበት ወቅት የመማር ማስተማር ሥራው እየተጠናቀቀ ስለ ፈተና የሚታሰብበት ነው:: በመሆኑም ቀድመው ጥናት የጀመሩትም ሆነ ያልጀመሩት ቀሪ ጊዜያትን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል:: ለዚህም ለእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት ወቅታዊ የክለሳ ፕሮግራምን ማዘጋጀት፣  የፈተናውን ባህሪ ቀድሞ መረዳት (ጥያቄዎቹ ምርጫ ወይስ በተጻፉ ነገሮች ላይ የተመሠረቱ?) ይገባል::

ብሪትሽ ካውንስል ለክለሳ ይጠቅማሉ ያላቸውን  ሐሳቦችም ጠቁሟል:: ተማሪዎች የተማሩትን የሚከልሱበትን ፕሮግራም ሲያወጡ ከቀኑ ውስጥ ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ጊዜ መምረጥ እንዳለባቸው አጽንኦት ይሰጣል። በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ነጥብ ለሚይዙ የፈተና ዓይነቶች ቅድሚያ መስጠት፣ አዕምሮን ለማደስ አዘውትሮ እረፍት ማድረግ እንደሚገባም በማከል ጠቁሟል::

መጻሕፍትን፣ በድምፅ የተቀዱ መመሪያዎችን እና ኢንተርኔት ላይ የሚገኙ በቪዲዮ የቀረቡ ዋና ዋና ሐሳቦችን ጨምሮ ለማጥናት የሚረዱ የተለያዩ ዝግጅቶችን በመጠቀም ትምህርቱን መከለስ ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳ ጠቁሟል:: በጥናት ወቅት ቁልፍ ነጥቦችን በማስታወሻ መያዝም ፈተናዎችን አሸንፎ ለማለፍ ይረዳል:: ከእያንዳንዱ ርእስ ጋር በተያያዘ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ጥያቄዎች እንዲጠይቁ ማድረግ ይበልጠ ለመዘጋጀት እንደሚያግዝ መረጃው አክሏል::

የጥያቄዎቹን ዓይነት እና የሚመደበውን ሰዓት በተመለከተ ግንዛቤ ለማግኘት ያለፉ ዓመታት ፈተናዎችን መመልከት እና መሥራት ተገቢ ነው:: ይህም በቀጣይ ለሚኖሩ ፈተናዎች የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል::

ጊዜ የሁሉም ዳኛ በመሆኑ  በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው ቤተ መጻሕፍትን በሁሉም የሳምንቱ ቀናት ክፍት እያደረጉ ነው፤ የማካካሻ እና የማጠናከሪያ ትምህርትንም አጠናክረው እየሰጡ ነው:: በተጨማሪም ተማሪዎች ከጓደኘቻቸው ጋር ለማጥናት ከፍተኛ ፍላጎት ይኖራቸዋል:: በዚያ ላይ በዓላት እና ወቅቱ ቤተሰብ የልጆቹን እርዳታ የሚፈልግበት በመሆኑ ጊዜን ከፋፍሎ መጠቀም የብልህ ተማሪ መርህ ነው::

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተማሪዎቹ የጥናት የጊዜ ሰሌዳን አዘጋጅቶ ሰጥቷል:: ተማሪዎቹም አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን ትምህርት ቤቱ አዘጋጅቶ በሰጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ወስነው እያጠኑ ውጤታማ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል:: ተማሪዎች የጊዜ ሰሌዳን ሲያዘጋጁ የቀን ትምህርታቸውን የሚከልሱበት፣ ከመምህራን የሚሰጡ መለማመጃዎችን የሚሠሩበት፣ ወደ ጥናት የሚገቡበት፣ እረፍ የሚያደርጉበትን፣ ቤሰብን የሚያግዙበትን እያንዳንዱን ሰዓት ያካተት ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል:: ተማሪዎች ያወጡትን የጊዜ ሰሌዳ በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ ለመሆን ከቤተሰብ አባል አንደኛው ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርግባቸው ፈቃድ ሊሰጡም ይገባል::

በተጨማሪም ሰውነታችን በአግባቡ ሥራውን እንዲሰራ ኀይል የሚሰጡ ምግቦችን መመገብ፣ ትኩስ እና አነቃቂ መጠጦችን መውሰድ ጥናታችን ውጤት እንዲያስገኝ ያግዝልናል::  ከተንቀሳቃሽ ስልክ እና ትኩረትን ከሚስቡ ነገሮች መራቅም ተገቢ ነው:: አዕምሮ ብሩህ ሆኖ የተሰጠውን እንዲቀበል አረንጓዴ እና ጸጥ ያሉ ቦታዎችን ለጥናት ተመራጭ ማድረግ መልካም ነው:: ለበቂ እንቅልፍ ትኩረት መስጠት፣ መረጋጋት እና በጎ በጎውን ማሰብ ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ ያግዛል:: እኛም መልካም የዝግጅት እና የፈተና  ጊዜ እንዲሆንላችሁ እንመኛለን!::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሚያዝያ 13ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here