“Road to 29” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ ወይስ የህልም ሩጫ?

0
8

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በክብር እና በናፍቆት፣ በውድቀት እና በፀፀት ስሜቶች መካከል የሚዋዥቅ ረጅም ታሪክ አለው። አህጉራዊውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከመሰረቱት ቀዳሚ ሀገራት አንዷ የሆነችው እና የዐስረኛው የአፍሪካ ዋንጫን በክብር ያነሳችው ኢትዮጵያ ከዚያ ወዲህ ባሉት ዐስርት ዓመታት ግን ስሟ ከመስራችነት ወደ ተሳታፊነት፣ ከውጤታማነት ወደ ተመልካችነት ተቀይሯል። ላለፉት ዐስርት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጉጉት እና በተስፋ መቁረጥ ስሜቶች መካከል ሲዋዥቅ ቆይቷል።

አሁን ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህንን ታሪክ ለመቀልበስ እና ሀገሪቱን ወደ አፍሪካ እግር ኳስ ማማ ለመመለስ “Road to 29” (የ2029 ጉዞ) የተሰኘ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ይፋ አድርጎ ወደ ተግባር ገብቷል። ለ”Road to 29” በሚል የተቋቋመው ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ያስመዘገበው ውጤት የሀገሪቱን እግር ኳስ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረውን ጉዞ ያሳያል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ ያደረገው “Road to 29” ፕሮጀክት የኢትዮጵያን እግር ኳስ መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት ያለመ ሳይንሳዊ ፍኖተ ካርታ ነው።  የፕሮጀክቱ ዋና ማጠንጠኛ ሁለት ግቦችን የያዘ ነው፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ በ2029 እ.አ.አ የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ የሚያስችላትን የዲፕሎማሲ እና የመሰረተ ልማት ዝግጅት ማሟላት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሀገራችን ለሚካሄደው ታላቅ ውድድር ተፎካካሪ እና አሸናፊ የሆነ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መገንባት ነው። የፌዴሬሽኑ የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረማሪያም ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሮጀክቱ የረጅም ጊዜ እቅድ ነው ብለዋል። “አላማው በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ዋንጫውን በቤታችን ውስጥ ለማስቀረት የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የዚህ ታላቅ ዕቅድ የመጀመሪያው ውጤት በቅርቡ በምሥራቅ አፍሪካ የሴካፋ ዞን የካፍ ከ17 ዓመት በታች ማጣሪያ ውድድር ላይ ታይቷል።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን (ቀይ ቀበሮዎቹ) ያሳዩት ብቃት እና ያስመዘገቡት ውጤት የ”Road to 29” ፕሮጀክት ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ያረጋገጠ ነበር።  ከዚህም ባሻገር ቡድኑ በውድድሩ ባሳየው ስፖርታዊ ጨዋነት (Fair Play) አሸናፊ ሲሆን ይህም በታዳጊዎቹ ዘንድ ከቴክኒክ ክህሎት ባልተናነሰ ለስነ-ምግባር እና ለዲሲፕሊን ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳይ ነው። ታዳጊዎች ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፋቸው ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና እና ሞሮኮ ከመሳሰሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያላን ልምድ ለመቅሰም ለታዳጊዎች ወርቃማ እድል ይፈጥርላቸዋል።

አሁን ላይ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ከአምስት ዓመት በኋላ በ2029 እ.አ.አ እድሜያቸው 21 እና 22 ዓመት ይደርሳል። ይህ የእድሜ ክልል ደግሞ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ምርጥ ብቃታቸውን ለማሳየት ትክክለኛ እድሜ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ፌዴሬሽኑ ይህንን ቡድን ለመገንባት በአዲስ አበባ እና በሲዳማ ከተሞች ማዕከልነት ከ40 በላይ የታዳጊ ክለቦች እና ፕሮጀክቶች የተሳተፉበት ሰፊ የውድድር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ከዚህ ውድድር የተገኙ 85 ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች ወደ ማጣሪያ ካምፕ የገቡ ሲሆን ለ15 ቀናት በቆየው የቴክኒክ፣ የታክቲክ እና የአካል ብቃት ምዘና (Screening) ሂደት በኋላ የመጨረሻዎቹ 25 ምርጥ ተጫዋቾች ተለይተዋል። እነዚህ ታዳጊዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደፊት ተስፋዎች ተደርገው የተወሰዱ ሲሆን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየሰሩም ይገኛሉ።

