ከ406 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ለማልማት የማሳ ዝግጅት እየተደረገ ነው

0
97

406 ሺህ 246 ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ለማልማት የማሳ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አስታውቋል፤ በበጀት ዓመቱ ዘመናዊ የግብርና ዘዴን በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት መደረጉንም ነው የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ያስታወቀው።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ቤዛዊት ጌታሁን እንደተናገሩት ዞኑ ለዘመናዊ የግብርና ሥራ ምቹ በመሆኑ ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ኃላፊዋ ወቅቱ ለእርሻ ሥራ አመቺ መሆኑን ጠቅሰው አርሶ አደሩ በእርሻ ሥራ መሠማራቱን ነው ያብራሩት።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ 406 ሺህ 246 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን በዕቅድ የተያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 129 ሺህ 676 ሄክታር መሬት ታርሷል። አምስት ሺህ 176 ሄክታሩ ደግሞ በትራክተር መታረሱን ነው የተናገሩት። በኩታ ገጠም (በክላስተር) ለማረስ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነውም ብለዋል። ምርታማነትን በሄክታር 43 ኩንታል ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም አክለዋል።

ዘመናዊ የእርሻ ሥራን በመከተል ምርታማነትን ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥተዉ እየሠሩ መሆኑን መምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ምክረ ሐሳባቸውን ለአርሶ አደሩ እያካፈሉ ነው።

እንደ ወ/ሮ ቤዛዊት ጌታሁን ማብራሪያ በምርት ዘመኑ 840 ሺህ 871 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል።  እስካሁንም 216 ሺህ 96 ኩንታል ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ገብቷል። ስምንት ሺህ 185 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።

እንዲሁም 39 ሺህ 754 ኩንታል የበቆሎ እና ሌሎች ምርጥ ዘር ለማቅረብ በዕቅድ ተይዟል። እስካሁንም ሁለት ሺህ 202 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።

በ2017/2018 የምርት ዘመን 17 ሚሊዮን 792 ሺህ 264 ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here