“ሰውን ያለ ምክንያት  መውደድ እንልመድ”

0
114

ሊቀ ሊቃውንት ስምአ ኮነ መልዓክ

የተወለዱት ከፍኖተ ሰላም ከተማ በቅርብ ርቀት  በምትገኘው አውንት ሚካኤል ቀበሌ ነው:: በአካባቢያቸው የዘመናዊ ትምህርት መሰጠት ባለመከፈቱ የአብነት ትምህርት ጀምረዋል:: አባታቸው የቤተ ክህነት መምህር መሆናቸው ወደ አብነት ትምህርቱ እንዲገቡ ዋነኛው ምክንያት ነበር:: በጎጃም፣ በጎንደር እና በሰሜን ሸዋ ተዘዋውረው የአብነት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል- ሊቀ ሊቃውንት ስምአ ኮነ መልዓክ:: ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልዓክ በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የአራቱ ጉባኤያት መምህርም ናቸው:: በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ ዙሪያ የሚከተለውን  ቆይታ አድርገናል::

መልካም ንባብ!

ያሳለፍነው የዐቢይ ጾም ነበር:: ለመሆኑ ጾም ምንድን ነው?

ጾም  ተወ፣ ታቀበ፣ ታረመ የሚል ትርጉም ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ነው:: የቃሉ ፍችም ከምግብ ወይም ከሌላ ነገር  መከልከል መጠበቅ ማለት ነው::  ሰውነትን ከመብል እና ከመጠጥ ከሌላውም ክፉ ነገር ሁሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቆጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እና እሱንም ደጅ መጥናት፣ ማረኝ ይቅር በለኝ በማለት ቅድመ እግዚአብሔር በመንበርከክ ምሕረትን ከአምላክ ለመቀበል መዘጋጀት ነው:: በቅድስቲቱ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቱ በልኬት እና በምክንያት የታጀበ ነው። ጾምን ስንመለከት አብዛኞቻችን በተለምዶ ሰዓት ሳንጠብቅ (እስከ 3፣ 6፣ 7፣ 9፣ 11 ሰዓታት እያልን) እንጾማለን እንጂ የአዋጅ አጽዋማት የተወሰነ የተገደበ ሰዓት አላቸው።

ጾም ለዘላለም ሁሉንም ሕዋሳት ከኃጢአት መከልከል፣ ለተወሰነ ጊዜ እህል ከመብላት፣ ዉኃ ከመጠጣት መታቀብ ወይም ለተወሰኑ ወራት ከጥሉላት ከሥጋ፣ ከወተት፣ ከቅቤ፣ ከእንቁላል፣ በአጠቃላይ ከእንሰሳት ዉጤት መከልከል ነው።

እስክንድር የሚባል ፈላስፋ አምስቱን የስሜት ሕዋሳት የልብ መስኮቶች ይላቸዋል:: ጾም ማለት በእነዚህ መስኮቶች የሚገባውን አጉል ወይም ሃጺያት የሆነ ነገር ሁሉ መከልከል ነው::

ጾም  የሥጋ ምኞትን የምታጠፋ፣ የነፍስን ቁስል የምታደርቅ፣ ለጎልማሶችም ጸጥታን እና እርጋታን የምታስተምር ከእንሰሳዊ ግብር ጠባይ የምትከለክል እና ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባት ደገኛ ሥርዓት ነች::

በብሉይ ኪዳን ብዙ ሰዎች በጾም ተጠቅመዋል:: እግዚአብሔር የጾምን ሥርዓት የደነገገው ገና ከጥዋቱ አዳምን በፈጠረበት ወቅት ነው:: “እጸ በለስን አትብላ!” ማለት ትዕዛዝ ቢሆንም ትዕዛዙ ግን የጾም ትዕዛዝ ነው፤ አዳም እና ሔዋን ይህን የጾም ሥርዐት በመሻር እጸ በለስን በልተው በመገኘታቸው ምን እንደደረሰባቸው በቅዱስ መጽሐፍ ላይ የምናነበው ነው:: በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳን አበው ጾምን “የጸሎት እናት፣ የእንባ ምንጭ፣ የጽድቅ መሠረት፣ ደገኛ ሥርዓት” በማለት ይገልጻሉ::

 

ዐቢይ ጾም ምንድን ነው?

በመጀመሪያ ‹‹ዐቢይ›› የሚለው ቃል ‹‹ዐበየ›› ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው:: ትርጓሜውም ‹‹ከፍ አለ›› ማለት ነው:: ዐቢይ ጾም ዐቢይ የተባለበት ሦስት ዐበይት ምክንያቶች አሉ:: ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጾመው ሥለሆነ፣ በቀኑ ቁጥር ከሌሎች አጽዋማት ስለሚበልጥ የቀኑ ብዛትም 55  ነው:: ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች እንዲሁም ደግሞ ሦስቱ ርዕሰ ኃጢአት የሚባሉት ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ነዋይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል የተመቱበት ስለሆነ ይህ ጾም ዐቢይ (ታላቅ) ተብሏል::

ዐቢይ ጾም በያዛቸው 55 ቀናት ውስጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሁዶች አሉ:: እነዚህ ስምንት እሁዶች የተለያየ ስያሜ አላቸው:: ስያሜአቸውንም የሰጣቸው የቤተ ክርስቲያናችን የዜማው ሊቅ  ቅዱስ ያሬድ ነው:: እነሱም ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብረ ሔር፣ ኒቆዲሞስ ፣ መጻጉዕ እና ሆሳዕና ናቸው::

በጾም ወቅት ምዕመኑ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?

ብዙ ጊዜ በጾም ወቅት የምንጨነቀው ከምግብ እና ከመጠጥ ለመራቅ ነው:: ነገር ግን አፍ እና ሆድ ብቻ ሳይሆን ልብም ንጹህ መሆን አለበት:: ወደ አፍ የሚገባው ብቻ ሳይሆን የሚወጣውም መጾም አለበት:: በቅዱስ መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የሚገባው ብቻ ሳይሆን የሚወጣውም ጭምር ነው ይላል:: ከአፍ የሚወጣው ማለት ስርቆት፣ ዝሙት፣ ጸብ የመሳሰሉ መጥፎ ምግባሮችን ነው:: ጠላትህን ውደደው፤ ልትበቀለውም፤ ከፈለክ ዝም በለው፤ እግዚአብሔር  ይጎዳዋል:: በመሆኑም በጾም ወቅት ጠላትህን በመውደድ፣ ከቂም እና ከበቀል በመራቅ፣ በመልካም ልብ መጾም ያስፈልጋል::

ክርስቶስ ጾሙን የጾመው ለሰው ነው፤ እኛም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መጾም አለብን:: ከምግብ የምትከለከለው ያ ልትበላው የነበረው ምግብ ለሌላ ለተቸገረ ሰው እንዲሆን ነው:: በመሆኑም ሌሎችን በመርዳት፣ በመንከባከብ እና አለሁ በማለት ምዕመኑ ጾሙን ማሳለፍ አለበት:: ይህ ምግባር ደግሞ ጾሙ ከአለቀ በኋላም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል::

አንድ ክርስቲያን በዚህ ዓለም የተተወበትን ምክንያት ማወቅ አለበት። የአባታችን መንግሥት በሰማይ ሆኖ ሳለ እዚህ ምን እናደርጋለን? ሀገራችን በሰማይ ነው እንላለን፤ ነገር ግን በምድር እንኖራለን። የእኛ ባልሆነ ምድር የተተውንበት ዓላማ እኮ ነግደን እንድናተርፍበት የተሰጠን መክሊት በመኖሩ ያንን እስክናረባ ድረስ ነው። መክሊታችንን ባረባነው ልክ ሊሾመን እና ሊሸልመን ስለሚፈልግ በዚህ ዓለም ትቶናል እንጂ እንዲሁ የተወን አይደለም።

ሐዋርያትን ትቷቸው ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ “እስከ ዓለም ዳርቻ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚል ትዕዛዝ የሰጣቸው መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። ጌታ እስኪመጣ እርሱ ወዳለበትም እስኪወስደን ድረስ ለእያንዳንዳችን ሥራ ሰጥቶናል። ሲመጣ የምንመልስለትን መልስ ሳይሆን በፊቱ የምናቀርበውን የመክሊታችንን ትርፍ ማኖር ይገባናል።