ቡድኑ በአጭር ጊዜ እቅድ በሴካፋ ዞን (CECAFA) በሚደረጉ የማጣሪያ ውድድሮች ውጤታማ በመሆን ወደ አፍሪካ ዋንጫ አልፏል። በረጅም ጊዜ ደግሞ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ዋና ብሄራዊ ቡድን በመሆን ኢትዮጵያን ለዓለም ዋንጫ ማብቃት ነው። ይህንን ፕሮጀክት ለማሳካትም ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ በታዳጊዎች ልማት ላይ አስደናቂ ሥራ ከሰሩት  ሞሮኮን ከመሰሉ ሀገራት ተሞክሮ ለመውስድ እየተሰራ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ከሞሮኮ በተጨማሪ ከሳውዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ (MOU) መፈራረሙ አይዘነጋም። ይህ ስምምነት በቴክኒክ ድጋፍ፣ በወጣቶች ልማት እና በልምድ ልውውጥ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል እንደሆነ ተነግሯል።

የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ከሜዳ ላይ ጨዋታ ባልተናነሰ የመሰረተ ልማት ዝግጅትንም ይጠይቃል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) የውድድሩን ተሳታፊዎች ቁጥር ከ16 ወደ 24 ከፍ ማድረጉን ተከትሎ አስተናጋጅ ሀገራት ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች  ከፍ ብለዋል። አሁን ባለው መስፈርት መሰረት ውድድሩን ለማስተናገድ ቢያንስ ስድስት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እና ከአራት በላይ አስተናጋጅ ከተሞች እንደሚያስፈልጉ የካፍ ኦንላይን መረጃ ያመለክታል።ይህንን ፈተና ለመወጣት ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የስታዲየም ግንባታ እና የማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። በቅርቡም የካፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና አማካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአርባ ምንጭ፣ በባሕር ዳር፣ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ስታዲየሞች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በተሰጠው ሙያዊ አስተያየት መሰረት የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረማሪያም ተናግረዋል።

በ”Road to 29” ፕሮጀክት ውስጥ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልዩ ቦታ ተሰጥቶታል። ብሄራዊ ቡድኑ በርካታ ድሎችን ያስመዘገበበት እና በሕዝብ ድጋፍ የሚታወቅ መሆኑም የሚታወስ ነው። ታዲያ ስታዲየሙ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ብሄራዊ ቡድኑን ከስደት ከመመለሱ ባሻገር ለ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ጥያቄ ለማቅረብ ትልቁ መተማመኛችን ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ። “Road to 29” በፌዴሬሽኑ የተነደፈ ቢሆንም ስኬቱ የሚረጋገጠው ግን በሁሉም አካላት ርብርብ ነው። ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክስ አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ የመንግሥት  የግሉ ዘርፍ እና የመላው ሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

የፕሮጀክቱ ዋና ማጠንጠኛ እ.አ.አ በ2029 ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ እንድታስተናግድ እድሉን ማሸነፍ ነው። ይሁን እንጂ ውድድሩን ማስተናገድ ግን ብቻውን ግብ አይደለም፤ ይልቁንም በሜዳው ላይ ተጋጣሚን የሚያሸብር እና ዋንጫውን በቤታችን ለማስቀረት የሚያስችል ብሄራዊ ቡድን መገንባት አለበት ተብሏል። “ህልማችን በ2029 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ነው፤ ያ ከተሳካ ለዚያ የሚመጥን ብሄራዊ ቡድን የማዘጋጀት ሥራ ከወዲሁ መጀመር አለበት” ሲሉ አቶ አብርሃም የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ያብራራሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የሚረጋገጠው የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው ሲቀጥሉ እና የ”Road to 29” ዕቅድ ከወሬ ባለፈ ወደ መሬት ሲወርድ ብቻ ነው። አሁን ኳሱ ያለው ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በቢሮ፣ በግንባታ ቦታዎች እና በመንግሥት እጅ ላይ ነውና አሚኮ በኩር ስፖርት ዝግጅት ክፍልም ትኩርት ሊሰጠው ይገባል የሚል መልዕክት አለው።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here