“ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው የሚገለጠው የውጭ ጠላት በወረራቸው ወቅት ነው” የሚለው እውነታ ለምን የውስጣዊ ሕብረታችን መታወቂያ አልሆነም? የሚል ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ የሰላም እጦቶች ሀገሪቱ ከፍታዋን ዕውን ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለማይደግፉ የውጭ ሀገራት ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው ይመስላል፡፡ ለዚህም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይሉ በየጊዜው የሚያወጣቸው መግለጫቸው እማኝ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን ለመፍታት የተለያዩ የሰላም ጥረቶችን ስታካሂድ ኖራለች፡፡ በቅርቡ የተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከእነክፍተቱም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ስምምነት መነሻውን የትግራይ አድርጎ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያካለለው የሰሜኑ ጦርነት እንዲያበቃ የተደረገ የሰላም ጥረት ነው፡፡
ጦርነቱ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት፣ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት፣ ማኅበራዊ ምስቅልቅ እና ለሥነ ልቦናዊ መላሸቅ ዳርጎ ማለፉ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለመስጠት ለኢትዮጵያ መልካም ጅማሮ ቢሆንም ሀገራዊ ሰላምን ግን ሊያመጣ አልቻለም፡፡
ስምምነቱ ከተፈጸመ ከአንድ ዓመት በኋላ የሰሜኑ ጦርነት መልኩን እና ባህሪውን ቀይሮ በአማራ ክልል ተቀስቅሷል፡፡ ክልሉ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የደረሰውን ጉዳት በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል የምክክር መድረክን በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅ ተመላክቷል፡፡ ይህም የሰሜኑ ጦርነት ክልሉን ለ522 ቢሊዮን ብር ጉዳት ከዳረገው ጋር ሲታይ ጦርነቶች እና ግጭቶች የአማራ ክልልን ብሎም ኢትዮጵያን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለመፈናቀል ዳርጓል፡፡ ከማኅበራዊ መስተጋብር መገለልን አስከትሏል፡፡ ከአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ታዳጊዎች የነገ ሕልም አጨናግፏል፡፡ የታመሙት በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይታከሙ፣ አምራቹ፣ ኅይሉ እና ነጋዴው… ምርቶችን ያለ ስጋት ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ አድርጓል፡፡ ይህን ተከትሎ የተከሰተው የኑሮ ውድነትም የዜጎች ፈተና እንዲሆን ምክንያት ሆኖ ይነሳል፡፡ እገታ፣ ዝርፊያ እና ውንብድና የዜጎችን ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ ውሎ ለመግባት፣ አድሮ ለመገኘት… ፈተና ሆኖ ቀጠሏል፡፡
“አሁን መፍትሔው ምን ይሁን?” የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ በሐሳብ ፍጭት የጥል እና የቀውስ ምክንያቶችን ለይቶ ምቹ መኖሪያን ለመፍጠር ብዙዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መድረክ አንደኛው የመፍትሄ መንገድ ነው፡፡
የምክክር ኮሚሽኑ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መምጣት ችግሮችን እየለየ ይገኛል፡፡ ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍን አካሂዷል፡፡
በምክክሩም ከአሥር የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ4 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች የአጀንዳ ልየታ ማከናወናቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በመጨረሻም እነዚህ የማኅበረሰብ ተወካዮች አጀንዳቸውን ለይተው “ይወክሉኛል፤ ሐሳቤንም እስከ መጨረሻው ያደርሱልኛል” ያሏቸውን ወኪሎቻቸውን በመምረጥ አጠናቀዋል፡፡
የማኅበረሰብ ተወካዮቹ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር በሁለተኛው ዙር በመወያየት እና መሠረታዊ የአማራ ሕዝብ አጀንዳ ናቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች በመለየት ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል ቴዎድሮስ ዘውዱ (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡ ነዋሪነታቸው በውጭ ሀገር ቢሆንም የአማራ ክልል ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ካለበት ግጭት እንዲወጣ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ለማዋጣት በምክክሩ ተገኝተዋል፡፡ እንደ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) የአማራ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ሳይሳተፍባቸው የተላለፉ በርካታ ውሳኔዎች ዛሬ ላይ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ገዥ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሀገራዊ ችግሮችን ለይቶ ሥር ነቀል መፍትሔ ለመስጠት እያከናወነ ያለው ሂደት መልካም ዕድል መሆኑንም አንስተዋል፡፡ አካሄዱም ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥ እና ነጻ ውይይትን የሚከተል በመሆኑ ወደ ፊት በሕገ መንግሥቱ ላይ ይነሳ እንደነበረው አይነት ጥያቄ እንዳይነሳ ሁሉም በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
