የኃያላኑ  ፍጥጫ

0
86

የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ ታሪፍ እና ሌሎች የንግድ ማዕቀቦችን መጣል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በሁለቱ ኃያላን መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግጭት እ.አ.አ ከጥር 2018 ጀምሮ የቀጠለ ነው፡፡

የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከያዙ በኋላ በተወሰኑ ሀገራት እና ሸቀጦች ላይ የሚጣሉ የቀረጥ ዝርዝሮች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት  የአሜሪካን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተናገሩት። የቅርብ ጊዜዎቹ የታሪፍ ጭማሪዎች ደግሞ ዓለም አቀፍ ምላሽን በማቀጣጠል ገበያዎች እንዲያሽቆለቆሉ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድቀት ያስከትላል የሚል ስጋትም ጨምሯል።

የትራምፕ አስተዳደር ለአብዛኛዎቹ ሀገራት ከፍተኛ ታሪፍ ማወጅን መሠረት ያደረገ የንግድ ፖሊሲ ለውጥ አድርጓል። የ10 በመቶዉ ዓለም አቀፍ ታሪፍ እንዳለ ሆኖ የታቀደው የሀገር ውስጥ ታሪፍ ጭማሪ ከቻይና በስተቀር ለ90 ቀናት ታግዷል፡፡

ዘ ኮንቨርሴሽን እንደዘገበው እ.አ.አ በ2024 ከአሜሪካ ወደ ቻይና የሚላከው ትልቁ የሸቀጦች ምድብ አኩሪ አተር ነበር፡፡ ይህም በዋነኛነት የቻይናን 440 ሚሊዮን አሳማዎች ለመመገብ ይጠቅማል። በተጨማሪም አሜሪካ ወደ ቻይና መድኃኒትና  ፔትሮሊየምን ትልካለች። በሌላ መንገድ ከቻይና ወደ አሜሪካ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ኤሌክትሮኒክስ፣ኮምፒውተሮች እና መጫወቻዎች ይገባሉ፡፡ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች  አስፈላጊ  የሆኑት ከፍተኛ መጠን ያላቸው ባትሪዎችም ወደ አሜሪካ ይላካሉ። ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡት (ትልቁ ምድብ) ስማርት ስልኮች ሲሆኑ ከጠቅላላው ዘጠኝ በመቶ ይሸፍናሉ። ከእነዚህ ስማርት ስልኮች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የቻይና አፕል  በአሜሪካ ደረጃ የተሠራው ነው፡፡ በቻይና ላይ የተጣለው የአሜሪካ ታሪፍ በ20 በመቶ ለአፕል የገበያ ዋጋ ማሽቆልቆል ምክንያት አንዱና ዋነኛው ነው።

የትራምፕ አስተዳደር ቀደም ሲል በቤይጂንግ ላይ በጣለው የ20 በመቶ ታሪፍ ምክንያት ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡት እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ለአሜሪካዊያን በጣም ውድ ሆነዋል። አሁን ታሪፉ ወደ 125 በመቶ እና ለአንዳንድ ምርቶች ደግሞ እስከ 145 በመቶ በመጨመሩ ተፅዕኖው በስድስት እጥፍ አድጓል፡፡

የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋም የጂ ፒ ሞርጋን ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ፌሮሊ በተቋሙ ድረገጽ //www.jpmorgan.com/ ላይ ባሰፈረው መረጃ እንዳለው  የአሜሪካ የሰሞኑ እርምጃ  የታሪፍ  መጠንን ይጨምራል። ነገር ግን ከቻይና  የሚገቡ ምርቶች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል። እንዲሁም  የቻይናን 2025 የሙሉ ዓመት  ዕድገት ወደ አራት ነጥብ አራት በመቶ ይቀንሳል፡፡

አንዳንድ ሀገራት የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገራት ላይ እየጣሉት ላለው ተጨማሪ ታሪፍ አጸፋ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ አጸፋ ከሰጡ ሀገራት መካከልም ቻይና አንዷ ናት፡፡

ለአሜሪካ የመልስ ምት እጇ የማይዝለው ቻይና  በመጀመሪያ ላይ ያደረገችውን የ34 በመቶ ጭማሪ በማጤን በአሜሪካ ላይ የምትጥለውን የታሪፍ ጭማሪ አሁን ላይ 125 በመቶ አድርሰዋለች። አሜሪካ የጀመረችውን የንግድ ጦርነት የምትቀጥልበት ከሆነም ቻይና እስከመጨረሻው ለመፋለም መዘጋጀቷን ነው  ቢቢሲ የዘገበው፡፡

የአሜሪካ ታሪፍ ጭማሪዎች  በዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ቻይና ባልተጠበቀ ሁኔታ አዲስ የንግድ መልዕክተኛ ሾማለች። የተሾሙት ደግሞ የቀድሞ የንግድ ሚኒስቴር ረዳት እና የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አምባሳደር ሊ ቼንግ ጋንግ ናቸው፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ቻይና አሜሪካ የጣለችባትን ከፍተኛ ታሪፍ  ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ አስጠንቅቃለች። ይህን የአሜሪካ ውሳኔ ተከትሎ የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ትክክለኛውን የጋራ ተጠቃሚነት መንገድ ለመመለስ አሜሪካ ስህተቷን ማረም ይጠበቅባታል ብሏል፡፡

ከሰሞኑ ዶናልድ ትራምፕ በቻይና የሚመረቱ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከታሪፍ ነጻ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና  የአሜሪካዉ የንግድ ሚኒስቴር  እንዳስታወቁት እንደዚህ ዓይነቶቹ ውሳኔዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ናቸው።

እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ በእነዚህ ምርቶች ላይ በተለየ ሁኔታ የታሪፍ ጭማሪ የሚደረግ ሲሆን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጭማሪው ይፋ ይደረጋል። አሜሪካ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በአሜሪካ እንዲሠሩ ትፈልጋለች፤ ሆኖም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ ቀርቷል መባሉ “ሐሰት” መሆኑንና  በአንጻሩ የተለየ የታሪፍ ሥርዓት እንደሚዘጋጅላቸው ማሳወቃቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

አሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ የምታደርገው ከሀገራት ጋር  የተሻለ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት በማሰብ መሆኑን አስታውቃለች፡፡ ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ ያለው ንግድ ‘የተዛባ’ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ታዲያ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ሀገራቸው  የንግድ ሥርዓቱን ማስተካከል፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ፋብሪካዎችን ወደ አሜሪካ መመለስ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እንደምትሠራ ነው የገለጹት፡፡ ይሁንና የትራምፕ ታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካ የአክሲዮን (ስቶክ) ገበያ እንዲዋዥቅ ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው።

በተያያዘም የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን የአውሮፓ ሀገራትን ወክለው ባደረጉት ንግግር  ታሪፉ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ በተለይም ጣሊያንን፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ከሌሎቹ በበለጠ በታሪፉ ተጎጂ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ዘ ኮንቨርሴሽን እንደዘገበው የአሜሪካ – ቻይና የንግድ ጦርነት ወይም የኢኮኖሚ ግጭት የተጀመረው እ.አ.አ በ2018 ነበር፡፡ በወቅቱ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 45ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡበት ጊዜ ነበር፤ ታዲያ በመጀመሪያዉ የፕሬዝደንትነት ጊዜያቸው ሀገራት ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጥለዋል።

ፕሬዚዳንቱ እ.አ.አ በ2018 ከጥር 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱ በተለይ ብረት፣ ማጠቢያ ማሽኖች፣ባትሪዎች፣ አሉሚኒየም፣ የአውሮፕላን ክፍሎች እና መሰል ምርቶች ታሪፍ የተጣለባቸው ነበሩ፡፡

ብዙ ሀገሮች በትራምፕ ውሳኔ (ተፈጻሚነቱ የዘገየውን) ላይ የአጸፋ ምላሽ ላለመስጠት የመረጡ ቢሆንም፣ ይልቁንም ድርድር እና ውይይትን ደግፈዋል፤ ቤይጂንግ ግን የተለየ እርምጃ ወስዳለች።

ዘ ኮንቭርሴሽን እንደገለጸው ቻይና ለአሜሪካ የንግድ ውጥረት የሰጠችው ምላሽ በአፍሪካ ፖሊሲዋ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ የሁንና ሀገሪቷ የቻይና – አፍሪካ የንግድ ጥረቶችን ለማበረታታት አዳዲስ እርምጃዎችንና ፖሊሲዎችን አስተዋውቃለች። ፖሊሲው በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here