በዓላት በለውጥ ውስጥ

0
106

አለቃ ዘድንግራ ማርያም

የዝግመተ ለውጥ እሳቤ ጠንሳሹ ቻርለስ ዳርዊን  ለውጥን በተመለከተ የሚለው ሐሳብ የጽሑፌ መጀመሪያ ይሁን።

“ጠንካራው ወይም  ብልህ ዝርያ  አይደለም በምድር ጸንቶ የሚቀጥለ፤ ለለውጥ ብዙ ምላሽ የሚሰጠው እንጂ” ይላል። የለውጥን ባህሪ ለሚያስተውል ሰው በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ለውጥ ይከሰታል፤ በግድ እና በውድ።

ፈልገው የሚለወጡ ሰዎች መለወጣቸውን በሚሹበት መልካም አቅጣጫ ያደርጉታል። ተገደው የሚለወጡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለውጣቸው ከመብዛት ይልቅ ማነስ፣ ከመኖር ይልቅ መጥፋት መንገዳቸው ይሆናል። ለውጣቸው ስብራት፣ ጉድለት፣ መጣመም አይለየውም።

ቻርለስ የሚለውም ይህን ነው። ለለውጥ ምን ምላሽ እየሰጣችሁ ነው? የሚል ጥያቄን በእዕምሯችን ያጭራል። የለውጥ ማዕበል ብዙዎችን ጠራርጎ አጥፍቷል።

ቀድመው የለውጡን አቅጣጫ አስተውለው በሚፈልጉት መልኩ የተለወጡ ዛሬም ይሁን ነገ በኩራት እና በክብር ይቀጥላሉ። ግን አምና ተለውጫለሁ ብለው ከርሞ ዝም ካሉ ይጠፋሉ። ሁልጊዜም ራሳቸውን በለውጥ ውስጥ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል።

ለውጡን ዝም ብለው የተቀበሉት፣ ራሱ ለውጡ እንደፈለገው የሰራቸውና የለወጣቸው ሰዎች ጉዟቸው ቁልቁል ነው። ማንነታቸው ጠፍቶ መጠሪያ ስማቸው ተረስቷል።

በሀገራችን ብዙ ባህሎች በለውጥ ውስጥ አልፈዋል። ቆመን ለውጥን ራሱ በፈለገው ቅርጽ እና መጠን እንዲያበጀን የፈቀድን ሰዎች እንደሆንን ይሰማኛል። እንደ ሀገር ከዘመናዊነት እሳቤ አንጻር ብዙ ነገራችን በሌሎች ባህል ተተክቷል። መታደስ ያልነበረበት ማንነታችን ታድሷል። መለወጥ ያልነበረበት ቀለማችን ተለውጧል። መጥፋት ያልነበረበት ትውፊታችን ተረስቷል። የባህል ባሕሪ ነውና መወለድ፣ ማደግ እንደገናም አርጅቶ መሞት ወይም መለወጥ አለ። ሙሉ በሙሉ ግን የሚቀይረን መሆን አልነበረበትም። ሕንድ እና ጃፓን ዛሬም ማንነታቸውን ጠብቀው በሰለጠነው ዓለም ውስጥ ዘመናዊ ሆነው ቀጥለዋል። ጸንተን ለመቀጠል የእኛ የሰዎች ድርሻ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ቻርለስ የሚለው ነው።

ሰሞኑን ሚሻ ሚሾ አለፈ አይደል? ይህን በዓል 1998 ዓ.ም እንዴት እንዳከበርሁ ዛሬ  ሳስታውስ በዚህ ፍጥነት እንዴት ሚሻ ሚሾ የሚያከብሩ ሰዎች ቁጥር ቀነሰ? ብዬ እገረማለሁ።

ይህ የሚሻ ሚሾ ጨዋታ ሃይማኖታዊ ትውፊት ያለው ነው። በሰሞነ ሕማማትም የሚደረግ ነው። በዕለተ ዓርብ የስቅለት ቀን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መቀበል በማሰብ ሲከወን ጨዋታው ረጂም ታሪክ አለው። በጨዋታውም ዱቄት፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ጨውና ሌሎችንም በመሰብሰብ አንድ ሰው ቤት ተሰብስቦ ምግብ ይዘጋጃል፡፡ ምግቡ ተዘጋጅቶም ታዳጊ ልጆች በጋራ ሆነው ይበሉታል። በዚህ መልኩ የሚሻ ሚሾን በዓል አክብሬያለሁ።

ቴክኖሎጂ፣ አኗኗር፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ ዘመናዊነት እና ሌሎችንም ምክንያቶች ልንጠቅስ እንችላለን። ምክንያቱ የቱንም ያህል ቢሆን መለወጥ ራሱ በፈለገው አቅጣጫ እየመራን ነው።  ለዓመታት ይከበሩ የነበሩ ቀደምት በዓላት በአዲሱ ትውልድ እየተረሱ ነው።

ያኛው ትውልድ ያስቀጠላቸው ብዙ ባህሎች ዛሬ በነበር የሚጠቀሱ እየሆኑ ነው። ባሕል ማንነት መሆኑን ለሚገነዘብ ሕዝብ የባህሎች መለወጥ ያሳስበዋል። ወደየት ነው የተለወጥነውም ብሎ እንዲጠይቅ ይገደዳል። በተለወጠው ባህል ፋንታ አዲሱ ትውልድ ምን አዲስ ባህል አዳበረ የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው። የገና ጨዋታ፣ ሆያ ሆዬ፣ እንቁጣጣሽ እና ሌሎችም የባህል ጨዋታ በሚያስገርም መልኩ ቅርጻቸውን ቀይረዋል።

የቅርጽ  ለውጥ ስል አንዳንድ ማሳያዎችን አነሳለሁ።  እነዚህን በዓላት የዛሬው ትውልድ በሚመቸው መልኩ ያከብራቸዋል። በቀደመው ዘመን ለማክበር የማይመቹ ሁኔታዎች አሉ። በለውጥ ውስጥ ማለፍ ያመጣው ችግር አንዱ ይህ ነው። እንቁጣጣሽ በዓል በ1990ዎች አጋማሽ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሲከበር የነበረውን መልክ በእህቴ በኩል አስታውሳለሁ።

የድመት ዓይን (ነጭ አበባ) ከመስክ  ፈልጋ ታመጣለች፤ በእንግጫ ጎንጉና ገመድ መሳይ ጌጥ ታዘጋጃለች። ይሄን ይዛ የእንቁጣጣሽ ቀን በጠዋት አያቴ ቤት ትሄዳለች። የአበባ ጉንጉኑ ትልቅ የቤት ምሶሶ ላይ ይታሰራል። የአያቷን ጉልበት ስማ፣ ተመርቃ፣ ምግብ ብልታ ወደ ቤቷ ትመለሳለች።

በዚህ ዘመን ይህን ትውፊት እንኳንስ በከተማ በገጠርም ማግኘት ከባድ ነው። እንግጫው፣ አደይ አባባው፣ ፍላጎቱ ከየት ይገኛል? ይህ ክዋኔ ሃይማኖታዊ ይዘት ቢኖረውም የጨዋታ መልክም አለው። ልጆች በጉጉት ይጠብቁታል፤ ይዝናኑበታል፤ ይጫዎቱበታል። ዛሬ ብዙ የልጆች የጨዋታ አማራጮች አሉ። እነዚህ ጨዋታዎች ቀላል፣ ምቹ፣ ልዩ ልዩ እና ከድሮዎቹ አንጻር ሲታዩ ዘመናዊ ናቸው።

አሁን ከተሞች አካባቢ ያለው የእንቁጣጣሽ አከባበር ምን ይመስላል? ልጆች ወረቀት ላይ አበባ ይስላሉ። ለሰፈር፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ለወላጅ እና ለሌሎች ሰዎች “እንኳን አደረሰህ/ሽ” በማለት ብር ይጠይቃሉ። ብር ተቀብለው ስንት ደረሰህ? ደረሰሽ? እያሉ ታዳጊ ልጆች በዓሉን ያከብሩታል። በዓሉ ከጨዋታ እና መንፈሳዊ ትውፊትነቱ እየተነጠለ ብር መሰብሰቢያ ሲሆን እያየን ነው።

በዚህ ዕለት ሌላም ዓይነት ገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ በቅርቡ ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል። ሻሽ በትልቁ የጠመጠሙ  ወጣት የአብነት ተማሪዎች ከበሮ እየመቱ፣ እየዘመሩ በየቤቱ እየገቡ ብር ይለምናሉ። መዝሙር በማቅረብ ገንዘብ መጠየቅ ምንም የእምነት ይሁን የባህል እሴት የለውም፤ በበዓል ስም መነገድ እንጂ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህን አካሄድ ከእኔ አስተምሮ ውጪ ነው ስትል አውግዛለች።

የገና ጨዋታን በተመሳሳይ ብንመለከት ገንዘብ ፍለጋ ላይ ትኩረት አድርጓል። ከዓመታት በፊት እኔም የገና ጨዋታን በመጠቀም ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ማግኜቴን አስታውሳለሁ። አሲና ገናዬ እያልን በየቤቱ እንዞራለን። ሰው እንደ አቅሙ ብር ይሰጠናል። ከዚህ ቀደም የነበረው መዝፈን ነበር። ሰፊ መስክ ላይ በቡድን ተከፋፍሎ ገና መጫዎት ነበር። በእኔ ልጅነት እና አሁን ያለውም ቢሆን ከገንዘብ የተላቀቀ አይደለም።

የገና ጨዋታን በድሮው  መንገድ ለማስኬድ ብዙ ችግሮች ይኖራሉ። መጫዎቻ ሜዳው፣ ሩሩ፣ ገናው እና ሌሎች ብዙ የጨዋታው ድባቦች አሁን የሉም። የገና ጨዋታ በባሕል ስፖርትነት ተመድቦ በዓመት አንድ ጊዜ ይደረጋል። የሚጫዎቱትም የኪነት ቡድን አባላት እና ትያትር ተጫዋቾች በመሆናቸው ባሕሉ መሰረቱን የያዘ አይደለም። ይህ በመሆኑ ባህሎች ከሕዝቡ  ልቦና እንዲነጠሉ ያደርጋል።

የልጃገረዶችን ጨዋታ መንግሥት ማክበር መጀመሩ ባህልን የፖለቲካ ማድመቂያ አድርጎታል፤ መንግሥት ማክበሩን ሲተው በዓሉ ተቀዛቅዟል ያሉ አንድ አባትን ንግግር አስታውሳለሁ።

በዓላት በየደጁ እና ቤቱ መከበር ሲገባቸው ሕዝቡ ወደ አንድ ማዕከል መሰብሰቡ ባህልን ለሌላ አሳልፎ ይሰጠዋል ብለው ነበር እኒያ አባት የተናገሩት። የልጃገረዶች በዓል በየትኛውም ሁኔታ ሲከበር ቆይቷል። በመንግሥት ሌሎች ጉዳዮች ስራ በዝቶበት ሳያከብረው ሲቀር ጉዳዩን መንግሥት የሚያከብረው እስኪመስል ድረስ አከባበር ይቀዘቅዛል። በዓሉን የፖለቲካ ንግግሮች ማድመቂያ ማድረግ በበዓሉ ንጽሕና ላይ ችግር ይፈጥራል።

የሆያ ሆዬ ጨዋታም “የእኔማ ጋሽዬ” እያሉ ገንዘብ ለመቀበል ግጥም ከመደርደር ባሻገር ከትውፊቱ ወርዷል።  የእኔ ትዝብት በዓላት ነባር ትውፊታቸውን ትተው ገንዘብ ማግኘት ላይ አተኮሩ፤ ጉዟችን ወደየት ነው፤ በገንዘብ የሚመራ ባሕል መዳረሻ የት ይሆን? የሚል ነው።

እነዚህን በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ ሌሎችም በዓላት ወደ ገንዘብ መሰብሰቢያነት እና “ፌስቲቫል” ነት እየተለወጡ ነው። የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ነው። መዝሙር እና ስብከት ማውጣት፣ ማቅረብ ሲገባ ወቅቱን ጠብቀው የሚቀርቡት ወጣቱን ወደ መጠጥ እና ጭፈራ ቤት የሚመሩት ሙዚቃዎች ናቸው።

እውነታው ምንድን ነው? በዓላት ሲኖሩ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚፈጥረው የቱሪስት ፍሰት አለ።  ይህም ገንዘብ ያስገኛል። ለብዙዎች የስራ እድል ይፈጥራልም። ቢሆንም ግን ገንዘብ ለማግኘት በተቀደሱ ቀናት መርከስ ተገቢ አይደለም። የመስሕብ  ስፍራዎች ማስተዋወቅ፣ ጤናማ ገቢ ማግኘት፣ የሃይማኖት ኮንፈረንሶችን ማድረግ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል። ፋሽን እየሆነ የመጣው ግን በዓላትን ለፍቅር ቀጠሮ እና ልቅ ወሲብ መፈጸሚያነት መጠቀም ነው።

የባህል አረዳድ እና ክዋኔ ክፍተት ተፈጥሯል። ትላልቅ ሰዎች ለበዓሉ የሚጠየቁትን ገንዘብ መስጠት ቢሰለቻቸውም  እንኳን ሌላ የተሻለ አከባበር አልተፈጠረም፤ አሮጌው መቀጠል አልቻለም።  “ይህን ገንዘብ መለመን ባህል ብላችሁ¡ ባህል በእኛ ጊዜ ቀረ¡ የዘንድሮ ልጆች ምኑን አውቃችሁት?” እና ሌሎች መሰል ትችቶች በቀደመው ትውልድ አባላት ዘንድ ይነሳሉ።

የዛሬው ትውልድ ደግሞ በዓለማቀፋዊነት ወጀብ ግራ ተጋብቶ ባህል፣ ትውፊት ዘመናዊነት ተዘበራርቀውበት በመወዛገብ ውስጥ አለ። የትውልድ ክፍተት ተፈጥሯል። አባት እና ልጅ በበዓላት አከባበር ላይ አይስማሙም። በምን ይታረቁ? አባት ለልጁ ባህሉን አላወረሰም። ልጅም የአባቱን ባህል ወርሶ ማስቀጠል አልቻለም። የማይችልባቸው ችግሮች ገጥመውታል።

ልጆች፣ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ መሪዎች ይህን መሰል ትውፊቶች እንዲቀጥሉ ምን አደረጉ? ይህን ክፍተት መሙላት ወይም ዘመኑ በፈለገው መስመር መቀጠል ምርጫችን ነው። ቻርለስ እንዳለው የምንሰጠው ምላሽ መዳረሻችንን እና ሕልውናችንን ይወስናል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here