ከሁሉም ሰው ጋር ፍቅርን አድርጉ። ሰውን ለመውደድ ምክንያት አታብጁ። ክርስቶስ አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን “ወዳጄ” ብሎ ጠርቶታልና:: እግዚአብሔር እኛን ያለ ምክንያት እንደ ወደደን እኛም ያለ ምክንያት ሰውን መውደድ እንልመድ። ክርስቶስ እኛን ጠላቱ ሆነን ሳለ ፍቅርን ካላጎደለብን ለጠላታችን ፍቅርን አናጉድልበት። ክርስቶስ ይሁዳን “ወዳጄ’’ ብሎ ከጠራው እኛም ይሁዳዎቻችንን ወዳጄ ብለን እንጥራቸው።  ጠላትን መውደድ መራራ ሐሞትን ከመጠጣት በላይ መራራ ነው። ነገር ግን  ለይሁዳዎቻችን ፍቅርን እንስጥ፤ ይህም መራራ ሐሞት የጠጣ ክርስቶስን እንድንመስለው ነው። ለሁሉም መስጠት በምትችሉት መጠን እንስጥ እንጅ አንቀበል። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነውና፤ በመስጠታችን ብፁዓን ተብለው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገቡት እንቆጠራለን።

የዐቢይ ጾም ካለቀ በኋላ ትንሳኤ ይበሰራል፤ ትንሳኤ ምንድን ነው?

ትንሣኤ ተንስአ- ተነሣ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው:: ይኸውም የሰው ልጅ ሞቶ ሥጋው ፈርሶ በስብሶ እንደማይቀር እና በዳግም ምጽአት ጊዜ እንደሚነሣ የሚያመለክት ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቁ ምክንያት የሞት ሞት ተፈርዶበት ነበረ:: “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” ተብሎ ነበርና::  በዚህም ምክንያት ከአቤል ጀምሮ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ የሰው ልጅ በሥጋ የሚሞት ሆኗል:: ነገር ግን እንደሞትን አንቀርም:: ሁላችንም ትንሳኤ አለን:: ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት የትንሣኤያችን በኲር ሆኖናልና::

“ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል›› እንዲል፣ ዘለዓለማዊ ሞታችን እና ፈርሶ በስብሶ መቅረት የቀረልን አካላዊ ቃል ሥጋችን ተዋሕዶ ሰው ሆኖ ሞትን በሞቱ ድል ከነሣልን በኋላ ነው:: ሊቁ ሱኑትዩ በሃይማኖተ አበው  ሞትን በሞቱ ያጠፋልን ዘንድ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ የእኛን ሞት ሞተ ብሎ እንደገለጠው:: “ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ” ያለ ጌታ በጥንተ ትንሣኤ መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ::

የክርስቶስ ትንሣኤ ከአልዓዛር ትንሣኤ የተለየ ነው:: አልዓዛርን ያስነሣው ራሱ ክርስቶስ ሲሆን ትንሣኤውም መልሶ ሞት ነበረበት:: ክርስቶስ ግን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው:: ዳግመኛ ሞትም የለበትም::

ጌታችን በአዳም ምክንያት የመጣዉን ሞት ይሽር ዘንድ በተዋሀደዉ ስጋ ሞቶ ተቀበረ:: ከዚያም በሦስተኛዉ ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ:: ጌታችን ራሡ ስለሰዉ ልጆች ድህነት በፈቃዱ መከራን እንደሚቀበል በመሥቀል እንደሚሠቀል እንደሚሞት እና በሦስተኛዉም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሳ አሥቀድሞ “እነሆ ወደኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰዉ ልጅም ለካህናት አለቆች እና ለፃፎች አልፎ ይሠጣል፤ የሞት ፍርድ ይፈረድበታል፤ ለአህዛብም አሣልፈዉ ይሠጡታል፤ ይዘባበቱበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤  ይገዱሉታልም፤ በሶስተኛዉም ቀን ይነሣል ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል:: ይህንን የተፈጸመውን ትንሳኤ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዓመቱ ያከብረዋል::

እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here