ታጥቀው ጫካ የገቡ እና በተለያየ ምክንያት የቀሩ ወንድሞች በምክክሩ በአካል በመገኘትም ሆነ ሀሳባቸውን በጽሑፍ በመላክ እንዲሳተፉ ጥሪ መደረጉ እና ዕድሉ መመቻቸቱ ሀገራዊ መፍትሔ ለማግኘት ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ዕድል መጠቀም ለነገ የማይተው የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አቶ ገብሬ ከፍያለው የሀገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ተከስተው ማለፋቸውን፣ አሁንም እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ዜጎችን ችግር ላይ የጣሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የችግሮች ማብቂያ ጊዜ ከዚህ በላይ መርዘም እንደሌለበት ሲገልጹ፣ ዋናው መንገድ ምክክር መሆኑንም አንስተዋል፡፡ “ሀገር የምትቆመው በምክክር፣ በውይይት፣ በይቅርታ እና በእርቅ ነው” ብለዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ አጀንዳዎች በሰላማዊ መንገድ በኢትዮጵያ ማእቀፍ ለመፍታት የሚያስችል አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ለግጭት ምክንያት የሆኑ እና ለዘመናት ሲታገሉባቸው የነበሩ ችግሮችን ነቅሰው በምክክር ኮሚሽኑ እንዲመከርባቸው እና ድርድር እንዲደረግባቸው የሚያስችል ማዕቀፍ ውስጥ ማስገባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በአጠቃላይ ሂደቱ ሁሉንም ያካተተ፣ ፍትሐዊ፣ ተስፋ የሚጣልበት፣ ነጻ እና ገለልተኛ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለእረጅም ጊዜያት በብዙ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ ችግሮች ውስጥ አልፈናል፡፡ እነዚህን ችግሮች እንደ ኢትዮጵያዊ አንድ ላይ ቁጭ ብለን እንዳንነጋገር ዛሬ ላይ ለክፋት የተጫጨነው ለምንድን ነው? ምንስ ሆነን ነው? ብለን የምጠይቅበት ጊዜ አሁን ነው ብዬ አምናለሁ!” ሲሉ የወቅታዊ ሁኔታውን አሳሳቢነት አስድተዋል፡፡
አምባዬ(ዶ/ር) “ወንድም ወገኑን ለምን ይገድላል? ለምንስ ያሳድዳል?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “ለመዝመት እና ለመዋጋት እንደምንደፍረው ሁሉ አሁን ደግሞ ቆም ብሎ በስክነት አንዱ የሌላውን ቁስል፣ ችግር፣ ስጋት እና ተስፋ ለመደማመጥ የምንደፍርበት ወሳኝ ወቅት ነው?” በማለት ስለ ምክክሩ አስፈላጊነት ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል እና የበርካታ ፍላጎቶች ባለቤቶች ናቸው” ያሉት አምባዬ (ዶ/ር)፣ በጋራ የሚያገናኙ መንገዶችን ለመቅረጽ መነጋገር እና መደማመጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ “ለኢትዮጵያውያን ህመም እና ቁስል ፈውስ ልናመጣ የምንችለው እኛው ኢትዮጵያውያን ነን!” በማለት ሁሉም ስለ ሀገሩ የሚመለከተው ሁሉ የልዩነት ምክንያቶችን በመነጋገር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ደግሞ “ኢትዮጵያ ከተደጋጋሚ ግጭት የምትወጣው ችግሮችን በምክክር ለይቶ መፍትሔ መስጠት ሲቻል ብቻ ነው” ይላሉ፡፡ ለዚህም የአማራ ክልል ሕዝብ ለነገ ሰላሙ ዛሬ ላይ የችግሮችን ምንጭ ለመለየት ወቅታዊ ችግር ሳይበግረው በምክክሩ በመሳተፉ አመስግነዋል፡፡
ምክክር የአንድ ወገን ሐሳብ ብቻ የሚወሰድበት ሳይሆን በየደረጃው ያለው ሁሉም አካል ያለምንም ፍርሀት እና ስጋት ለሀገር ይበጃል የሚለውን አጀንዳ የሚያዋጣበት ቀዳሚው የሰላም መንገድ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ “ማንም ባለ ሥልጣንን ፈርቶ እና አስቀድሞ ለሀገሩ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስንበትን ሐሳብ የጋን ውስጥ መብራት እንዲሆን መፍቀድ የለበትም!” በማለትም አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል፡፡
“በምክክር አሸናፊው ሁሉም ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በመሆኑም ቅድሚያ ለማሸነፍ ሳይሆን ለመግባባት መወያየት እና መነጋገር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ለተሻለ ሐሳብ መደማመጥ ዋናው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባም አስምረውበታል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ሀገር የምትድነው በምክክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች አልተግባባንም፤ አሁንም የሐሳብ ልዩነቶች ደም እያፋሰሱን ነው፤ አሁን ግን በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ደም መፍሰስ መቆም አለበት፤ ለዚህም ምቹ ሁኔታው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የፈጠረው የአንድነት መድረክ ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ውጥንቅጥ ሁኔታ ወጥታ ለዛሬው እና ለነገው ትውልድ ብሩህ ተስፋን ለማስረከብ የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን በመመለስ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ግብ ሆኖ እየተሠራ ነው፡፡ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የሕዝብ ችግሮችን በውስጣዊ አቅም መፍታት፤ ለዚህም ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባህልን ማዳበር የኮሚሽኑ ዋና ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት በመፍጠር ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት እንዲኖራት ምክንያት መሆን ይፈልጋልም ብለዋል፡፡ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እና ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚጠበቁ ውጤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
“እኛ እያልን ያለነው በንግግር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት በመፍጠር የኢትዮጵያን ከፍታ ዕውን እናድርግ ነው! ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት አብረውን እንዲሠሩ እንፈልጋለን! ከዚህ ውጪ የሚፈለገው እና የሚጠበቀው ምንድን ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም